ከፍተኛ መጠን ስኳርን ከተመገቡ ለስኳር በሽታ ያጋልጣል?
በአለማችን ላይ እያደጉ ያሉ አገሮችም ሆኑ ያደጉ አገሮች በእኩል አይን አይተው የሚጎዳው እና በአሁኑ ጊዜ በብዛት እየጨመረ ያለው የስኳር በሽታ እ.ኤ.አ. በ2016 ውስጥ እንዳለም 422 ሚሊዮን (422 Million) ሰዎችን ይዟል፡፡ ይህ በሽታ እየጨመረ ያለው ለምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ በርካታ ተመራማሪዎች የሚሰጡት ምላሽ ቁጥሩ የጨመረው የሰዎች የአካል ክብደት በመጨመሩ ነው በማለት ነው፡፡ ይህ የአካል ክብደት ከመጠን በላይ መጨመርም በስኳር በሽታ አይነት ሁለት (Type II Diabetes Mellitus) ለመያዝ ስለሚያጋልጥ ነው። የስኳር በሽታ ካለባቸው ሰዎች በከፊሉ ህመሙ ያለባቸው መሆኑን አያውቁም። የአሜሪካ የበሽታዎች ቁጥጥር እና መከላከያ ድርጅት (CDC) እንደገለፀው በአሜሪካ አገር ውስጥ ብቻ 23.1 ሚሊዮን በሚሆኑ ሰዎች አካል ውስጥ የስኳር በሽታ ተገኝቶ ህክምና ላይ ያሉ ሲሆን 7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ይህ በሽታ ያለባቸው መሆኑን ስለማያውቁ ህክምና ሳያገኙ ከበሽታው ጋር እየኖሩ ይገኛሉ። አሜሪካ ያደገች እና ሰው ሳይታመም በመመርመር በታወቀች አገር ውስጥም ይህን ያህል ሰው በሽታው እያለባቸው የማያውቁ ከሆነ በሀገራችን ውስጥ ምን ያህል ሰው ተመርምሮ እየታከመ ይገኛል የሚለውን መገመት ከባድ አይደለም። ይህ የስኳር በሽታ ተመርምሮ ያለባቸው መሆኑን ማወቅ ቀላል በመሆኑ በበርካታ የጤና ድርጅቶች (ጤና ጣቢያን ጨምሮ) የሚገኝ እና ዋጋውም የተጋነነ አይደለም። ሳይታወቅ እና ሳይታከም ከቆየ ግን ቀስ በቀስ እንደ አይን፣ ኩላሊት፣ ልብ እና የነርቭ ስርአት ያሉ የሰውነት አካሎቻችንን በመጉዳት በከፋ ደረጃ ላይ ሊያደርስ ይችላል፡፡
ስኳር በሽታ ምንድነው?
ከፍተኛ መጠን ስኳርን ከተመገቡ ለስኳር በሽታ ያጋልጣል? የሚለው ጥያቄ ቁጥራቸው ባላነሰ ሰዎች ዘንድ የሚነሳ ነው፡፡ መልሱ አያጋልጥ ነው፤ ጤናማ ሰው ከፍተኛ መጠን ስኳር በመመገብ ለስኳር በሽታ አይጋለጥም፡፡ ነገር ግን በስኳር በሽታ ከተያዘ በኋላ ስኳር (ለአፍ ጣፋጭ የሆኑ) ምግቦችን መብላት ለችግር ያጋልጣል፡፡ ሰውነታችን ምግብ በምንበላበት ጊዜ የምንበላውን ምግብ ወደ ግሉኮስ በመቀየር ይጠቀምበታል። በሰውነት ውስጥ ያለውን ግሉኮስ ሰውነታችን እንዲጠቀምበት የሚያደርጉ ኢንሱሊን (insulin) የሚባል ሆርሞን ነው፡፡ ኢንሱሊን የሚባል ሆርሞንን የሚያመርተው ጣፊያ ነው፡፡ ይህ ኢንሱሊን ምግብ ስንመገብ ስኳሩን (ግሉኮሱን) ሰውነታችን እንዲጠቀም በማድረግ ዝቅ ያደርጋል፡፡ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ህመማቸው ኢንሱሊን የሚባል ሆርሞን ሰውነታቸው ማምረት ከማቆሙ የተነሳ ነው፡፡ የኢንሱሊን ሆርሞን ከሰውነታቸው መጥፋትም በሰውነታቸው ውስጥ ያለው ስኳር (ግሉኮስ) ያለቁጥጥር ከፍ እንዲል እና ልዩ ልዩ ምልክቶችን እንዲያሳይ ያደርጋል፡፡
ሁለቱ የስኳር በሽታ አይነቶች መለያ ምንድናቸው?
ስኳር በሽታ ሁለት ዋና ዋና አይነቶች አሉት፡ እነሱም በስኳር በሽታ አይነት አንድ (Type I Diabetes Mellitus) እና በስኳር በሽታ አይነት ሁለት (Type II Diabetes Mellitus) ይባላሉ፡፡ ሁለቱም አይነቶች ሰውን የሚይዙበት ዘዴ እና የሚታከሙበት ዘዴ ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡
ስኳር በሽታ አይነት አንድ (Type I Diabetes Mellitus) የሚባለው የስኳር በሽታ አይነት ብዙውን ጊዜ በእድሜያቸው ልጅ እና ወጣት የሆኑ (ብዙውን ጊዜ ከ30 አመት በታች) የሆኑትን ሰዎች የሚይዝ ነው፡፡ የአንደኛ አይነት የስኳር በሽታ ሰውን የሚይዘው ኢንሱሊንን የሚያመርቱ የጣፊያ (Pancreas) ሆርሞን ሴሎች መጎዳት/ ማለቅ ነው፡፡ ከሰውነታቸው ውስጥም ኢንሱሊን ሙሉ በሙሉ መታጣት ነው፡፡ በርካታውን ጊዜ የሚታወቅባቸው ሶስቱ ምልክቶች ከፍተኛ የውሃ መጠማት፣ ከፍተኛ ሽንት መሽናት እና ከመጠን በላይ መራብ ናቸው። በተጨማሪም የሰውነት ከመጠን በላይ መክሳት፣ ማድከም የመሳሰሉትን ምልክቶች ሊያስከትል ይችላል፡፡ የዚህ ስኳር በሽታ አይነት ህክምና በየቀኑ (በቀን 2 ወይም ከዛ በላይ) ኢንሱሊን በመወጋት ይሰጣል፡፡
ስኳር በሽታ አይነት ሁለት (Type II Diabetes Mellitus) በሰውነት ውስጥ የተወሰነ ኢንሱሊን ይመረታል፡፡ ነገር ግን አነስተኛ እና በትክክል የማይሰራ ነው፡፡ ይህ አይነት እድሜያቸው አዋቂ እና ከዛ በላይ መሆናቸው እንዲሁም የሰውነታቸው ክብደት ከፍ ያለውን የሚይዝ ነው፡፡ ይህ አይነት ምልክት ሳያሳይ በርካታ አመታት ከቆየ በኋላ ሊገኝ ይችላል፡፡ ለዚህ የስኳር በሽታ አይነት ከሚያጋልጡት ውስጥ የሰውነት ክብደት ከመጠን ከፍ ማለት፣ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ (በተለይም ስራቸው አንድ ቦታ ቁጭ ብለው የሚሰሩ ሰዎች)፣ የእድሜ መጨመር (እድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር በሁለተኛ አይነት የስኳር በሽታ የመያዝ እድል እየጨመረ ይሄዳል)፣ ከቤተሰብ ውስጥ (ለምሳሌ እናት፣ አባት፣ ወንድሞች/ እህቶች) ሁለተኛ አይነት የስኳር በሽታ ያለባቸው መኖር እና እንደ ደም ግፊት፣ የኮሊስትሮል (cholesterol) መጠን መጨመር ሌሎች ህመሞች ናቸው፡ ፡ የህክምናው ሁኔታም የሚዋጡ መድሃኒቶች (ክኒን) በመውሰድ ሊታከም የሚችል እና የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግም እራስን መርዳት የሚቻል ነው፡፡ በመጨረሻም መድሃኒት በመዋጥ የስኳር መጠን ከሰውነት ውስጥ ዝቅ ካላለ ግን ኢንሱሊን ወደ መወጋት ህክምና ይኬዳል፡፡
የስኳር በሽታ ባይታከም ምን አይነት ችግሮችን ያስከትላል?
የስኳር በሽታ ህይወትን የሚቀጥፍ እና የሰው እድሜ የሚቀንስ፣ ከሰውነት አካላት ውስጥ በህይወት ለመኖር የሚያስፈልጉ እንደ ልብ፣ ኩላሊት እና አንጎል በመጉዳት ነው፡፡ ነፍስን የማይቀጥፉ ነገር ግን የእለት ተእለት ኑሮአችንን የሚወስኑ እንደ አይን እና እግር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። የስኳር በሽታ በሰውነት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ዝርዝር በአጭሩ ከዚህ በታች ማየት እንችላለን፡፡
- በልብ እና ደም ስርአት፡ ላይ ውስጣዊ ደም ስሮችን በመጉዳት ለልብ በሽታ (ድንገተኛ የልብ ድካምን ጨምሮ) እና በአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስን ያስከትላል፤
- የነርቭ ስርአት፡ በጣም ትናንሽ የሆኑ የደም ስሮች (capillaries) ነርቭን የሚመግቡ ስሮችን በመጉዳት የነርቫችን ስርአት በተለይም በእግር ውስጥ የሚገኙ ነርቮች ስርአት በመጉዳት የማቃጠል፣ የመውጋት እና የመደንዘዝ ስሜቶች እንዲታይ ያደርጋል፣
- ኩላሊት፡ ኩላሊት የስኳር በሽታ ከሚጎዳቸው አካላት ውስጥ አንጋፋ ሲሆን የስኳር በሽታ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ኩላሊት መተካት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ያደርሳል፤
- እግር፡ የእግር ነርቭ ከተጎዳ በኋላ የመቁሰል እና ኢንፌክሽን የመኖር እድል ከፍተኛ ነው፤ በስኳር በሽታ የተያዘ ሰው እግር ቢቆስል እና ኢንፌክሽን ቢኖር የመዳን እድሉ ዝቅተኛ ነው፤ ከጊዜ በኋላም እግር ወደ መቆረጥ ይሄዳል፤
- አይን፡ የስኳር በሽታ የሰው አይን ስሮችን በመጎዳት በመጨረሻ ላይም ብሌኑን ያጠፋል፤ በተጨማሪም እንደ ከተራክት (cataract) እና ግላኮማ (glaucoma) ላሉ የአይን በሽታዎችም ያጋልጣል፤
- እንደዚሁም የሰውነት ቆዳ፣ የጆሮ መስማትን መጎዳት እና ሌሎች በርካታ ጉዳቶች ያጋልጣል፤
ይቀጥላል ……
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 3/2012