በመከላከያ ውስጥ እየተሰራ ያለው አዲስ አደረጃጀት (ሪፎርም) ሥራ የሠራዊቱን ግዳጅ የመወጣት አቅም የማጠናከርና ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ የሚያገለግልበት ሁኔታ እንደሚፈጥር የመከላከያ ሚኒስቴር የሠራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች ሰሞኑን ይፋ አድርገዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ የሚንቀሳቀስበትን አዲስ አደረጃጀት (ሪፎርም) ማድረጉ ጥሩ ቢሆንም ዋናው ግን ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ ሥራ ሲሰራ ነው ሊታመን የሚችለው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር መረራ ጉዲና ይናገራሉ፡፡
በመከላከያ እየተሰራ ያለው አዲስ አደረጃጀት (ሪፎርም) ሥራ የሠራዊቱን ግዳጅ የመወጣት አቅም የማጠናከርና ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ የሚያገለግልበት ሁኔታ እንደሚፈጥር የገለጹት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሞላ ኃይለማርያም ፣አዲሱ አደረጃጀት ሠራዊቱ ለህገ መንግሥቱ ተገዥ ሆኖ የህዝብ አለኝታነቱ የሚጠናከርበት ነው፤ የብሄር፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦች ተዋጽኦ እንዲመጣጠን አድርጓል፤ መከላከያ ዕጩ መኮንኖችን ከዩኒቨርሲቲ እንዲቀጥር ያደርጋል፣ የሰራዊቱ ማሰልጠኛ ማዕከላትን አቅም የሚያጠናክር የሪፎርም ሥራ ነው ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
በሪፎርሙም የምድር ሀይል፣ የአየር ሀይል፣ የልዩ ዘመቻዎችና የባህር ሀይል፣ የሳይበር ሴኩሪቲ በሚል ይደራጃል፡፡ ስድስት የነበረው ዕዝ ቁጥርም ወደ አራት ዝቅ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም የአዲሱን አደረጃጀት ተከትሎም የቆዩት አመራሮች በአዳዲስ መተካት ተችሏል፡፡ ባለፉት ዓመታት ከክልሎችም ሆነ ከሌሎች የጸጥታ አካላት በመከላከያ ገለልተኝነት ዙሪያ ስሞታዎች ይቀርቡ እንደነበር አውስተው፣ በአሁኑ ጊዜ ግን እነዚህን ስሞታዎች የሚፈታ የሪፎርም ሥራ ተሰርቷል ነው ያሉት ሌተናል ጀነራል ሞላ፡፡
የቀድሞው የአየር ሀይል አዛዥ ሜጀር ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) በ21ኛው ክፍለ ዘመንና የሳይበር ሴኩሪቲ ችግር በሆነበት ዓለም ከ10ኛ ክፍል ብቻ ወታደር እየቀጠርክ የምትሄድበት ሁኔታ አዋጪ አይደለም ይላሉ፡፡ መከላከያ ሚኒስትርም ብቃት ያላቸው ሰዎች ከውጭ ሊቀጥር ባለመቻሉም የተማረ የሰው ሀይል እጥረት አጋጥሞታል፡፡ በተለይ ጥልቅ ምርምር የሚጠይቁ ወታደራዊ ሥራዎች እየተዳከሙ መጥተዋል፡፡ ስለዚህ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሰዎችን ማስገባት ያስፈልጋል፡፡እነዚህ የወደፊቱ የመከላከያ ሠራዊቱ መሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ዕጩ መኮንኖች የወደፊቱን ዓለም አቀፍ ተሞክሮን መቅሰም፣ ምርምሮችን መስራትና ዘመናዊ ሠራዊት የመገንባት ሂደቱን ማፋጠን የሚችሉ መሪዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የተማሩ ባለሙያዎችን ከውጭ መቅጠር የሚችልበትን በር መክፈቱ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱን በእውቀትና በችሎታ እንዲመራ ለማድረግም ያስችለዋል፡፡
ሌላው የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች በቅርቡ ለውጡን እንደግፋለን የሚል መግለጫ መስጠታቸው ትክክል አይደለም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ህዝብ ቢደግፈውም ባይደግፈውም ለውጥ ፖለቲካ ፕሮግራም ነው፡፡ ስለዚህ መከላከያ ሠራዊት ለውጥ ዕደግፋለሁ እቃወማለሁ ማለት የለበትም፡፡ምክንያቱም ህገ መንግሥቱን ብቻ ነው መጠበቅና ማስጠበቅ ያለበት እንጂ መከላከያና ፖሊሲ የለውጥ ደጋፊ ነኝ ማለት አይችሉም ሲሉ ተችተዋል – ሜጀር ጀነራል አበበ፡፡
‹‹በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለውጡን ማደናቀፍ መብት ነው፡፡ ህግ መጣስ ብቻ ነው የሚያስከስሰው ያሉት ሜጀር ጀነራሉ፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆኑን ይፋ ማድረጉ ጥሩ ቢሆንም የአስተሳሰብ፣ የአደረጃጀትና የአሰራር ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህን የአደረጃጀትና የአሰራር ለውጥም ወደ መሬት ሊወርድ ይገባል ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሠራዊቱ ተፈልጎም ሆነ ሳይፈለግ በብሄር ተዋጽኦ እየተመጣጠነ እየሄደ ነበር፡፡ አሁን በአዲሱ አደረጃጀት የበለጠ እንዲሆን ተደርጎ ተሰርቶ ከሆነ የበለጠ ጥሩ ነው የሚሆነው፡፡ ሠራዊቱ በብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን በአመጣጠነ መልኩ የተዋቀረ መሆኑ ጥሩ ቢሆንም በአንድ ጊዜ ማመጣጠን አይቻልም፡፡ ሆኖም ማመጣጠኑ በተፈለገው መንገድ አልሄደም በሚለው ሃሳብ እስማማለሁ ብለዋል፡፡
ለምሳሌ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ሠራዊቱን ለማመጣጠን ተብሎ ብዙ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ወታደሮች ከሠራዊቱ እንዲቀነሱ ተደርጓል፡፡ በኃላፊነት ደረጃም ቢሆን እኩል ብቃት ያላቸው ሰዎች አንዱ ጀነራል ሲሆን፣ ሌላው ኮሎኔል እንዲሆን ተደርጓል፡፡ እናም ማመጣጠን ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ጭምር ነው፡፡ እስካሁን ድረስም የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም በሂደት እየተመጣጠነ መጥቷል፡፡ አሁን ደግሞ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ተዋጽኦ በአመጣጠነ መልኩ ሪፎርሙ መካሄዱ ይበልጥ አስፈላጊ ነው የሚሆነው የሚል እምነት አላቸው፡፡
የሰሜን ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጀነራል ጌታቸው ጉዲና በበኩላቸው፣ በአገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቆምና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ሠራዊቱ ከተለያዩ የፀጥታ አካላትና ህብረተሰቡ ጋር ትዕግስት በተሞላበት ሁኔታ እየሰራ ይገኛል፡፡ በችግሩ ተዋንያኖች ላይ ቆንጠጥ ያለ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ግጭቱ ቢቀንስም አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልቆመም፡፡
ለምሳሌ በምስራቁ የአገራችን ክፍል በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ቀደም ሲል ከጫፍ ጫፍ የሚከሰት ግጭት ነው የነበረው፡፡ አሁን ግን በከፍተኛ ሁኔታ ግጭቱ ቀንሷል፡፡ ሆኖም አልፎ አልፎ የሚከሰት ግጭት አለ፡፡ በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወሰንን ከለላ በማድረግ የሚነሱ ግጭቶች ተስተውለዋል፡፡ በአማራና በትግራይ ክልሎችም በማንነት ሳቢያ የሚነሱ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ ደቡብ ክልልም የተከሰቱት ችግሮች በተመሳሳይ ከማንነት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
አጠቃላይ ግጭቶቹ በባህሪያቸው መወሳሰብና የተለያየ መልክ የመያዝ ሁኔታ ይታይባቸዋል፡፡ ስለዚህ ችግሮቹን ለመፍታት የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍ የግጭቱ ተዋንያኖችን በመለየት እርምጃ የመውሰድ ሥራ ትዕግስት የሚጠይቅ ነው፡፡
በተለይ የማረጋጋት ሥራው ወታደራዊ ሥራ ብቻ ባለመሆኑ በአብዛኛው ከህብረተሰቡም ሆነ ከሌሎች የጸጥታ አካላት የተቀናጀ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ የአካባቢው የጸጥታ ሀይልና የህዝቡን ሁለተናዊ ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ እናም በአጭር ጊዜ ግጭቶችን ለማስቆም ወታደራዊ ስምሪት በማድረግ ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት ሠራዊቱ በቦታው እያለ ግጭት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይህንን በተረጋጋ መንገድና ጉዳቱን በሚቀንስ መልኩ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው ሲሉ ነው የሚናገሩት፡፡
በመጀመሪያ በአካባቢው የፀጥታ ኃይል ችግሩን ለመፍታት ሥራ ይሰራል፡፡ ከእሱ አቅም በላይ ከሆነ ደግሞ በክልሎች ጥያቄ ሠራዊቱ የሚሰማራ ይሆናል፡፡ ይህ የራሱ ሂደት አለው፡፡ ምክንያቱም በወታደራዊ ኃይል ብቻ የመፍታት ዝንባሌ ካለ ውጤቱ ጥሩ አይመጣም፡፡ አብዛኛዎቹ ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ግጭቶች ሲጀመሩ በጣም አነስተኛና እርምጃ ለመውሰድም ውስብስብ ናቸው፡፡ ስለዚህ የችግሩን ተዋናዮች ለመለየት ጊዜ የሚጠይቅ፣የሁሉንም የፀጥታ አቅም ማቀናጀት የሚያስፈልግ ነው፡፡ ህዝቡንም የማሳተፍ ጉዳይ አስፈላጊ ነው፡፡ እናም ጉዳዩን ከዚህ አንጻር ማየት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
የአገር ውስጥ የፀጥታ ሥራዎች የሁሉንም ቅንጅት የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ጥቂት አመራሮችና የፀጥታ ኃላፊዎች ግጭቱ እንዲቀጥል በስውር የሚንቀሳቀሱ አሉ፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንደሆነ እንጂ ጠንከር ያለ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በምዕራብ ወለጋ የተነሳው ግጭት ሰበቡ ወሰን ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ችግሩን ለመፍታት የሁለቱም የክልል ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ በመሆን የችግሩ ተዋናዮች ላይ እርምጃ ለመውሰድና ችግሩን በእርቅ ለመፍታት ዕቅድ ወጥቶ ወደ ተግባራዊ ሥራ ተገብቷል ሲሉ ሜጀር ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና ይገልጻሉ፡፡
ሌተናል ጀነራል ሞላ ኃይለማርያም በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ግጭቶችን ለማረጋጋት ሰፊ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ከክልሎች ጋር በመግባባት ግጭቶችን ለማስቆምና ለመከላከል ገለልተኛ ሆኖ እየፈጸመ ነው፡፡ ችግሮች ካሉ እንኳ ገንቢ ሀሳብ በመስጠት ማስተካከል ይቻላል፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ተላብሶ የተፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቆም ሳይታክት ቀንና ሌት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት የምስራቅ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጀነራል ዘውዱ በላይ ሠራዊቱ በጥብቅ ዲስፕሊን የሚመራ ነው ብለዋል፡፡
ሌተናል ጀነራል ሞላ ቀደም ሲል መከላከያ ሠራዊቱ ገለልተኛ አይደለም የሚል ወቀሳ ሲደርስ እንደነበር አውስተው፣በአዲሱ አደረጃጀትም ከፖለቲካ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ዜጎችን በእኩል የሚያይና የሚያገለግል ኃይል ሆኖ እንዲገነባ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ የሪፎርሙ ግብ ለህገ መንግሥቱና ለህዝቡ ታማኝ የሆነ አገራዊ ሠራዊት መገንባት ነው፡፡ በሰው ፍላጎት የሚመራ ሳይሆን ሰው ቢቀያየርም ግልጽ በሆነ የአሰራር ሥርዓት የሚመራ ሠራዊት የመገንባት ሥራ ነው የተሰራው፡፡ ከባለፈው በተሻለ መልኩ ኢትዮጵያን ተምሳሌት በሆነ ተዋጽኦን አማክሎ ሊደራጅ ችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት ሠራዊቱ ብሄር ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የሚወክል ሠራዊት ነው ሲባል ቢቆይም በተግባር ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር መረራ ጉዲና፣አሁንም በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ አዲስ አደረጃጀት ተግባራዊ ስለመደረጉ የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡
ሆኖም በመገናኛ ብዙሃን እንደተነገረው የመከላከያ ሠራዊት ከፖለቲካ ነጻ የሚያደርግ አደረጃጀትና አሰራር ከተገበረ ጥሩ ነው፡፡ በጣም ተፈላጊም ጭምር ነው፡፡ ቀደም ሲል የነበረውን ማለትም በንጉሱ፣በደርግና በኢህአዴግ ዘመን የነበረው የፖለቲካ መሳሪያ ከሆነውን የመከላከያ ሠራዊት መልክ የሚያሲዝ ይሆናል፡፡ ግን እውነት መሆኑ ነው ዋናው ጉዳይ ይላሉ፡፡
ምክንያቱም እስካሁን ድረስ እኛ የምናው ቀው የተጨበጠ፣መሬት ላይ ያየነው ነገር የለም፡፡ ሆኖም የሚባለው ነገር የሚተገበር ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም አሁንም የመከላከያ ሠራዊቱ የህዝብ አለኝታነቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሱ ስሞታዎች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ለምሳሌ እኛ ከቦረና፣ከወለጋና አንዳንድ አካባቢዎች መከላከያ በሚፈለገው መልኩ ህዝቡን እየጠበቀ አይደለም፡፡ መከላከያ እያየ እንደበደባለን፣እንፈናቀላለን የሚል ስሞታ ይደርሰናል፡፡ በዚህ ምክንያትም ለሚፈና ቀለው ህዝብ ሠራዊቱ የህዝብ አለኝታነቱን እያሳየ አይደለም የሚል ቅሬታ የሚያነሱ ወገኖች መኖራቸውን አልሸሸጉም፡፡ ስለዚህ ከዚህ ተነስቶ የተባለው አደረጃጀት ምን ያህል ሥራ ላይ እንደሚውል ውሎ አድሮ አስተያየት መስጠቱ ይበጃል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲልም ኢህአዴግ ሠራዊቱ ከፖለቲካ ገለልተኛ ነው ሲል ነበር፡፡ ለምሳሌ ህወሓት ለሁለት ሲከፈል መወገን ያልፈለጉ የኢህአዴግ ጀነራሎች ከሠራዊቱ የተሰናበቱ መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ እናም ኢህአዴግ ሠራዊቱን ሲፈልግ ይጠቀምበታል፤ ሲፈልግ ደግሞ ገለልተኛ ነው ይላል፡፡ ስለዚህ ሠራዊቱ ከፖለቲካ ነጻ ነው የምንለው ውጭ ሆነን በመገናኛ ብዙሃን በምንሰማው ሪፎርም ሳይሆን በሚወስዳቸው እርምጃዎች ፈተናዎችን ሲያልፍ ነው ሲሉ ሞግተዋል፡፡
ለአብነት ያህል በአገሪቱ በተወሰኑ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶች ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ተፈናቅሏል፡፡ በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች፣በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጉጂ ኦሮሞና ጌዲዮ፣ትንሽም ቢሆን ወልቃይት ጠገዴና ራያ አካባቢዎች ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ ነገር በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ሀሜታን ፈጥሯል፡፡ ስለዚህ የመከላከያ ሠራዊት ለህዝብ ወገንተኝነቱን እያሳየ የአካባቢውን ፀጥታ ማስጠበቅ አለበት፡፡ አለበለዚያ ህዝቡ እንደ ጠላት እንጂ እንደ ወዳጅ አያየውም፡፡ሆኖም መከላከያ ሠራዊት ባለባቸው አካባቢዎችም ይህ ጉዳይ በቀላሉ ሊታይ አይገባም፡፡ እናም ሠራዊቱ በሚነሱ ግጭቶች ገለልተኛ፣ ከፖለቲካ ነጻ መሆኑንና የህዝብ አለኝታነቱን በተግባርም ማረጋገጥ አለበት የሚል እምነት አላቸው፡፡
ለምሳሌ የደርግ ሠራዊት ህዝብ የሚያከብረው ባለመሆኑ ግማሽ ሚሊዮን ሠራዊት ተበትኖ ነው የቀረው፡፡ የአሁኑም ሠራዊት ከዚህ ህዝብ በሚሰበሰብ ግብር እንደመተዳደሩ የህዝቡ ጋሻ መሆንና የህዝብ ፍቅርን መግዛት መቻል ይኖርበታል ባይ ናቸው፡፡
እስካሁን በነበረው ረጅም ጊዜያት በንጉሱ፣በደርግና በኢህአዴግ ጊዜም ሠራዊቱ የገዥው ወገን ክንፍ ሆኖ ነው የሚቆጠረው፡፡ በተለይ ለ27 ዓመታት ከህዝብ ተነጥሎ የኖረ ሠራዊት ነው፡፡ ይህ ሠራዊት የህዝብ ሠራዊት ነኝ ለማለት ጥርጣሪዎችን ማስወገድ አለበት፡፡ ስለዚህ ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ ለማለትና በህዝቡ ያለውን የተዛባ ዕይታ ለመቀየር ብዙ የአደረጃጀትና ስርዓት የመቀየር ሥራዎችን መስራት አለበት፡፡ ሠራዊቱ የመንግሥት ጠባቂ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ጠባቂ መሆኑን በተግባር መገለጽ አለበት፡፡
‹‹የፖለቲካ ስርዓቱ የሚፈቅድ ከሆነ ነጻና ገለልተኛ የአገር መከላከያ ሠራዊት መገንባት ቀላል ነው›› የሚሉት ዶክተር መረራ፣ሠራዊቱ ብቻውን ገለልተኛ ነኝ ስላለ ሳይሆን የፖለቲካ ስርዓቱ ነጻ ተቋማትን የሚፈጥር ከሆነ የመከላከያ፣ የፖሊስና ፍትህ ተቋማት የየራሳቸው ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ ይህ የሚሆነው የፖለቲካ ስርዓቱ ሲስተካከል ነው የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡
ለ35 ዓመት በመከላከያ ሠራዊት አገልግለው ከሠራዊቱ የወጡት ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ የመከላከያ ሚኒስትር ራሱን በአዲስ አደረጃጀት (ሪፎርም) ማድረጉ ከአሁን ቀደም ተደርጎ የማይታወቅ፣ አሁን ካለው የአገሪቱ ለውጥ ጋር አብሮ መሄድ የሚችል ነው ይላሉ፡፡ አዲሱ አደረጃጀት (ሪፎርሙ) ሠራዊቱ ከማንኛውም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ እሱም በፖለቲካው ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ የሚያደርግ ነው፡፡ ሆኖም በአንድ ጀንበር የሚቀየር ባይሆንም በሂደት ለውጥ መምጣቱ አይቀርም የሚል አስተያየት አላቸው፡፡
ሌላው የአዲሱ አደረጃጀት አካል የሆነው ደንቦችና ህጎችን ማሻሻል መሆናቸውን ሌተናል ጀነራል ባጫ ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አንዱ የሠራዊቱ የዕጩ መኮንንነት ምልመላ የሚደረገው ከሠራዊቱ የበታች መኮንኖች ብቻ ነው የሚል ደንብ እንደነበረው ያስታውሳሉ፡፡ ይህ ደንብ ዘመናዊና በተማረ የሰው ኃይል የተገነባ ሠራዊት መፍጠር እንዳንችል አድርጓል፡፡ ዘመናዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ አቅምና ጥንካሬ ያለው ሠራዊት ለመፍጠር የተማረውን የሰው ኃይል ለመቅጠር የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱ ለመከላከያ ሠራዊቱም ሆነ ለአገሪቱ ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ በተለይ ብቃት ያለውና ብሄራዊ ተዋጽኦን ያመጣጠነ መኮንኖችንም ለማፍራት ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2011
ጌትነት ምህረቴ