በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ እምብዛም ነው። ለዚህም ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ጫናዎች እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ከዚህ በተለየ መልኩ የሚገጥማቸውን ፈተና በመቋቋም ያለሙትን ግብ የሚያሳኩ ትንታግ እንስቶች እዚህ እዚያም ብቅ ማለት ጀምረዋል።
ቤተሰብ፣ማህበረሰብና ሰፍቶም ሀገር በመገንባቱ ሂደት እናትነት ከማንም የላቀውን ትልቅ ድርሻ ይወስዳል።
እናት ሆኖ ልጅን አንፆ ከማሳደግ ከፍ ባለ መልኩ ለሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ እድገትና የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ድርብ ድል ነው። በሳይንስና ምርምር ረገድ የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆን ደግሞ የዘርፉን አበርክቶ ያልቃል። ሄዋንነት ልዩ ፀጋ፤ እናትነት ትልቅነት፤ መታደል፤ ሴትነት ትልቅ ክብር ነው። ሔዋንነት ልጅን አንፆና በፍቅር ኮትኩቶ አሳድጎ ለሀገር የሚተርፍ የማድረግ ትልቅ ሃላፊነት ነው።
ቤተሰብን መርቶ፤ አስተካክሎና ገርቶ ለቁም ነገር ማብቃት ነው እናትነት፤ ሴት ልጅ ቤተሰቧን ቀጥ ለጥ አድርጋ ከማስተዳደሯ ባለፈ፤ ወጣ ብላ በአደባባይ ላይ የምትሠራው ጉልህ ሥራ ተጽዕኖ ፈጣሪነትዋ ካየለ የትልቅ ትልቅነትዋን መላቅ ምስክር ይሆናል።
አዎን! ቤተሰቧን ስኬታማ ለማድረግ በምታደርገው ሩጫ ሳትደናቀፍ ወጣ ብላ በተለያየ መስክ አጋጣሚው ምቹ ሁኔታ ከፈጠረላት በአዳም ጋር ትግል ታግላና ተወዳድራ ስኬት ላይ ስትደርስ ምን ያህል ጥንካሬዋን ማሳያ መሆኑን መመልከት ያስችላል። ሴቶች የማህበረሰቡ አንቀሳቃሽ ሞተር፤ የእድገት ቀያሽ፤ ታሪክን ገንቢ፤ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚያፈሩ፤ ትውልድን የመቅረፅ ትልቁ ኃላፊነት የተጣለባቸው መሠረት ናቸው።
በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው መሳተፍ ቢችሉ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ በርግጥም ይችላሉ። ዛሬ ላይ ሀገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስክ በግል ጥረት እና ከአካባቢያቸው ባገኙት ድጋፍ አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ ያሉ እንስቶች በማፍራት ላይ ትገኛለች።
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶቻችን ውስጥ ኢትዮጵያውያት ሴት ተመራማሪና መምህራን ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በጥናትና ምርምር ዘርፍ ተጠቃሽ ውጤቶችን በማስመዘገብ ላይ ይገኛሉ። በዚህ ዘመን ሀገራት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በተቀላጠፈና በአጭር ጊዜ ለመከወን፤ ምርትና አገልግሎት ለማሳደግና ህይወትን ቀለል ለማድረግ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያም በዘርፉ የሚታየውን ለውጥ ለማስቀጠል የተሻለ ውጤት ማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎች በመሥራት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ትገኛለች። የማህበረሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶችም ለሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል። ዛሬ ላይ በመንግሥት በተደረገው ድጋፍና በእንስቶቹ የግል ጥረት ስኬቶችን በመመዝገብ ላይ ይገኛሉ።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ ያሉ እንስቶችን ከዚህ በፊት በዚሁ አምድ በተደጋጋሚ ማቅረባችን ይታወሳል። ዛሬም በዘርፉ በሀገር ደረጃ ትልቅ ተጽዕኖ መፍጠር የቻለች ብቸኛ አስትሮ ፊዚስት እንስትና ሥራዎችዋን ልናስተዋውቃችሁ ወደድን።
ዶክተር ፀጋ ብርሃነ ትባላለች። በሥራዋ ትጉህና ውጤታማ ሴት ነች። ስኬት ላይ ለመድረስ ያደረገችው ሩጫ አልጋ ባልጋ ሆኖላት፤ አላማዋን ለመሳካት ፍላጎቷ በቀላሉ ሰምሮላት አልነበረም ከመነሻዋ ጀምሮ ዛሬ ከደረሰችበት ደረጃ ላይ መገኘት የቻለችው፤ ነገር ግን፤ ምኞትና ህልሟ ስንቅ ሆኗት ነገን በመናፈቅ ያደረገችው ጥረት ዛሬ የተገኘችበት ስኬት ላይ አድርሷታል።
በጥረትና በትጋቷ የቤተሰብ ሃላፊነቷ በትክክል ከመወጣት ባሻገር ሀገራዊ ትልቅ ተልዕኮዋን በመወጣት ላይ ትገኛለች።
ዶ/ር ፀጋ ብርሃነ ተወልዳ ያደገችው በትግራይ ክልል በአድዋ ከተማ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን እዚያው አድዋ ከተማ ውስጥ በሚገኘው “ዓዲ አቤቶ” 9ኛ ክፍል ክልሉ የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ያመጡትን ተማሪዎች በማወዳደር ወጪያቸውን ሸፍኖ በሚያስተምርበት መቐለ “ቃላሚኖ ትምህርት ቤት” ተከታትላለች። ከ10ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ወደ አድዋ በድጋሚ ተመልሳ ንግስተ ሳባ መሰናዶ ትምህርት ቤት ገብታ ተከታትላለች።
የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በከፍተኛ ውጤት በማምጣት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብታ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በፊዚክስ ጨርሳለች። ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ እዚያው በመቀጠል በኒኩሌር ፊዚክስ ተመርቃለች።
ለአራት ዓመታት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት አገልግላ ሦስተኛ ዲግሪዋን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በናሳ መካከል በተፈጠረው ስምምነት በአስትሮ ፊዚክስ ትምህርቷን ተከታትላ በጥሩ ውጤት አጠናቅቃለች። የመመረቂያ ጽሁፏን በሶላር አስትሮ ፊዚክስ የሠራች ሲሆን፤ የጥናቷ ውጤት ተግባራዊ ለማድረግ እጅግ የቀለለና በዘርፉ ትልቅ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው።
በመምህርነት፤ በተመራማሪነትና በሳይንስ ዘርፍ በልዩ ልዩ ተግባሮች ተሳትፎዋ የምትታወቀው ዶክተር ፀጋ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ በፊዚክስ አስተማሪነትና ተመራማሪነት፣ በዩኒቨርሲቲው በኢንስቲትዩት ኦፍ ኢንቫይሮመንት፤ ጀንደር ኤንድ ኢንቫይሮመንት ስቴዲስ ዳይሬክተር በመሆንም አገልግላለች።
ዶክተር ፀጋ በትምህርት ህይወቷ ብዙ ፈተናዎችን የተጋፈጠች መሆንዋን ትናገራለች። በተለይም፤ በትምህርት ቤት ቆይታዋ ማህበረሰቡ ከትምህርት ይልቅ ትዳር ይዛ ልጆች እንድትወልድ የአካባቢው ማህበረሰብ ጫና ይበዛባት እንደነበረና በተደጋጋሚ ከቤተሰብ ተለይቶ ለመኖር አቅዳ እንደነበርም ከትውስታዎችዋ መሀል ማሳያ የሚሆኑ ገጠመኞችዋን ትናገራለች።
በትምህርት ቤት ደረጃ ሴት ተማሪዎች ብዙም ባልነበሩበት በዚያ ወቅት ውድድር ታደርግ የነበረው ከወንዶች ጋር እንደነበር ትናገራለች። በዛን ጊዜ እንደ አሁኑ ለሴቶች የተለየ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ያለተለመደ፤ ለስኬታቸው ስምረት ልዩ ድጋፍ ማድረግ የማይዘወተር ተግባር ነበር።
በወቅቱ በሴትነት የሚደርሱ የተለያዩ የማህበረሰቡ ጫናዎች ከወንዶች እኩል በትምህርትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሴቶች ተሳትፎ እንዳያደርጉ ያግዳቸው እንደነበር ዶክተር ፀጋ ትናገራለች። እነዚህን መሰናክሎች ተጋፍጣ የሚገጥማት መጦፎ ገጠመኞች አጠንክረዋት ፈተናዎቹ አበርትተዋት ዛሬ ለደረሰችበት ትልቅ ደረጃ በቅታለች።
ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ ከፍተኛ ውጤት አምጥታ እንደነበር የምትናገረው ተመራማሪዋ መምህርት ዶክተር ፀጋ፤ ካሉት የትምህርት መስኮች ፊዚክስ የመረጠቸው በሳይንስና ምርምር መስክ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ያለመችውን ህልሟን ለማሳካት ነበር። “በወቅቱ የትምህርት ክፍሉን የተቀላቀልኩት ብቸኛ ሴት እኔ ነበርኩ” የምትለው ዶክተር ፀጋ ‘ሴት ልጅ የወንድን ያህል አቅም የላትም’ ከሚለው የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ ተማሪዎች ‘እንዴት ፊዚክስ ትመርጣለች?’ በማለት እንደ ስህተተኛ አድርገው በመመልከት ይጠቋቆሙብኝ ነበር በማለት ገጠመኞችዋን ትዘረዝራለች።
“ማህበረሰባዊ አመለካከቱን ለመለወጥ አሁንም ቢሆን ብዙ መሠራት ይኖርበታል” የምትለው ዶክተር ፀጋ፤ በተለይም ሴቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ጎልተው እንዳይታዩና ተሳትፏቸው እንዲቀንስ ያደረገው ዋነኛ ምክንያት ይሄ እንደሆነ ትናገራለች። “ጥናትና ምርመር ፆታ አይለይም” የምትለው መምህርና ተመራማሪዋ ፤ ሳይንስ አላማው የህብረተሰቡ ችግር መፍታት እስከሆነ ድረስ ሴቱም ወንዱም በዚህ ሥራ እኩል ተሳትፎ ማድረግ የሚኖርበት መሆኑን ታስረዳለች።
በተለይም፤ “ሴቶች በመስኩ ትልቅ ተሳትፎ ማድረግ ይገባቸዋል” የምትልው ዶክተር ፀጋ፤ ለዚህም ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው ይገባል። የምርምር ሥራ በባህሪው የተረጋጋ ህይወትና ጊዜ የሚፈልግ መሆኑና ለዚህም ብዙ መሥራት የሚገባ መሆኑን ትገልፃለች። ሴቶች በሳይንስና በምርምሩ መስክ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው በግል ከጣሩና ለጥረታቸው ዋጋ የሚከፍል አጋጣሚ ከተመቻቸላቸው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉም ትነገራለች።
ሴቶች ስኬታማ እንዳይሆኑ የሚያደርጋቸው ብዙ ምክንያት መኖሩን የምትዘረዝረው ዶክተር ፀጋ፤ እነዚህን ችግሮች በመቋቋም ለህልማቸው እውን መሆን የግል ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ትጠቁማለች። “አንዱ ለአንዱ አለመሳካት ምክንያት መሆን የለበትም። ወጣት ሴቶቻችን በየትኛውም ነገር መሆን የፈለጉትን መሆን እንደሚችሉ ማመን አለባቸው።” በማለትም ምክራቸውን ይለግሳሉ።
የዶክተር ፀጋ ሀሳብና የወደፊት ህልም እጅግ የገዘፈና ብዙ፤ መድረሻውም ትልቅ ነው። “ኢትዮጵያ ሮኬት ማምጠቅ በምትጀምርበት ጊዜ እኔም የዚያው አካል እና ዋና ተሳታፊ መሆን እፈልጋለሁ” ትላለች። ለዚህም “ሮኬት ማምጠቅ ተግባር በሙያዬ የሚያስፈልገውን ሚና መጫወትና የሀገሬን ህልም ሲሳካ ማየት የሚያስደስተኝ ዋነኛ ጉዳይ ነው” በማለት ለሀገርዋ ያላትን ጥልቅ ፍቅር ትገልፃለች።
ለሮኬት ማምጠቅ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎችን በመሥራት፣ ሮኬቱን ለማምጠቅ የሚረዳ ንድፈ ሀሳብ በማዘጋጀት፣ ለዚያ ግብዓት የሚሆኑ ጉዳዮችን በመለየት፣ ሀገራዊ ጠቀሜታን የሚያጎላ ሥራ ለመሥራት በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ወደፊት ለሚሠሩ ሠራዎች ሰፊ ዝግጅት በማድረግ ላይ የምትገኘው መምህርና ተመራማሪዋ ዶክተር ፀጋ፤ “ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር አብረን መሥራት እንፈልጋለን። አሁን ያዘጋጀናቸው የጥናትና የምርምር ፕሮፖዛሎች አሉን” በማለት የዘርፉ ዋንኛ ተዋናይ ከሆነው ተቋም ጋር የመሥራቱ ፍላጎት እንዳላት ትገልፃለች። ለምርምርና ለጥናት የሚሆኑ የተለያዩ ንድፈ ሀሳቦች ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እደምታቀርብም ትናገራለች።
እነዚህ እና የመሳሰሉ ትልልቅ ሐሳቦችን ወደፊት ወደ ተግባር ለመለወጥና ለመሥራት ሌት ተቀን በትጋት በመታተር ላይ ትገኛለች። አሁን ላይ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ መሆን ቁጭት እንደሚፈጥርባት የምትገልፀው ዶክተር ፀጋ፤ ሴቶችን በበቂ ሁኔታ ያላሳተፈ መስክ ስኬታማነቱ የሚያጠራጥር ነውና በትኩረት ሊጤን የሚገባ መሆኑን ትናገራለች።
“ለሴቶች ዘርፈ ብዙ ተሳታፊነት ልዩ ትኩረት ያስፈልጋል” የምትለው ተመራማሪና መምህር ዶክተር ፀጋ፤ “ሴትን ሳንይዝ እድገት እናመጣለን ብሎ ማሰብ የማይቻል ነገር ነው። ይህንን በማመንም የሚመለከታቸው አካላትም ሆነ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ መቀጠል አለበት” በማለት ዋነኛ ያለችውን መልዕክቷን አስተላልፋለች።
አበቃን ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን መስከረም 2/2011
ተገኝ ብሩ