በተወለደችባት ምድር ይህን መሰል ስቃይ እቀበላለሁ የሚል እምነት አልነበራትም፡፡ እንደ ዕድሜ እኩዮቿ ቦርቃ የማደግ ህልሟ በአጭሩ ይቀጠፋል ብላም አስባ አታውቅም፡፡ የሆነው ግን እንዲህ ነው፡፡ በገዛ ቤተሰቦቿና ዘመዶቿ ክፉኛ ተቀጣች፡፡ በለጋ ዕድሜዋ የስለት ሰለባ ሆነች-ሌይላ ሁሴን፡፡
ሌይላ ሁሴን በሶማሊያ ምድር ለዘመናት እንደ በጎ ሲታይ የነበረውን የሴት ልጅ ግርዛት ሳትወድ በግዷ ለመቀበል ተገድዳለች፡፡ እንክብካቤ የሚሻው የህፃን ሰውነትዋ በዘመዶቿና በቤተሰቦችዋ ፍላጎት በቢላዋ ተተለተለ፡፡ ይህን ተከትሎም ከፍተኛ ህመምና ስቃይ ማስተናገድ ዕጣ ፈንታዋ ሆነ፡፡ ስቃይን ተሸክማ ከማደግዋ በተጨማሪ ባል ስታገባ ደግሞ ስቃይዋ ይባስ በረታባት፡፡ መውለድ መሳም ቢያምራትም የግርዛቱ ክፉ ጠባሳ ለስቃይ እንጂ ለፍላጎቷ ማሟያ የሚሆን አልሆነም፡፡
የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቆም በዚህ ዙሪያ የሚንቀሳቀስ ‹‹ዶሂላ ፕሮጀክት›› የሚል ድርጅት በመክፈት ፀረ ሴት ልጅ ግርዛት ዘመቻ ጀምራለች፡፡ በዚህም የራሷን ተሞክሮ ለሌሎች በማስተማር ዓለም የሴት ልጅ ግርዛትን እንዲከላከል ብርቱ ትግል እያደረገች ትገኛለች፡፡ በርካታ ተከታዮችም ማፍራት ችላለች፡፡
በየመድረኮቹ ‹‹ መገረዜ ከምወድደውና ከማፈቅረው ሰው ጋር ወሲብ እንዳልፈፅም፤ ልጅ እንዳልወልድ፤ ደስተኛ ህይወት እንዳልኖር ትልቅ እንቅፋት ሆኖብኛል፡፡ በልጅነቴ ያሳለፍኩት መከራ ያተረፈልኝ ስቃይ ሳይበቃኝ አሁንም ስነ ልቦናዊ ጫና አሳድሮብኛል፡፡ በእኔ ላይ የደረሰው በደልና ግፍ በሌሎች ላይ እንዳይደርስ እታገላለሁ፤ እናንተም አግዙኝ›› በማለት ሁሉም የሴትን ልጅ ግርዛትን ለመከላከል ዘብ እንዲቆም ትሞግታለች፡፡
እንደ ሌይላ ሁሉ በርካታ ሴቶች በገዛ ቤተሰባቸው ለስቃይ ተዳርገዋል፤ ይዳረጋሉም፡፡ ይህ ደግሞ በህፃናት ላይ የሚፈፀም የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በ30 አገራት ብቻ በዓመት 200 ሚሊዮን ያህል ሴቶች ይገረዛሉ፡፡ ችግሩ በተለይ በአፍሪካ ጎልቶ ይታያል፡፡ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንግዲህ በእነዚህ አገራት የሚኖሩ ህፃናት ሴቶች ናቸው፡፡
ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ህገ ወጥ ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ መብት ጥሰትም አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ ሊከበሩላቸው የሚገቡ መብቶች በሰዎች ፍላጎት ከተጣሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን ድንጋጌዎቹ ያስገነዝባሉ፡፡ እናም ጉዳትን የሚያስከትሉ ድርጊቶች በሰዎች ላይ ከቶውንም ሊፈፀሙ አይገባም፡፡
በተለያዩ የዓለም አገራት የሚንቀሳቀሰው አፍሪካ ሁማኒታሪያን አክሽን የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ዓለም ዓቀፍ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመንግሥትና በህብረተሰቡ እንደሚፈፀሙ ያትታል፡፡ በህብረተሰቡ ከሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መካከል ደግሞ ያለ ዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሌይላን ሃሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡
መንግሥት በፖለቲካ ሰበብና ሽፋን ዜጎችን ለእስርና ለእንግልት እንደሚዳርጋቸው ሁሉ ህብረተሰቡም በባህል ሰበብ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈፅማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የህፃናት ጉልበት ብዝበዛና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርም የጥሰቱ ተጨማሪ መገለጫዎች ናቸው፡፡
እናም ችግሩን በመከላከሉ ሂደት ህብረተሰቡ የጎላ ሚና መጫወት አለበት፡፡ ‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፀመ›› እያለ የሚጮህ ማህበረሰብ እጁን ከጥፋቱ መሰብሰብ ይኖርበታል፡፡ ርምጃው ታዲያ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ አካላትን ለህግ በማቅረብ የበኩሉን ሚና የመጫወት ግዴታም አለበት፡፡
የዓለም የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ የፀደቀበት 70ኛ ዓመት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተከብሯል፡፡ እ.አ.አ ታህሳስ 10 ቀን 1948 የፀደቀው ሰነድ ሁሉም ሰዎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ይደነግጋል፡፡ የዓለም አገራትም ለድንጋጌው ተፈፃሚነት ቃል በመግባት ስምምነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ድንጋጌውንም በአገራቸው ህግ ውስጥ በማካተት ወደ ተግባር ገብተዋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ከፀደቁ ሰባት አስርት ዓመታት ቢያስቆጥሩም የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ግን በሁሉም አካባቢዎች ከመሻሻል ይልቅ ብሶበታል፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥታት ለጉዳዩ የሚፈለገውን ያህል ትኩረት ባለመስጠታቸው የተነሳ እንደሆነ ነው የሚነገረው፤ አንዳንድ መንግሥታት የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ በመንግሥት ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ ዜጎች ይታሰራሉ፣ ይሰደዳሉ፡፡ በዚህ ረገድ የአፍሪካ መንግሥታት በቀዳሚው ደረጃ ይቀመጣሉ፡፡ ስልጣንን በዘር የመያዝ አባዜ የተጠናወታቸው የዓረብ አገራት ደግሞ ከአፍሪካውያኑ የባሱ የስልጣን ጥመኞች መሆናቸው ነው የሚስተዋለው፤ በእነዚህ አገራት በርካታ አፋኝ ህጎች በመኖራቸው የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች በስፋት እንዲጣሱ እያደረጉ ነው፡፡
ሶርያንና የመንን በመሳሰሉት አገራት ማባሪያ ያጣው ግጭት ዜጎችን ለተለያዩ ችግሮች ዳርጓል፡፡ ንፁኃን ዜጎች ከአካባቢያቸው እንዲፈናቀሉ፤ እንዲሰደዱ፤ ለርሃብና ለውሃ ጥም እንዲዳረጉ አድርገዋል፡፡ የመን በግጭት ሳቢያ በ50 ዓመት ታሪክ ከአጠቃይ ህዝቧ 70 በመቶ የሚሆኑት ለአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ ድጋፍ መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡ በሶርያ ደግሞ 11 ሚሊዮን ህዝብ ለመፈናቀል፤ 11 ሚሊዮን ለተለያዩ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ሲዳረጉ፤ ከ300ሺ የሚበልጡት ደግሞ አልቀዋል፡፡
ከሶርያና ከየመን በተጨማሪ በተለያዩ አገራት የሚከሰቱ ግጭቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እንዲከፋ ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ በአገር ውስጥ ያለውን ግጭት በመሸሽ ስደትን ምርጫቸው ያደረጉ ሰዎች በየመንገዳቸው ለተለያዩ አሰቃቂ ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡ ብዙዎቹ የሰውነት ክፍላቸው ይወሰዳል፤ ሴቶች ይደፈራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሊሆን የማይጠበቅ የባሪያ ንግድ ተስተውሏል፡፡ በአፍሪካዊቷ አገር ሊቢያ የባሪያ ንግድ በገሃድ መታየቱ ዓለምን ያስገረመና ያስደነገጠ ድርጊት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ እነዚህና መሰል ህገ ወጥ ድርጊቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እየባሰበት መምጣቱን የሚያመላክቱ እንደሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
በኢትዮጵያም ቢሆን ባለፉት ዓመታት እጅግ ዘግናኝ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን መንግሥት አስታውቋል፡፡ በእነዚህ ድርጊቶች ላይ የተሳተፉ አካላትን ለህግ የማቅረብ ዕርምጃ ውስጥም ተገብቷል፡፡ እነኝህን መሰል ዕርምጃዎች በሁሉም አካባቢዎች ሊተገበሩ እንደሚገባ ብዙዎች ሃሳብ ይሰጣሉ፡፡ ለሰብዓዊ መብት ዘብ የመቆም ዕርምጃው በተግባር መታየት አለበት፡፡
ለሰብዓዊ መብት መጣስ የተለያዩ ምክንያት መኖራቸው ግልፅ ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ በመንግሥ ታትና በህብረተሰቡ የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ ችግሩን ለማስቆም ታዲያ አንዱ በሌላኛው ላይ ጣት መጠቆሙ ውጤት አያመጣም፡፡ ይልቁንም፤ ዘላቂ መፍትሔ የሚመጣው ሁሉም ራሱን ሲመለከት ነው፡፡ ህብረተሰቡ በባህል ሰበብ በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚያደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማቆም አለበት፡፡
ቤተሰብ ልጆቹን ለተሻለ ገቢ ፍለጋ በሚል ወደውጭ አገራት እንዲሰደዱ የሚያደርገውን ጥረት መግታት ይኖርበታል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሀሳብ ባይቆም እንኳን በህጋዊ መንገድ እንዲሄዱ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ አገራት ለማስተላለፍ የሚሯሯጡ ግለሰቦችም ካልተገባው ድርጊታቸው መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡ ህፃናትን ያለ ዕድሜያቸው በተለያዩ ሥራዎች በማሰማራት የጉልበት ብዝበዛን የሚያበረታቱ አካላትም ከተሳሳተው ጎዳና መውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
መንግሥታትም በገቡት ቃል መሰረት ለሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መከበርና መተግበር የሚጠበቅባቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ድንጋጌዎቹ ያስቆጠሩትን ዕድሜ ያህል አለመተግበራቸው ሊያስቆጭ ይገባል፡፡ ስለሆነም፤ ሰብዓዊ መብት ለሁሉም መከበር እንዳለበት ሁሉ ለመብቱ መከበርም ሁሉም ወገን ኃላፊነት አለበት፡፡ እናም ህብረተሰቡም፤ መንግሥትም ኃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉም ለሰብዓዊ መብት መከበር ዘብ መቆም ይጠበቅበታል፡፡
ሰብዓዊ መብት እንዲከበር በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ አገር ዓቀፍና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት በስፋት መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ አካላት በመንግሥታት ብዙም ትኩረት የማይሰጣቸውና የማይበረታቱ መሆናቸው ብዙውን ጊዜ ይነገራል፡፡ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱት ሂውማን ራይትስ ዎችና አመንስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ ተቋማት በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ትግል እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን መንግሥታት በተለይም የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም የሚጥሩት አይፈልጓቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ውስጣዊ ችግራቸውንና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉድፋቸውን እንዳያሳዩባቸው በመፍራት ነው፡፡ ይህ ዕርምጃቸው ለጊዜው እፎይታ የሰጣቸው ቢመስልም አጋዥ እንዳያገኙ ማድረጉ ግን አልቀረም፡፡
ምክንያቱም በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አቅም ስላላቸው መረጃዎችን ለመንግሥታት በማድረስ የመፍትሔ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ለማድረግ ያግዛሉ፡፡ እናም እነዚህን ድርጅቶች እንደ አጋዥ አካል የመጠቀም ባህልን ማዳበር ይገባል፡፡ ዘንድሮ የተከበረውን 70ኛ ዓመት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ የተከበረበትን ቀን በማስመልከት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ የአሁኑ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ መድረክም የተንፀባረቀው ይሄው ነው፡፡ መንግሥታት የሚያግዟቸውን አካላት ከማቅረብ ይልቅ መግፋትና ማሳደድ ይመርጣሉ፡፡ በኢትዮጵያም ባለፉት ዓመታት የነበረው ይሄው ነው፡፡
ይህን መሰሉ የመገፋፋት አባዜ ከቀረ ሰብዓዊ መብትን ለማክበርም ሆነ ለማስከበር የሚደረገው ጥረት ፍሬ ያፈራል፡፡ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው የሌሎች መብቶች እንዲከበሩ የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ፤ ቀደም ሲል እንደ መልካም ባህል ተይዘው የነበሩና ጎጂነታቸው የከፉ ልማዶች እንዲቀሩ ህብረተሰቡን ማስተማርና ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ የሃይማኖት አባቶች፣ የገር ሽማግሌዎችና ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
በኢትዮጵያም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋማት ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ እነዚህ ተቋማት ሰብዓዊ መብትን ለማስከበርና የዲሞክራሲ ግንባታውን ለማጠናከር ቢቋቋሙም በተግባር የታየው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው
የሚሉ በርካታ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ተቋማቱ ችግሮችን ከመከላከልና የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወሰድ ከመስራት ይልቅ ችግሮችን በመሸፋፈን ሥራ ላይ ተጠምደው ቆይተዋል ተብለው በብዙዎች ዘንድ ይተቻሉ፡፡
በዚህም ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ እንዳይወጣ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ ነው የሚነገረው፤
አሁን ጊዜው ሁሉም ሰብዓዊ መብቱ ተከብሮለት የሚንቀሳቀስበት፤ ሁሉም ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚጠበቅበትን የሚወጣበት ነው፡፡ ለዚህ ዕውንነት የነቃ ተሳትፎና ጥረት ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል፡፡ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ወደ መሬት ወርደው ይታዩ! የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ከማነብነብና ቀኑን ብቻ ጠብቆ ከማክበር የዘለለ ውጤት ለማስመዝገብ ይሰራ! ሁሉም ለሰብዓዊ መብት መጠበቅና መከበር ዘብ መቆም ይኖርበታል!!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2011
ሠላም ዘአማን