ማምሻውን ችቦ ሲያበሩ ሲጨፍሩ ያመሹት የመንደሩ ሰዎች አሮጌውን ዓመት ዳግም ላይመለስ እየሸኙት ነበር። እዮሀ አበባዬ መስከረም ጠባዬ እያሉ። ያ ድቅድቅ የጨለማው ወር ክረምቱ፣ ዶፍ ዝናቡ ጎርፉ ውሃ ሙላቱ አለፈ። እነሆ ብራው መስከረም ጠባ። አዲስ ዘመን ገባ ። ደስ ይበለን ደስ ይበላችሁ ነው የጭፈራው መልእክት።
ደስታና ፈንጠዝያ ችቦ ማብራቱ፣ ሁካታው፣ ጫጫታው፣ ጭፈራው፣ እዚህም እዚያም እንደ ደመራው ችቦ ተቀጣጥሎአል። ርችቱ ወደ ሰማይ ይለኮሳል። ይኖጋል። እዚህም እዚያም ባሻገር ማዶም እልልታው ይቀልጣል። ሆ በል!! ሆ በል!! እዮሀ አበባዬ መስከረም ጠባዬ እያለ ያስገመግማል። እንቁጣጣሽ የኢትዮጵያዊነት ታላቅ መገለጫ ነው። የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ። እንኳን ሁላችንንም ከቁጥር ሳያጎድል ለአዲሱ አመት አደረሰን መጪው ጊዜ የሠላም የፍቅር የብልጽግና ዓመት ይሁንልን የሚል ብርቱ ምኞት ይስተጋባል።
ድፍን ሀገር በዋዜማው እዮሀ አበባዬ እያለ የሚዘፍነው ዘፈንና ጭፈራ ሆታው መንደር ከመንደር ጎራ ከጎራ ያስተጋባል። በየቦታው የደመራው ችቦ ጭስ ይትጎለጎላል። ምሽቱን እንደየባሕሉ ጭፈራው ይቀልጣል። ጠላው አረቄው ይጠጣል ይጨፈራል። ዛሬ ዛሬ ከተሜውና ዘመናዩ ተወው እንጂ በሀገር ባሕል ልብስ አባቶች እናቶች ጎረምሳው ልጃገረዱ ሕጻናቱ ደምቀውና አሸብርቀው በዋዜማው በተደመረው ደመራ ዙሪያ ሁነው ሆ በል !! ሲሉ ባሕላዊ ጭፈራቸውን ሲጨፍሩ ለፈጣሪያቸው ምስጋናቸውን ሲያቀርቡ ያመሻሉ። ኢትዮጵያ—-ኢትዮጵያ !! አቻም የለሽ ኢትዮጵያ !!
አባባ አቻምየለህና ወ/ሮ ጫልቱ ጎረቤታቸው ወ/ሮ ባፈና አቶ እንዳሻውና ሌሎችም የግቢው ጎረምሳና ሕጻናት ጭምር አዲሱ ዘመን የሰላም የፍቅር የጤና እንዲሆን በመመኘት በደመራው ዙሪያ ታድመዋል። አዲሱን ዓመት ባለው ማክበር በደስታ መቀበል ድሮም የነበረ ባሕላችን ነው አሉ አቶ አቻምየለህ።
ወ/ሮ ጫልቱ ወ/ሮ ባፈናም አዎን አዎን አሉ። ጎረቤቶቹም ተቀበሉ። አቶ እንዳሻው የሚነጋውን እንቁጣጣሽ እያሰበ ይመስላል በደስታ ዜማ እያወረደ ይጨፍራል። ምነው ባለፈው ኑሮ ተወዶዷል ዓመት በዓሉ ይቀየር ብለህ አልነበረም ወይ አሉት ጎረቤቶቹ። ኑሮው ተወደደም ረከሰም የእኔ ዓመትባሎች እናንተ ናችሁ፤ እምዬ እናንተን አያሳጣኝ አላቸው።
መልሱ አንጀት ያላውሳል። አይዞህ እኛ እያለን አሉት ሁሉም። እውነት ብለሃል እንዳሻው መቼም እንደው እንደ ድሮው ማክበር ባይቻልም ፈጣሪን አመስግኖ እንደ አቅም መዋል ይቻላል። ዋናው ነገር ሀገር ሰላም ሕዝቡ ሰላም ሲሆን ነው ዓመት በዓሉም የሚያምረው የሚደምቀው። ሀገራችንን ሰላም አማን ያድርግልን አሉ አቶ አቻምየለህ።
ወ/ሮ ጫልቱ ቀጠሉና ሆሆይ ከሀገር ሰላም በላይ ምን ይኖራል ? በማን ላይ ሆነሽ ማንን ታሚያለሽ አሉ። ብናጣ ብናገኝ ቢከፋን ብንደሰት የሁሉ ገመና ከታች እምዬ ኢትዮጵያ ሀገራችን ነች። እሷን ክፉ አይንካብን አሉ። ባፈና ቀጠሉና እናንተዬ ሀገር ስላለን ነው እኮ እንደ ባሕላችን እንደ ጥንቱ እንደ ጠዋቱ እንደ አያት ቅድመ አያቶቻችን እንደ አባት እናቶቻችን እኛም ዛሬ ሰብሰብ ብለን የበዓሉን ዋዜማ የምናከብረው።
አዲሱን ዓመት በጋራ የምንቀበለው። ሀገር ከደፈረሰ ሰላም ከሌለ እንኳን በዓል ምንም አይኖርም። ሀገራችንን ልጆቻችንን ሕዝቡን ፈጣሪ ይጠብቅልን። አዲሱ ዓመት የሰላም የፍቅር የጤና የሀገር ሰላም ዓመት ይሁንልን ሲሉ ወ/ሮ ባፈና በችቦ ማብራት ሥነ ሥርዓት ላይ ለተሰበሰበው ጎረቤት በሙሉ ምርቃት ሰጡ። ሁሉም በሚያስተጋባ ድምጽ አሜን! ኧረ አሜን! አሉ። አሁንም አሜን አሜን !! ደመራው ተበትኖ ሁሉም ወደየቤቱ ገባ። አዲሱን ዓመት ለመቀበል የሌሊቱን ማብቃትና መንጋት በተስፋ ሊጠባበቅ።
ሁሉም በየቤቱ እንደ አቅሙ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ሲዘጋጅ ከርሟል። እነሆ መንጋቱ አይቀሬ ሆኖ ነጋ። ዕለተ ሐሙስ መስከረም 1/2012። የአዲሱ አመት መጀመሪያ። የዶሮው፣ የበጉ፣ የበሬ ቅርጫው እርድ በስፋት ቀጥሏል። በየቤቱ ቄጠማው ተጎዝጉዞ ረከቦቱ ቀርቦ ቡናው ሲፈላ ዳቦው ሲቆረስ የእጣኑ ጭስ ሲትጎለጎል ፈንዲሻው በተን በተን ሲደረግ በቤትም በጎረቤት ያለውም እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ ሲባባል ልዩ ስሜት ይፈጥራል። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዬ ማን እንዳንቺ?
ሕጻናት ሴት ልጆች ማልደው በመነሳት ‹‹እዮሀ አበባዬ›› እያሉ የእንቁጣጣሽን ዘፈን እየዘፈኑ በየቤቱ ሲዞሩ ስጦታ ሲሰጣቸው፤ አባወራና እማወራ ከልጆቻቸው ጋር ቤቱን ሲያደምቁት፤ ጎረቤት ዘመድ አዝማድ ተጠራርቶ በአብሮነት ቤት ያፈራውን ተካፍሎ በልቶ ጠጥቶ መዋል ጥንት ጠዋት የነበረ የእኛና የእኛ ብቻ የሆነ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የማንነታችን ማሳያ ዘመናትን የተሻገረ ባህላችን ነው። ሀገሬ እምዬ ሀገሬ እንዲሉ።
አቶ አቻምየለህና ወ/ሮ ጫልቱ እንዲሁም ወ/ሮ ባፈናና ሌሎችም ቤተሰቦች ቤት በዕለቱ ያገቡ የተዳሩ ልጆቻቸው እንኳን አደረሳችሁ ለማለት በዓሉንም ከቤተሰቦቻቸው ጋር አብረው ለመዋል አቅማቸው የፈቀደውን ስጦታ በመያዝ ልጆቻቸውን አስከትለው እንደሚመጡ አውቀው ይጠብቃሉ። እውነትም የአቶ አቻምየለህና የወ/ሮ ጫልቱ ልጆች ቀድመው ደረሱ። አዛውንቶቹ በደስታ ፈንድቀው ተቀበሏቸው። እንዳሻው ትናንት ተልኮ የገዛውን በግ በጠዋት አርዷል። እንግዶችንና ጎረቤቶችን ለመቀበል። ተሰርቶ ገበታው ተሰናድቶ አባትና እናት መሀል ልጆችና የልጅ ልጆች ዙሪያውን ከበው ተቀምጠዋል። አቶ አቻምየለህና ወ/ሮ ጫልቱ በሀገር ባሕል ልብስ አምረዋል። ደምቀዋል።
አቶ አቻምየለህ በቀኝ እጃቸው የያዙትን ጭራ እየነሰነሱ መናገር ጀመሩ። አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ ለዛሬው አዲስ ዓመት ያደረሰን አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤ አዲሱ አመት በአራቱም ማዕዘን የሀገር ሰላም የቤተሰብ ሰላም የሰፈነበት የፍቅር የጤና የበረከትና የረድኤት ዓመት ፈጣሪ ያድርግልን። ከሁሉም በላይ ሁሉም ነገር በሀገር ያምራል ይደምቃልና ሀገራችንን ከክፉ ሁሉ ይጠብቅልን። ሰላም አማን ያድርግልን ሲሉ ቤተሰቡ አሜን አሜን ይል ገባ።
የጥንቶቹ የአባቶቻችን የእናቶቻችን አምላክ ሀገራችንን ይጠብቅ፤ የተወለዱት ይደጉ፤ አዝመራው ጥጋብ ይሁን። የሀገር ምሰሶ የሆነውን ገበሬውን ከሞፈርና ቀንበሩ፤ የሀገር ጠባቂ የሆነውንም ወታደር በያለበት ሕዝባችንንም በሙሉ በያለበት ይጠብቅልን። ልጆቼ እድሜና ጤና ይስጣችሁ። ከክፉ ሁሉ ይጠብቃችሁ። ከነቤተሰቡ ከነጎረቤታችን አቅፎ ደግፎ የከርሞ ሰው ይበለን ሲሉ ሁሉም ቆሞ ምርቃቱን አሜን! አሜን! በማለት ተቀበለ። አሁንም ኧረ አሜን አሜን !!
የአቶ አቻምየለህ ልጆቻቸው አንዱ በሕክምና ሙያ አንዱ በውትድርና ሌላው በንግድ ሌሎች ሶስት ደግሞ አሜሪካ ካናዳና ጀርመን የሚኖሩ ናቸው። እነሱም በዕለቱ ደውለው አባት እናታቸውን እህት ወንድሞቻቸውን ወዳጅ ዘመዱን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል። ኑሮው ቢወደድም ተመስገን ለልጆቼ እድሜና ጤና ስጥልኝ ፈጣሪ አሉ ጫልቱ። ባፈናም እውነት ነው ሲሉ ደገሙ።
ይህ አባባል የሁሉም ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች አባባል መሆኑን ልብ ይሏል። እንደው በዚህ በጨሰ የኑሮ ውድነት በየውጭ ሀገሩ ያሉ ልጆች ባይኖሩን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር አሉ ሁሉም። ደገሙና የትም ቢሆን የት ያሉትን ልጆቻችንን እድሜ ጤና እንጀራ ይስጥልን። ክፉአቸውን አያሣየን አሉ። ሁሉም ምርቃቱን በአሜን ተቀበሉ። አሜን አሜን !!
አዎና ከድቅድቅ የክረምቱ ጨለማ ወደ ብርሃን የማሸጋገሩ በጋው እንዲነጋ የማድረጉ ስልጣን የሰው ሳይሆን የፈጣሪ ነው። አያቶች አባቶች እናቶች ይመርቃሉ።ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት እንዲሉ ከቡሄ በኋላ ጳጉሚትን ሸኝቶ አጅሬ መስከረም ከተፍ ይላል። የወራቶች አውራው መስከረም። የሰው ልጅ ሁሉ አምናን አልፎ አምናንም ረስቶ አዲስ ተስፋ አዲስ ሕይወት በመመኘት ኣመቱን የሚጀምርበት ወር ነው መስከረም።
ጋራ ሸንተረሩ ካባ የደፋ ይመስል በአረንጓዴ ልምላሜ ተሞልቶ መንፈስን ያስረቀርቃል። በመስከረም ብቻ በዓመት አንዴ በኢትዮጵያ ምድር የሚፈነጥቀው የእንቁጣጣሽ አበባ ፈክቶና ደምቆ የሚታይበት፤ የመስከረም ወፍ ተደብቃ ከከረመችበት ወጥታ እነሆ በልዩ ድምጿ መስከረም ጠባ የምትልበት ነው። እንደ አባቶቻችን እናቶቻችን ምርቃት ዘመኑ ሀገራችን ሰላም የምትሆንበት፤ ፍቅር መደማመጥና መቻቻል የሚሰፍንበት ፤ጥላቻና መናቆር የሚወገድበት የበረከት የረድኤት ዘመን ይሁንልን!! አሜን በሉ አሜን !! አሜን!!
አዲስ ዘመን መስከረም 1 /2012
ወንድወሰን መኮንን