የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚካሄደው የ30 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በሳምንቱ መጨረሻ ለ5ኛ ጊዜ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።ቻይናውያንን ጨምሮ በርካታ አትሌቶች በተካፈሉበት በዚህ ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ብርቱ ፉክክር ታይቶበታል።በሆራና ባቦጋያ ሃይቅ ዙሪያ መለስ የከተማዋን የተለያዩ ቦታዎች እያቋረጠ በተካሄደው በዚህ ውድድር ገና በማለዳ በከተማዋ ዋና አውራ ጎዳናዎች የተገኘው ታዳሚ ታጅቦ ቢሾፍቱን ይበልጡኑ አድምቋታል።
የነፍስ ሃሴት የሆኑ ሀይቆችና ማራኪ ተፈጥሮ የተቸረችው ከተማዋ በአስደማሚ ድባብ ታጅቦ የተካሄደው ውድድር የተጀመረው በሴቶች መካከል በተካሄደ ውድድር ነው። በፉክክር ደረጃ እንብዛም ጠንካራ ሆኖ ባልታየበት በዚህ ውድድርም በውጤቱ አትሌት ሮዛ ደረጄ ቀዳሚ ሆናበታለች።
የፌዴራል ማረሚያዋ አትሌት ውድድሩን ከፊት በመምራት ለማጠናቀቅ የወሰደባት ጊዜም 1:46.33 ሆኖ ተመዘግቧል።ኦሮሚያ ማረሚያ ቤቶች አትሌቷ ታደለች በቀለ 1:46.44 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ስትሆን፣ ዝናሽ መኮንን ሶስተኛ ሆና አጠናቃለች።የኦሮሚያ ፖሊሷ አትሌት ዝናሽ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የወሰደባት ጊዜም 1:46.53 ሆኗል።
ከሴቶቹ ውድድር በላቀ ብርቱ ፉክክር በታየበት በወንዶች መካከል የተካሄደው 30 ኪሜ ጎዳና ሩጫ ነው። በፍልሚያውም በአትሌት ፅዳት አበጀው አሸናፊነት ተጠናቋል።1:31.56 የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አትሌት ውድድሩን የጨረሰበት ሰዓት ሆኗል።ፅዳትን በመከተል ሁለተኛ ሆኖ የገባው የኦሮሚያ ክልል አትሌት ጅግሳ ታደሰ ሲሆን የገባባት ሰዓትም 1:32.06 ሆኖ ተመዝግቧል። የፌዴራል ፖሊሱ ፍቅረ በቀለ 1:32.09 ሰዓት ሶስተኛ ሆኖ ገብቷል።
አምስተኛውን የጎዳና ሩጫ ካደመቁት ውድድሮች ሌላኛው ደግሞ በአንጋፋ አትሌቶች መካከል የተካሄደው ነው። ከሃምሳ ዓመት በላይና በታች በሚል ተከፍሎ የተካሄደው ይህ ውድድር የበርካታ ታዳሚያንን ቀልብ ስቧል።በውጤቱም ከ50 ዓመት በላይ አያሌው እንዳለ አንደኛ ሆኖ አጠናቋል።ካሱ መርጊያ ሁለተኛ ሲሆን ተስፋዬ ጉታ ሶስተኛ ሆኗል።ከ50 አመት በታች ውድድር ደግሞ፤ገዛኸኝ ገብሬ፤ ዳንኤል ቄቤሎ እና ንጋቱ አጋ አንደ ቅድም ተከተላቸው ከአንድ እስከ ሶስት ጨርሰዋል።
በሴቶች የቡድን አሸናፊዎች ኦሮሚያ ፖሊስ በ27 ነጥብ አንደኛ ሆኗል።ፌዴራል ፖሊስ በ52 ነጥብ ሁለተኛ ሲሆንኦሮሚያ ማረሚያ በ57 ነጥብ ሶስተኛ ሆኗል።በወንዶች የቡድን አሸናፊዎች ፌዴራል ፖሊስ በ64 ነጥብ አንደኛ ሲሆን፤ኢት/ኤሌክትሪክ በ70 ነጥብ ሁለተኛ መከላከያ በ70 ነጥብ አሸናፊ ሆነዋል።
በሴቶች መካከል የተካሄደውን ውድድር አሸናፊዋ አትሌት ሮዛ ደረጄ፣ ለውድድሩ ጠንካራ ልምምድና ዝግጅት ስታድርግ መቆየቷን በመጥቀስ፤በውጤቱም እጅግ ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ ውድድሮች ተሳትፎ ያልነበራት አትሌት ሮዛ፤በ5ኛው የ30 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ መጀመሪያ ተሳትፎ የመጀመሪያ ድሏን አሳክታበታለች።አትሌቷ በቀጣዩ ዓለም ዋንጫ በማራቶን ውድድር ጥሩ ውጤት በማምጣት አገሯንና ሯሷን ማስጠራት እንደምት ፈልግም ተናግራለች።
የመብራት ሀይሉ ፅዳት አበጀው፤የዘንድሮው ዓመት ውድድር በጣም ፈታኛና ከባድ ብርቱ ፉክክር የታየበት መሆኑን ጠቅሶ፣በማሸነፉ በእጅጉ መደሰቱን ይገልጻል፡፡እርሱም ሆነ ክለቡ መብራት ሃይል ለሁለተኛ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆናቸው ምክንያት የሆኑትን አሰልጣኙንም አመሰግኗል።በቀጣይም በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች የአገሩን ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርጎ ለማውለብለብ ፅኑ ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።
በውድድሩ አንደኛ ሆነው ላጠናቀቁ አትሌቶች ሰላሳ ሺ ሁለተኛ ለወጡት 22 ሺ ሶስተኛ ለሆኑት ደግሞ 16 ሺ ብር ሽልማት ተሰጥቷል። ከአንድ እስከ ሶስት ከገቡት ባሻገር እስከ አስረኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ አትሌቶች የገንዘብ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል። የቬትራን ከሃምሳ ዓመት በታች እና በላይ ተወዳዳሪዎች ከሶስት ሺ ብር አንስቶ እስከ አምስት መቶ ብር የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴሬሽኑ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሜዳልያና የዋንጫ ሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓቱን አካሂደዋል።
የቻይና አትሌቶችን ጨምሮ በርካታ አትሌቶች የተካፈሉበት 5ኛው የ30 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ደማቅ በሆነ መልኩ በሰላም ተጠናቋል።ለዚህም አዘጋጅ ኮሚቴ ከውድድሩ አንድ ቀን ቀድሞ በቢሾፍቱ ከተማ የባህል አዳራሽ ያካሄደው ለውድድሩ ስኬትና ደህንነት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን የመስጠት የህክምና የአቅጣጫ እንዲሁም ሌሎችንም መረጃ የመስጠት ቅድመ ውይይት ሁነኛውን አስተዋፆኦ አበርክቶም ታይቷል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2011
ታምራት ተስፋዬ