የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 6ኛ ሳምንት መርሐግብር በሳምንቱ የእረፍት ቀናትም በተለያዩ ከተሞች ተካሂዷል።በባሕር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የባሕር ዳር ከነማንና ኢትዮጵያ ቡናን አገናኝቷል።በበርካታ ደጋፊዎች ታጅበው ጨዋታቸውን ያካሄዱት የጣና ሞገዶች ጃኮ አራፋት ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ቡና 1ለ0 አሸንፏል፡፡ባሕር ዳር ትናንት ማሸነፉን ተከትሎ ስምንት ነጥቦችን በመሰብሰብ በፕሪሚየር ሊጉ ወደ 5ኛ ደረጃ ማደግ ችሏል፡፡
በዚህ ጨዋታም ስፖርት ከመዝናኛነት ባለፈ የሕዝብ ለሕዝብ አንድነትና ወንድማማችነት ማጠናከሪያ ሆኖም ታይቶበታል። የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ‹ክለብ› ደጋዎች ማኅበር በባሕር ዳር ለሚገኙ ተፈናቃዮች 10 ኩንታል ፊኖ ዱቄትና 200 ኪሎ ግራም አልሚ የሕጻናት ምግብ ድጋፍ ማድረጉም ታውቋል።
ሌላኛው የስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታ በጎንደር በአጼ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከነማ መከላከያን አገናኝቷል። በሜዳቸው ጦሩን ያስተናገዱት አፄዎች በጨዋታው ሁለት እኩል አጠናቀዋል።ሽመክት ጉግሣ እና ጂብ ቃሲም የአፄዎቹን ገብ ሲያስቆጥሩ ምንይሉ ወንድሙና ፍቃዱ ዓለሙ የእንግዳውን መከላከያ ግቦች አስቆጥረዋል።
አዳማ ከተማና መቀሌ 70 እንደርታ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ የተገናኙበት ጨዋታ በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡አዳማ ከተማ በሜዳው ባደረገው ጨዋታ 3 ለ 1 አሸንፏል፡፡ በጨዋታውም በተለይ በዘንድሮ የሊግ ውድድር ድካማ ሆኖ የታየበትን በግብ ማግባት ድክመት አርሞ ታይቷል።ውጤቱንም ተከትሎም ከደረጃው ሰንጠረዙ ግርጌ መውጣት ችሏል።
ሌላኛው የስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታ ስሁል ሽረን ከሲዳማ ቡና አገናኝቷል።በአምስተኛው የሊጉ ሳምንት መርሃ ግብር ከጅማ ጋር እቻ የተለያዩት ሽረዎች በስድስተኛው ሳምንት ጨዋታም አሸናፊ ሆነው መውጣት አልቻሉም።በሽረ ስታዲየም የተካሄደው ጨዋታም አንድ እኩል ተጠናቋል። ጨዋታው ለሲዳማ ቡና አዲስ ግደይ፣ ለስሁል ሽረ ደግሞ ልደቱ ለማ ኳስን ከመረብ ያገናኙ ተጫዋቾች ሆነዋል።
በስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ሳይካሄድ የቀረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ትናንት ተካሂዶ ያለምንም ግብ ተጠናቋል።
ሀዋሳ ከተማ 11 ነጥቦችን በመሰብሰበ በፕሪሚየር ሊጉ ሰንጠረዥ ቀዳሚ ነው፡፡ሲዳማ ቡና ደግሞ በ 9 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ፋሲል ከነማ፣ኢትዮጵያ ቡና፣ ባሕር ዳር ከነማ እና ወላይታ ዲቻ በተመሳሳይ ስምንት ነጥቦች በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ3ኛ እስከ 6ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ ደደቢት ያለምንም ነጥብ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ይገኛል፡፡
ከፍተኛ ግብ አግቢነቱን አዲስ ገደይ በአምስት ግቦች ሲመራ፤የሃዋሳው ታፈሰ ሰለሞንና እስራኤል እሸቱ እንዲሁም የፈረሰኞቹ አቤል ያለው እያንዳንዳቸው በሶስት ግብ ይከተሉታል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2011
ታምራት ተስፋዬ