እግር ኳስ በመዝናኛነቱ እንዲቀጥል ሰላማዊ የውድድር መድረክ መፈጠሩ የግድ ነው። ስኬታማ ሊግ ለመመልከት ደግም ጊዜና ገንዘቡን ወጪ አድርጎ፣ ፀሐይና ብርድ ሳይበግረው፣ተስፋ አስቆራጩን ሰልፍ ተቋቁሞ ስታድየም የሚገኘው የስፖርት ቤተሰብ የአደጋገፍ ስርዓትና ስፖርታዊ ጨዋነት ወሳኝነት አለው።
ወጥ የውድድር መርሃ ግብር እጦት፤የዳኝነት ውሳኔ አሰጣጥ ችግር እንዲሁም ደጋፊዎች፤ የተጫዋቾችና የአሰልጣኞች ስፖርታዊ ጨዋነት ምግባር ችግር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መገለጫ መሆን ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል።
የወንድማማችነትና የመግባባት ምሳሌ የሆነው ንፁህ እግር ኳስ ተብክሏል። የስታድየም ድምቀትና ለእግር ኳሱ ውበት ዋና ተዋናይ የሆኑ ደጋፊዎች የአደጋገፍ ስርአት ተለውጧል።ከስታድየሞቻችን የሚሰሙት ህብረ ዝማሬዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየደበዘዙ በአንፃሩ አፀያፊ ስድቦችና ፀብ አነሳሽ ድርጊቶች ጎልተው ተሰምተዋል፤ታይተዋል።በእግር ኳስ ሁነት ማሸነፍና መሸነፍ ያለና ወደፊትም የሚኖር መሆኑ ተረስቷል።
ይህን ተከትሎ በሚነሱ ግርግሮች ስጋትም ስታድየሞቻችን ለህፃናት፣በእድሜ ለገፉ ሰዎች፣ሴቶችና ለአካል ጉዳተኞች ምቾት የሚነሱ ሆነዋል።አዳዲስ ተመልካችን ለመመልከት እስኪያቅትም የካምቦሎጆው መንደር ለእንግዶቹ በሩን የዘጋ መስሏል።
ይሁንና በተለይ ባለፈው ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ መገለጫዎች እስኪመስሉ የተስተዋሉና የአገሪቱን እግር ኳስን መቀመቅ የሚከቱ እክሎች በዘንድሮው የሊግ ውድድር እንዳይስተዋሉ ሊጉም ካለፉት ጊዜያት በተሻለ በስፖርታዊ ጨዋናት የታጀበ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ብዙ ደክሟል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ የፌዴሬሽኑ አዲስ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጂራ በየክልሉ እየዞሩ ስፖርታዊ ጨዋነትን ማረጋገጥ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ከከተማ አስተዳደሮች ጋር ተወያይተዋል።ክለባትና የደጋፊ ማህበራትም በየፊናቸው የየበኩላቸውን ተወጥተዋል።ክለቦች ተጨዋቾቻቸውን በስነ ምግባርና በእውቀት በማነጽ ረገድ የቤት ስራቸውን እንዲወጡ ተደርጓል። ከሳምንት በፊት በአዳማ ከተማ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ የስፖርት ቤተሰቡን ያሳተፈ ውይይትም ተካሂዶ ነበር ።
ይሁንና በስድስተኛው ስምንት የሊጉ መርሃ ግብር ፌዴሬሽኑም ሆነ የስፖርት ቤተሰቡ ጥረት ከንቱ ሆኖ የተለያዩ መድረኮች የተካሄዱ ስብሰባዎችም ፍሬ አልባ ሆነው ታይታል።በእለቱ በቅድሱ ጊዮርጊስና በሃዋሳ ከተማ መካከል ሊካሄድ በነበረው ጨዋታ ቀደም ሲል ለስፖርታዊ ጨዋነት ምክንያት ሆነው የሚቀርቡ ፤የዳኛ ውሳኔ አሰጣጥ ጉድለት፤ አሊያም ዳኞችን ውሳኔ አምኖ አለመቀበል፤ክብር የሚነኩ ዘለፋዎች፣የተጫዋቾችና አሰልጣኞች ለፀብ የሚያነሳሱ ድርጊቶች አልተስተዋሉም።
ይልቅስ የስፖርታዊ ጨዋናት ጉድለቱ ጨዋታው ከመጀመሩ ቀድሞ የተከሰተ እንደመሆኑ ሌላ የግጭት መነሾ ተስትውላል። ከጨዋታው መጀመር 25 ደቂቃ ቀድሞ በደጋፊዎች መካከል የተካሄደው አምባጓሮም በርካታ የስፖርት ቤተሰቡን አባላት ለጉዳት ዳርጓል።ክስስቱም ጨዋታውን ለመታዳም ወደ ሜዳ የገቡ ደጋፊዎች ስሜት ክፉኛ አሳዝኗል፣አንገት አስደፍቷል።
አስር ሰዓት ላይ መጀመር የነበረበት ጨዋታ እስከ ምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት ድረስ ቢጠበቅም የኋላ ኋላ በተለይ ሃዋሳ ከተማዋዎች ጨዋታውን ለማካሄድ ባለመፈለጋቸው ሳይካሄድ ቀርቷል።
ከብጥብጡ በኋላ ለክስተቱ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ የቀረበው፤ በእለቱ ለእንግዳ ደጋፊዎች የተዘጋጀው የመቀመጫ ስፈራ አናሳ ሆኖ መቅረቡ ነው የተባለ ሲሆን፤ይህ ግን ብቻውን ለክስተቱ አሳማኝና በቂ ምክንያት ነበር ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ምክንያቱም የቦታ ጥያቄ ከሆነም በውይይት መፍታት ሲቻል ድንጋይ የሚያወራውር አንዳችም ምክንያት ይኖራል ተበሎ አይታሰብም።
ምንም እንኳን በእለቱ የግጭቱ ቀስቃሽ የሆኑ ደጋፊዎችን በውል መለየት ቢያስችግርና ቅድሚያ ጥፋተኛ የነበረው ማነው የሚለውን አጣርቶ ውሳኔ የሚያሳልፈው የሊግ ኮሚቴው በእለቱ በስታዲየሙ አንድ አቅጣጫ የተስተዋለው ግጭትና በሜዳው ክልል የነበረው ድብድብ በእጅጉ የሚያሳፍ፤ የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግም ስርዓቱን የሚያስጠብቅለት እንደሌለ የሚመሰክር ሆኖ ታይቷል።ከሁሉም በላይ በእንግዳ ክለብ ደጋፊዎች በአግባቡ መለየትና ከአደጋ መከላከል የማያስችል አጥር መኖሩም ጉዳቱን ከባድ አድርጎታል።
በተለይ የድንጋይ ውርውራውን ተከትሎ ሸሽተው ወደ ሜዳው ክልል በገቡ የሃዋሳ ደጋፊዎችና በቅዱስ ጊዮርጊስ ስትዋርትቶች መካከል የተፈጠረው ግብ ግብ እጅጉን የሚያሳዝን ሆኖ ታይታል።ይሁንና ስታዲየሙን ከአፍ እስከ ገደፉ የሞሉት የፈረሰኞቹ ደጋፊዎች ከምንም በላይ ለስፖርታዊ ጨዋነት በመገዛት ወደ ፀብ አለመመራትና ሜዳ ወደነበሩት የሃዋሳ ደጋፊዎች አለመግባታቸውም በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አሰጥቷቸዋል።
የስታድየሙን ፀጥታ ለማስከበር የሚመደቡ የፖሊስ ኃይሎች ቀደም ሲል ከነበረው ታሪክ ጋር ሲነፃፃር ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ዱላን አማራጭ አድርገው አለመታየታቸው በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አሰጥቷቸዋል።
በአጠቃላይ አንድ እርምጃ ፈቀቅ ማለት በተሳነው እግር ኳሳችን መሰል ክስተቶች መመልከት የሚቆመው እንዲሁም ሊጉን ስነስርዓት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው የስፖርት ቤተሰቦች ይህኑ ተግባራቸውን በአግባቡ የሚወጡት መቼ እንደሆን ለመረዳት አዳጋች ሆኗል።
ከሁሉም በላይ በቅዱስ ጊዮርጊስና በሃዋሳ ከተማ መካከል ሊካሄድ ከነበረው ጨዋታ ቀድሞ የተከሰተው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ግን ሊጉ ዘንድሮም ስርዓቱን የሚያስከብርለት ማጣቱን አሳይቷል።የሊጉን ስነስርዓት ለማስጠበቅ ከስፖርት ቤተሰቡም በላይ ከባድ ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለይም ጠንካራ ህግጋትን በማስተላለፍ ረገድ ከባድ የቤት ስራ እንዳለበት አመላክቷል።
ይህን መሰሉ የስታድየም ብጥብጥና ሁከት በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት፤ ነገሮች ፈራቸውን ሳይለቁ አስቀድሞ ነገሮችን ማስተካከልና መስመር ማስያዝ ካልተቻለ ከዚህም በከፋ ሁኔታ ወደ መቀመቅ መውረዳችን ሳይታለም የተፈታ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2011
ታምራት ተስፋዬ