መግቢያ በሩ ላይ እንደደረስን ከመኪናችን ወርደን፡፡የምንገባበትን ግቢ ከሩቅ ቃኘሁት፡፡ወደ ውስጥ ከሚያስገባው የአስፋልት መንገድ ውጪ ግቢው ጫካ ነው፡፡ ሰአቱ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ቢሆንም የገቢና ወጪው ብዛት ግን ከረፋድም በላይ ያስመስለዋል፡፡ በርካታ ሰዎች ይገባሉ፤ ይወጣሉ፡፡ ወደ ስፍራው ለመምጣት ተኝተው ያደሩም አይመስልም፡፡
ወደ ውስጥ መግባት ጀምረናል፡፡አንዳንዶቹ ወደ ውስጥ የሚገቡት በአካል በቃት እንቅስቃሴ ታጀበው ነው።መንገዱ ዳገታማ ቢሆንም ወደ ኋላ የሚጓዙም ይስተዋላሉ። ምክንያታቸው ግን ትንሹን ትልቁን ግር ያሰኛል። ጥያቄንም ያጭራል።
ፎቶ የሚነሳው እና የሚያነሳው ብዛቱ ልክ የለውም።ወደ ውስጥ ሲዘለቅም ግቢው ዳጋታማ፣ ቁልቁለታማ ፣በደን የተሸፈነ ነው፤ አበባው ግቢውን ስጋጃ የተነጠፈበት አስመስሎታል፡፡ መንገዶቹ ለእግረኞችም ሆነ ለተሸከርካሪ ምቹ ቢሆኑም ተሽከርካሪ ሲገባም ሆነ ሲወጣ አይስተዋልም፡፡
ለውስጥ ለውስጥ አገልግሎት ይሁን ለሌላ ግን ለየት ያሉ የሚያማምሩ ግልጽ ተሽከርካሪዎች ቆመው ይታያሉ፡፡ምን አልባትም ግቢውን እየተዘዋወሩ ለሚጎበኙ፣ ለአካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች ወይም ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ግቢው ለሚመጡ እና ከግቢው ለሚመለሱ ተብለው የተዘጋጁም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ያለነው በቻይና ጉዋንዡ ከተማ ከሚገኝ አንድ ሀውልት ስፍራ ነው፡፡ከመግቢያው በስተቀኝ በኩል የጉዋንዡ ግንብ ይታይል፡፡ወራሪዎችን ለመከላከል የተገነባ ነው አሉ፡፡በስተግራ ፊት ለፊት ከፍ ባለ ስፍራ ላይ አንድ ግዙፍ ሀውልት ቆሟል፡፡ ወደ ሀውልቱ ለመድረስ ብዙ ደረጃዎች መውጣትን ይጠይቃል፡፡70 ደረጃን ባያህልም ሌሎቹን ይስተካከላል፡፡
በሀውልቱ ላይ የአምስት ፍየሎች ምስለ ቅርጽ ይታያል፡፡ የአስጎብኚያችን እውነተኛ ስም ቻን ነው፡፡ለእኛ ግን ፍሌክስ በሉኝ ብሎናል፡፡መጠሪያ ስሙን ከቻን ወደ ፍሌክስ የቀየረው ለእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች እንዲመች በሚል ነው፡፡
ወደ ተነሳሁበት ሃሳብ ልመለስና በሀውልቱ ስለሚታዩት ስለአምስቱ ፍየሎች ፍሌክስ የነገረንን ላጫውታችሁ።ጥንት የጉዋንዡ ምድር በድርቅና በረሃብ ክፉኛ ይመታ ነበር ።ይህን ችግር የተመለከተ አንድ መንፈሳዊ ሀይል ታዲያ አምስት ፍየሎችን የስንዴ ዘላላዎችን አስይዞ ወደ ምድር ይልካቸዋል፡፡የአካባቢው ሰዎች ይህን ዘር ወስደው በመዝራት ረሀብን ተሰናበቱ፣ ከዚያን ጊዜም አንስቶ የጉዋንዡ ምድር ጥጋብ ሆነ፣ ፍየሎቹም አለት ሆነው ቀሩ፤ ይባላል፡፡ የአምስቱ ፍየሎች ሀውልትም ይህን አፈ ታሪክ ታሳቢ በማድረግ እንዲቆም የተደረገው ነው።
ቻያናውያን በየከተሞቹ አካባቢያቸውን የሚገልጽ ሙዚየም ይገነባሉ፤ ሀውልት ያቆማሉ፡፡ለእኔ ከሀውልቱም በላይ የቆመበት አካባቢ ማርኮኛል፡፡ ይህ ሀውልት ያለበት አካባቢ በሙሉ ያምራል፡፡ዳገት ቁልቁለት፣ደን ጢሻ በአንድ ስፍራ በሚማርክ መልኩ ይታዩበታል፡፡ የስፍራው የፓርክ ገጽታ በእጅጉ ይጎላል። ስፍራውም የፍየሎቹ ሀውልት ከሚባል ይልቅ አስደማሚው ፓርክ ቢባል ይበልጥ ይገልጸዋል፡፡ ፓርክ ብሎ ማቆምም ያስቸግራል፡፡ በሙዚቃና በአሰልጣኝ የታገዘ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ይሰራበታል።እነሱን የሚመለከት ደግሞ ስፍራውን አስደማሚው ጂም ሲል ሊሰይመው ይችላል።
በደረጃ መውጣት መውረድ ፣መንገድ ይዞ ቁልቁል መሄድ መመለስ ፣ሽቅብ መውጣት በራሱ ስፖርት ነው፡፡በእዚህ ላይ ነው እንግዲህ ብዙዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሚታየው፡፡ ከደረጃው ቁልቁል መውረድ ፣ ከጢሻዎቹ ወይም ከሸለቆው አካባቢ ሽቅብ መውጣት ለሚፈልግ ይመስላል ሊፍት ተዘጋጅቷል፡፡ይህ ምናልባት ለደካሞች የተዘጋጀም ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ነገር የሃሳቡ ምጡቅነት ነው፡፡የቀረው ለቻይና ብዙም ብርቅ ያልሆነው እስካሌተር ብቻ ነው፡፡
ቻይናውያን እና የተለያዩ ሀገሮች ዜጎች ከልጅ እስከ አዛውንት በስፍራው መገኘታቸው ብዙ ጥቅም ቢያገኙበት ነው፡፡ በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፍ ያሰኛል፡፡ ሀውልቱ የአረንጓዴ ስፍራው፣ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ምቹነት፣ የመሬቱ አቀማመጥና ይህን ሁሉ አገልግሎት እንዲያበረክት ተደርጎ የተሰራበት ሁኔታ ወዘተ በሙሉ የስፍራው ውበት ናቸው፡፡ታሪካዊ፣ መንፈሳዊ እና ተፈጥሯዊና የሰው ልጅ ጥበብ ጭምር የተካተተበት ይህ ስፍራ ሰዎች በዝተው በታዩበት አይደንቅም፡፡ ሰዎች የፈሉገትን ወይም ሁሉንም ማድነቅ የሚችሉበት ነው፡፡
ከቤጂንግ የሶስት ሰአት በረራ አርገን ጉዋንዡ ከገባን በኋላ አዳራችንን ለማድረግ ምሽቱኑ ያቀናነው ወደ የባህል መድኃኒቶች እጽዋት መገኛ ወደ ሆነው ሎፉ ተራራ አካባቢ ነው፡በአቅራቢያው ሎፉ የምትባል ትንሽ ከተማ ትገኛለች፡፡ በእዚህ ከተማ የማደራችን ሚስጢርም ጧት ላይ በዚህ ደን ክልል ውስጥ የሚገኘውን የባህል መድኃኒት ሙዚያም ለመጎብኘት ነው፡፡
አካባቢው እጅግ ውብ ነው፡፡የባህል መድኃኒቶች ሙዚየሙ የተመሰረተበት ስፍራ እና በሙዚየሙ ውስጥ የሚገኙት ባህላዊ መድኃኒት አመራርትን ፣በባህል መድኃኒት ታዋቂ የሆኑትን ጊ ሆንግን የሚመለከቱ ሰነዶች ተካተውበታል፡፡ በደኑ ውስጥ ወደ 1ሺ 200 ለባህል መድኃኒት ቅመማ የሚያገለግሉ እጽዋት እንደሚገኙ ከሙዚየሙ አስጎብኚዎች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡በአቅራቢያወም ይህን እምቅ ሀብት መሰረት ያደረገ ግዙፍ የመድኃኒት ፋብሪካ ተገንብቶ የባህል መድኃኒቶችን በዘመናዊ መንገድ እያመረተ ይገኛል፡፡
ስፍራውን እና የባህል መድኃኒት እጽዋቱን ይዞ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባሮችን የእኛ ሀገር የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ፣የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የሚመለከታቸው አካላት ይህን ስፍራ ቢጎበኙት ምንኛ ጥሩ ነበር፡፡
ማለዳ ቁርሳችንን በልተን የመጀመሪያ ጉብኝት ያደረግነው በደን ውስጥ የሚገኘውን አንድ ታሪካዊ የባህል መድኃኒት ተክሎች የሚገኙበትን ፣ ጥንት የባህል መድኃኒት የሚመረትበትን መንገድ ፣ በባህል መድኃኒት የሚታወቀውን ጊ ሆንግን ዝና ሰማን፡፡አነበብን፡፡
ሙዚየሙ በትክክለኛ ስፍራ ላይ ነው የተገነባው፡፡የባህል መድኃኒት ተክሎች በብዛት የሚገኝበት ስፍራ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ከዚህ በመለስ የአካባቢው አረንጓዴነት ፣ አካባቢውን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ የእግር መንገዶች ፣ድልድዮች ፣ የአበባ ስፍራዎች በርቀት የሚታየው በደን የተሞላ ተራራማ ስፍራ በሙሉ መልሰው መልሰው ቢጎበኟቸው አይጠገቡም፡፡
ተማሪና ተመራማሪዎች ስፍራውን ያዘውትሩታል፡፡ የተለያዩ የህብተሰብ ክፍሎች ከልጅ እስከ አዛውንት በአካባቢው ያልተገኘ የለም።
በሼንዜን ከተማም ያስተዋልነው የሀገሪቱ ሙዚየሞችና ሀውልቶች ሙዚየምና ሀውልቶች ብቻ አለመሆናቸውን እና የአረንጓዴ ስፍራዎችም ጭምር መሆናቸውን ነው፡፡ አንዳንዶች ከሀውልትና ሙዚየሙ አረንጓዴ ስፍራዎቹን ሊያስበልጡ ይችላሉ፡፡ የሼንዜን ሙዚየምም ግዙፍ በአቀራረቡም የተለየ ሙዚየም ከመሆኑ በተጨማሪ ዙሪያውን ያሉት የአረንጓዴ ስፍራዎች ትታችሁን አትሂዱ የሚሉ ናቸው፡፡በእዚህም ስፍራ ልጆች ወጣቶችና አባቶች ጭምር በብዛት የሚታዩበት ነው፡፡በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎችም ይታያሉ፡፡
በእዚህ ስፍራ የቻይና ሪፎርሚስት መሪዎች ሼንዜንን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ብለው ከሰየሙዋት ከዛሬ ሃምሳ አመት ወዲህ በሀገሪቱ በተለይ በግዛቲቱ የተደረጉ እንቅስቃሴዎችን የሚመለከቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና የዘመኑን ልማት የሚመለከቱ በአካል የተገኙ የሚመስሉ ቅርጻቅርጾች የቀረቡበት ነው፡፡
በሙዚየሙ የሪፎርሚስቱ መሪ የዴን ዣዎፒንግ ቅርጽ ከእነሙሉ ልብሳቸው ቆመው ሲታዩ በአካል ያሉ ይመስላል፡፡በመሪነት ዘመናቸው ይጠቀሙባት የነበረች አውቶሞቢል የቻይናን ሰንደቅ አላማና የኮሚኒስት ፓርቲውን አርማ እያወለበለበች፣ መሪው ከመኪናዋ በላይ ባለው ክፍት ቦታ ሆነው ንግግር የሚያደርጉባቸው ሶስት ማይኮችም ይታያሉ፡፡
ከሁሉም ከሁሉም የሚያስገርመው የቻይና የግንባታ ሰራተኞች በስራ ላይ እንዳሉ አድርጎ የሚያሳይ የቅርጻ ቅርጽ ስራ ብዙ ትምህርት የሚቀሰምበት ነው፡፡አታምኑኝም ቀርቤ እስካረጋገጥኩበት ሰአት ድረስ በሙዚየሙ ውስጥ አንዳች የእድሳት ስራ እየተካሄደ ያለ ነበር የመሰለኝ፡፡
የተወሰኑት በህንጻ መወጣጫዎች ላይ የተወሰኑት ከስር እቃ ሲያቀብሉ ፣ የሚገነባው ሲገነባ፣ ከእነ ግንባታ መሳሪያዎቻቸውና በግንባታ ወቅት ልብሳቸው ይታያሉ፡፡ ምን አለፋችሁ በጥድፊያ ግንባታ ሲካሄድ ያያችሁትን እንቅስቃሴ በአካል ያለ ያህል ተደርጎ የቀረበበት ይህ ጥበብ ሙዚየምና ሀውልት አደራጆቻችን ትምህርት የሚቀስሙበት ነው፤ኢትዮጵያውያን የዘርፉ የጥበብ ባለሙያዎች ይህን ታዩት ዘንድ እመኝላችኋለሁ፡፡
ጥንት በድራጎን ትታወቅ ነበር በምትባለው ሆያን ከተማ የሚገኘው የድራጎን ሙዚየምም ሌላው በልዩ ሁኔታ የተደራጀ ሙዚየምና የመስህብ ስፍራ ነው፡፡በእዚህም እንደሌለቹ የሙዚየምና የሀውልት ስፍራዎች በርካታ ቻይናውያንና የውጭ ሀገር ዜጎች ይታያሉ፡፡
የድራጎን ቅሬት አካሎች በብዛት የቀርቡበት ውብ ሙዚየም ነው፡፡ሙዚየሙ በአረንጓዴ ስፍራ የተዋበ ሲሆን፣ ቻይናውያን በድራጎን ቅሪተ አካሎች የተሞላውን ሙዚየም እና የአረንጓዴ ስፍራዎቹን በእጅጉ ይጎብኙታል፡፡
ገና ወደ ሙዚየሙ አዳራሽ ሲገባ በአካል ያለ የሚመስል የግዙፍ ድራጎን ቅርጽ ይታያል፡፡በተለያዩ ፊልሞች የሚሰማው የድራጎን ድምጽ ከፍ ብሎ ተለቋል፤በዚህ ክፍል የሚሰማው ይህ የድራጎን ድምጽ እና ቅርጹ ድራጎን በአካል ያለ ይመስላል፡፡አብረውን ከሚገኙ ጎብኚዎች ብዙዎቹ ድምጹን ሲሰሙ ፊልሞቹ ትዝ እንዳላቸውም ሲገልጹ ነበር፡፡
የሀገሪቱ ሙዚየሞች እና ሀውልቶች የሚገነቡበት ሁኔታ ብዙ ትምህርት የሚቀሰምበት ነው፡፡ከአረንጓዴ ስፍራዎች ተቀናጅተው የተገነቡበት ሁኔታ ተመልካቻቸው እንዲበዛ ፣ በህዝብም ዘንድ ይበልጥ እንዲታወቁ ያደርጋልና እኛም ከዚህ ብዙ መማር ይኖርብናል፡፡
ሀገሪቱ ሀውልቶች እና ሙዚየሞችን የያዘችበት መንገድ ፣ ቻይናውያንና የሌሎች ሀገሮች ዜጎች አዘውትረው እንዲጎበኙዋቸው አድርጓል ፡፡ በእርግጥ በአንዳንድ የሰማእታት ሀውልቶች አረንጓዴ ስፍራዎች ተያይዘው የተገኙቡበት ሁኔታ ቢኖርም ይበልጥ ሊሰራበት ግን ይገባል፡፡ጎበዝ የቤት ስራ አለብን፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2011
በኃይሉ ሳህለድንግል