እንቁጣጣሽ ከሌሎች በዓላት ሁሉ ይለያል። ሌሎች በዓላት ሃይማኖታዊ ወይም ባህላዊ ይዘታቸው ይጎላል። ለምሳሌ መስቀል፣ ገና፣ ፋሲካ ብንል ሃይማኖታዊ ይዘታቸው ይበልጣል። ጥምቀት፣ አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል ብንል መነሻቸው ሃይማኖታዊ ይሁን እንጂ ባህላዊ ይዘታቸው ጎልቶ ይታያል። እንቁጣጣሽ ግን ጥበብ ነው፤ ሳይንስ ነው።
በሌላ በኩል እንቁጣጣሽ የእነዚህ ሁሉ በዓላት ማስጀመሪያ ነው። ለምሳሌ የ2011 ዓ.ም መስቀል፣ የ2011 ዓ.ም ገና፣ ጥምቀት፣ አረፋ፣ መውሊድ፣ ፋሲካ፣ አሸንዳ… እያልን የምንጠራው እንቁጣጣሽ በቀየረው ዓመት ነው። እንቁጣጣሽ ብዙ ጥበብና ሳይንስ የያዘ በዓል ነው።
በብዙ ነገሮቻችን ሁሉ ‹‹የራሳችን የዘመን አቆጣጠር ያለን›› እያልን እንጠራለን። ኢትዮጵያ ልዩ የሚያደርጋትም ይሄው ነው። ‹‹የ13 ወር ፀጋ›› በሚል ትታወቃለች። ይሄ ደግሞ ከዓለም ለየት ያደርጋታል። ይሄ ሁሉ የሆነው በእንቁጣጣሽ ጥበብ እና ሳይንስ ነው። እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ ምን ያህል የመጠቁ ሊቃውንት እንደነበሯት ያሳያል። የእንቁጣጣሽ ጥበባዊና ሳይንሳዊ ቀመር ምስክራችን ነው። ብዙዎቻችን ልብ የማንላቸው (አንዳንዴም ሃይማኖታዊ እየመሰለን) ሳይንሳዊ ቀመሮች አሉት። እንቁጣጣሽን በተመለከተ፤ ከመጻሕፍት፣ ከመጽሔቶችና ከልዩ ልዩ ሰነዶች መረጃዎችን በማሰባሰብ ስለእንቁጣጣሽ እናስነብባችሁ።
በእንቁጣጣሽ በሚቀየረው ዘመን ዓመቱ የራሱ የሆነ መጠሪያ አለው። ይሄውም ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስ እና ዘመነ ዮሐንስ ይባ ላል። ዘመኑን ለማወቅ ዓመተ ኩነኔ (5500) እና ዓመተ ምሕረት (አሁን ያለንበትን ዓመት ማለት ነው) በመደመር የሚገኘውን ውጤት ለአራት እናካፍላለን። በዚህ ስሌት መሠረት ቀሪው አንድ ከሆነ ዘመኑ ማቴዎስ ይባላል። ሁለት ከሆነ ዘመነ ማርቆስ፣ ሦስት ከሆነ ዘመነ ሉቃስ እና ያለ ቀሪ ከተካፈለ ደግሞ ዘመነ ዮሐንስ ይባላል ማለት ነው። በዚህ ስሌት መሰረት ከአራት ቀን በኋላ የምንሸኘው 2011 ዓ.ም ዘመነ ሉቃስ ነበር ማለት ነው። ምክንያቱም 5500+ 2011 = 7511 ነው። 7511 ለአራት ሲካፈል ቀሪው ሦስት ይሆናል።
እንቁጣጣሽ እንዲህ አይነት ሳይንሳዊ ቀመር ቢኖረውም ሃይማኖታዊ ይዘትም አለው። ለአራት የተካፈለበት ምክንያትም በአራቱ ወንጌላውያን (ማቲ ዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ዮሐንስ) ነው። ጥቅል መጠሪያው (በብዙዎች የሚጠራው) እንቁጣጣሽ በሚለው ቢሆንም ሌሎች መጠሪያዎችም አሉት። እነዚህ መጠሪያዎች ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ናቸው። እንቁጣጣሽ ከሚለው ጀምረን እንያቸው።
ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ የጠቢቡ ሶሎሞንን ዝና ሰምታ ኢየሩሳሌም ተጉዛ ስትመለስ ‹‹እንቁ ለጣትሽ›› በማለት ከእንቁ የተሠራ የጣት ቀለበት ንጉሥ ሶሎሞን እጅ መንሻ እንዲሆናት አበረከተላት። ይህን ታሪክ መነሻ አድርገው ‹‹እንቁጣጣሽ›› የሚለው ስያሜ ከዚያ እንደመጣ የታሪክ ድርሳናት ያስረዱናል። በኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ዕለት ምድሪቱ በክረምቱ ዝናብ ውሃ እና ጭቃ ሆና የቆየችው ጭቃና ጎርፉ ተወግዶ በአረንጓዴ እጸዋት ተውባ ሜዳው፣ ሸለቆውና ተራራው በአደይ አበባ ተንቆጥቁጠው የሚታዩበት ወቅት በመሆኑ ዕለቱ ‹‹እንቁጣጣሽ›› እንደተባለም ይነገራል።
ሌላኛው መጠሪያው ‹‹ዘመን መለወጫ›› የሚለው ነው። ይሄ ደግሞ ሳይንሳዊ ምክንያትን የሚከተል ይመስላል። ዘመን መለወጫ መስከረም ወር የሆነበት ምክንያት ብርሃንና ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው የሚሉም አሉ። ሌሊቱ ከቀኑ ጋር ይስተካከላል። የዓመቱ ቀናት 364 እና 365 (የጳጉሜን 5 እና 6 መሆን ተከትሎ) እየተባሉ የሚጠሩትም በዚህ አቆጣጠር ነው። በሃይማኖታዊ ምክንያት ደግሞ በኖህ ዘመን ተጥለቅልቆ የነበረው የጥፋት ውሃ የጎደለበት ወር ስለሆነ መስከረም የዘመን መለወጫ እንደተደረገ የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ።
ቅዱስ ዮሐንስ የሚል መጠሪያም አለው። ይሄኛው መጠሪያ ሙሉ በሙሉ ሃይማኖታዊ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ የተባለውም የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል መነሻ በመሆኑ ነው።
ስለእንቁጣጣሽ ስሞችና ቀመሮች ይህን ካልን የዘመን አቆጣጠራችን ከሌሎች የዓለም አገራት ለምን እንደተለየ ደግሞ ሊቃውንት የሚነግሩንን እንመልከት። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ‹‹ባሕረ ሐሳብ›› በሚል መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከምዕራባውያን የተለየበ ትን ምክንያት ሲገልጹ ‹‹ሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ዘመን መነሻ አድርገው ይጠቀማሉ፤ ታላቁ እስክንድርም የገነነበት ዘመን መቁጠሪያቸው ሆኖ ነበር›› ይላሉ። የኢትዮጵያ ካህናትም ዘመነ እስክንድር በሚል ይጠቀሙበት እንደነበር መጻሕፍት ይመሰክራሉ። ሶርያውያን የዘመን አቆጣጠራቸውን የሚለኩት በፀሐይ ቆጥረው የዓመቱን 365 ቀን ለስድስት አካፍለው ከሮማውያን በተዋሱት ጊዜ የዓመቱን መጀመሪያ አዲስ ዓመት ይሉታል። በኋላ የሰማዕታት መታሰቢያ እንዲሆን በ460 ዓመተ ዓለም ወደ መስከረም 1 ቀን ለወጡት። የአገራችን ሊቃውንትም አዲስ ዓመታችን መስከረም አንድ ቀን እንዲሆን የወሰኑት ይኸንን በመከተል ነው። የዓመቱን መጀመሪያ በመስከረም ማድረግን ከሶርያውያንም ሆነ ከግብጾች ብናገኘውም ጀማሪው በ46 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ይገዛ የነበረው ዩልዮስ ቄሣር ስለነበር የዩልዮስ ባሕረ ሐሳብ ይባላል።
ዩልዮስ ቄሣር በ46 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ባወጣው የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት መሠረት የዓመቱን 365 ቀናት ለስድስት ሰዓት አድርጎ ለአራቱ ወራት 30/30 ቀን ለአንዱ 28 ቀን በአራት ዓመት አንዴ 29 ቀናት፤ ለቀሩት ሰባት ወራት 31/31 ቀናት መድቦላቸው በ12 ቦታ ከፍሎታል።
አውሮፓውያኑ የሚጠቀሙበት ይህን አቆጣጠር መነሻ አድርገው ነው። የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን እንዴት እንደተለየ አሥራት ገብረማ ርያም ‹‹የዘመን አቆጣጠር›› በሚለው መጽ ሐፋቸው ሲገልጹ ‹‹ዲዮናስዮስ የተባለው የሮም መነኩሴ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተወለደበት ዘመን በስሌት ለመድረስ የተከተለው መንገድ የታሪክ ክስተትን ነበር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ዘመን ለመወሰን የታሪክ ክስተትን አልተከተለችም። ቤተ ክርስቲያናችን የተከተ ለችው ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን 5500 ዘመንን ነው›› በማለት የልዩነቱን ምክንያት ይገልጻሉ።
የዘመን አቆጣጠር ልዩነት መነሻው የዚህ ክስተት መሆኑን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲያረጋግጡ ‹‹ኢትዮጵያ ዘመነ ብሉይን እንዲህ አስከትላ 5500 ብላ ስትቆጥር ዘመነ ሐዲስ ልዩ ሆኖ ከማንም ቁጥር አይገጥምም። ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ከምስራቆቹም ከምዕራቦቹም ሁልጊዜ በሰባት ዓመት ታጎድላለች። ምክንያቱም ባለታሪኮችን ትታ ወንጌል ተርጓሚዎችን መነሻዋ ስላደረገች ነው›› ይላሉ። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ እና የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ልዩነት ሊኖረው ቻለ። ይሄ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን ጨምሮ የዓለምን መፈጠር ምክንያት አድርጎ የተቀመረ ወጥ አቆጣጠር እንጂ ነገሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የሚቀያየር አይደለም።
ስለኢትዮጵያውያን የቀን አቆጣጠር ካወራን ስለጳጉ ሜ ማንሳት የግድ ነው። ከዘመን አቆጣጠር ስሌቷ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ልዩ የምታደርጋት ይቺ የጳጉሜ ወር ነች። ይቺ ወር አምስት ወይንም ስድስት ቀን ናት። በአራት ዓመት አንዴ ስድስት ትሆናለች። በ600 ዓመት አንዴ ደግሞ ሰባት እንደምትሆን ሊቃውንት ይና ገራሉ። ይቺ አሥር ቀን እንኳን ያልሞላች ‹‹ወር›› እየተባለች ትጠራለች። የቤት ኪራይ አይከፈልባትም፣ የወር ደመወዝ አይገኝባትም።
ጳጉሜ በገጠር አካባቢ ‹‹ቋግሜ›› እያሉ ይጠሯታል። በጽሑፍ ደግሞ ብዙ ቦታ ላይ ጳጉሜ ቢሆንም ‹‹ጳጉሜን›› እየተባለም ይጻፋል። ያም ሆነ ይህ ቃሉ አማርኛ ወይም ሌላ የአገር ውስጥ ቋንቋ ሳይሆን የግሪክ ቃል ነው። ትርጉሙም፤ ቀሪ ዕለታት፣ ቅጥያ፣ ተጨማሪ…ማለት እንደሆነ ይነገራል።
የጳጉሜ ወር ብዙ ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክዋኔዎች ይከወኑባታል። የጳጉሜ ውሃ ከሌሎች ወራት በተለየ ቅዱስ ነው ተብሎም ይታሰባል። በዚህም ምክንያት በተለይም በገጠር አካባቢ ሰዎች በማለዳ በመነሳት ሰውነታቸውን ይታጠባሉ። ጳጉሜ ሦስት ደግሞ ‹‹ሩፋኤል›› ይባላል። በዚህ ዕለት ዝናብ ከጣለ ዓመቱ የሰላምና የበረከት ይሆናል ተብሎ ይታመናል።
ይህን ሁሉ ጥበብ የቀመሩልን እንግዲህ ሊቃውንት አባቶቻችን ናቸው። ሃይማኖታዊም ይሁን ሳይንሳዊ፣ ባህላዊም ይሁን ዘመናዊ ይህን የመቀመር ጥበባቸው የሥልጣኔ ጀማሪዎች እንደነበርን ማሳያ ነው።
የየትኛውንም ዓለም የዘመን አቆጣጠር ብንመለከት አንድን ክስተት መነሻ አድርጎ የተቀመረ ነው። ለዚያም ብዙ የዓለም አገሮች የሚጠቀሙት አንዲት አገር በቀመረችው ቀመር ነው። ኢትዮጵያ ግን ራሷ ቀምራ በራሷ የዘመን አቆጣጠር ትጠቀማለች። ይሄ ኩራታችን ነው። በዚህ ዓመት ደግሞ ነገ ጳጉሜ ሦስት የኩራት ቀን ተብሎ እየተከበረ ነው። እንዲህ አይነት የሚያኮራ ታሪክ አለንና መልካም የኩራት ቀን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011
ዋለልኝ አየለ