– ለ508 ኪሎ ሜትር መንገዶች ጥገና ይደረጋል
አዲስ አበባ፡- በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት 300 ኪሎ ሜትር አዳዲስ መንገዶች እንደሚገነቡና ለ508 ኪሎ ሜትር መንገዶች ጥገና እንደሚደረግ ተገለጸ። ለመንገዶቹ ግንባታ እና ጥገና አምስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በጀት ተይዟል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጥኡማይ ወልደገብርኤል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በ2012 በጀት ዓመት 808 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባትና ለመጠገን ዕቅድ ተይዟል። ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የመንገድ ጥገና ነው። የአዲስ አበባ መንገዶች ለረጅም ጊዜ ያገለገሉና በተለያየ ሁኔታ የተጎዱ ስለሆነ ከአዳዲስ መንገዶች ግንባታ ይልቅ ለጥገና ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ከሚጠገኑ መንገዶች 110 ኪሎ ሜትር አስፋልት፣ 100 ኪሎ ሜትር ጠጠር፣ 225 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅ መስመር፣ 30 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ እና 50 ኪሌ ሜትር የኮብልስቶን ጥገናዎች ናቸው። 16 ድልድዮች፣ 11 ሺህ የመንገድ ዳር መብራቶችና የአምፖል ጥገናዎች ይደረጋሉ። ‹‹አዳዲስ የሚገነቡ መንገዶች ሁሉም አስፋልት ላይሆኑ ይችላሉ›› ያሉት አቶ ጥኡማይ፤ ገረገንቲና አክሰስ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
የሚጠናቀቁበትን ጊዜ አሁን ላይ መወሰን እንደማይመች የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ለ2011 ዓ.ም ታቅደው ባለመጠናቀቃቸው ለ2012 የተላለፉም እንዳሉ አስታውቀዋል። በ2012 ዓ.ም ይጠናቀቃሉ ተብለው በ2010 ዓ.ም የተጀመሩ 16 ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅ ሥራም እንደሚከናወን አስረድተዋል። በ2012 ዓ.ም የሚጀመሩ አዳዲስ የመንገድ ግንባታዎች በቁጥር 40 እንደሆኑም አቶ ጥኡማይ ገልጸው ቀደምሲል የተጀመሩትን ከሳር ቤት ቄራና ጎተራ እና ከሃያ ሁለት በጎላጎል ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ የሚወጣው ሁለት ፕሮጀክቶች የማጠናቀቅና ሌሎቹንም የማስጀመር ሥራ በበጀት ዓመቱ እንደሚከናወን አስረድተዋል።
የመንገድ ግንባታዎች ላይ የኮንትራክተሮችን ብቃት በተመለከተ ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፤ ግንባታዎችን በወቅቱ እንዳያጠናቅቁ እንቅፋት የሆነው የወሰን ማስከበር ጉዳይ ነው። አንዳንድ ኮንትራክተሮችም ብቃት እያላቸውና ቶሎ መጨረስ እየፈለጉ በወሰን ማስከበር ጉዳይ ይጓተትባቸዋል። በሌላ በኩል በኮንትራክተሮች ብቃት ማነስም የተጓተቱ አሉ። በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት በተደረገው ግምገማ ከላምበረት በኮተቤ ካራ ያለው ፕሮጀክት ዝቅተኛ አፈጻጸም ያስመዘገበው በኮንትራክተሮቹ ድክመት ነው።
በኮንትራክተሮች አማካኝነት የሚታዩ የግንባታ መጓተቶችን ችግር ለመቅረፍ ለአንዳንድ ኮንትራክተሮች ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባሻገር በወሰን ማስከበር ጉዳይ ግንባታዎች እንዳይጓተቱ ከተለያዩ አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስድስት ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ በአገልግሎት ላይ ይገኛል። በ2012 ዓ.ም በአዲስ መልክ ከሚገነቡ መንገዶች መካከል የታሰቡት ከጎጃም በር በሽሮ ሜዳ ፈረንሳይ፣ ኮተቤ ኪዳነምህረት፣ ከናይጀሪያ ኤምባሲ ቀጨኔ፣ ቦሌ ኢንዱስትሪ መንደር፣ ማሪዮት ሆቴል ፍላሚንጎ፣ ፍልውሃ አደባባይ ይጠቀሳሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011
ዋለልኝ አየለ