ለአንድ አገር የዕድገት መሰረቱ ትምህርት እና ስልጠና ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የብልጽግና ማማው ላይ የተቀመጡ አገሮች አሁን ላሉበት የዕድገት ደረጃ የበቁት የሰው ኃይላቸውን በትምህርትና ስልጠና በመገንባታቸው መሆኑ አያጠያይቅም። ኢትዮጵያም የእነዚህ ያደጉ አገሮችን ልምድ በመቅሰም በተለይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ለአገር ዕድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንዲሆን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል።
በአገር አቀፍ ደረጃም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት 1 ሺህ 687 መድረሳቸው መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያመላክት ሲሆን፤ በአገር አቀፍ ደረጃ በነዚህ ተቋማት መካከል በቴክኖሎጂና በጥናትና ምርምር እንዲሁም በክህሎት የተደገፈ የፈጠራ ስራ ውድድር ይካሄዳል። ይህ የፈጠራ ስራ ውድድር መካሄዱ በተቋሞቹ ብቁ ባለሙያዎች እንዲፈሩ ከማገዙም ባለፈ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ አያሌ የፈጠራ ስራዎች እየፈለቁ ይገኛሉ።
በእነዚህም ተቋማቱ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማሸጋገር ረገድ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ የመጣ ሲሆን፤ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው በዘጠነኛው አገር አቀፍ የፈጠራ ስራ ውድድር ላይ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት አሰልጣኞች ከተሰሩ አያሌ ችግር ፈች የፈጠራ ስራዎች መካከል አንዱ ሁለገብ የእህል መውቂያ ማሽን ነው።
ይህ የፈጠራ ስራ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ኢንስቲትዩት የተሰራ ነው። ይሄንን የፈጠራ ስራ የኮሌጁ የማኑፋክቸሪንግ ትምህርት ክፍል አሰልጣኞች አቶ ሳምሶን ኃይሉ፣ አቶ መኮንን ፍላቴ፣ አቶ ሙሉቀን ገዛኽኝ እና አቶ ግዛቸው ከበደ በቡድን የሰሩት ነው፡ ፡ የፈጠራ ስራቸው በክልሉ በተካሄደ የአሰልጣኞች የፈጠራ ስራ ውድድር አንደኛ ከመውጣቱም ባሻገር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው በዘጠነኛው አገራዊ የፈጠራ ስራ ውድድር ላይ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ አድርጓቸዋል።
እኛም እነዚህ አሰልጣኞች የሰሩት የፈጠራ ስራ ለአገር የሚያበረክተው ፋይዳ ምን እንደሚመስል ስለፈጠራ ስራቸው ገለጻ እንዲያደርጉልን የፈጠራ ስራውን ከሰሩት አሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆኑትን አሰልጣኝ ግዛቸው ከበደን ለዛሬ በሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችን እንግዳ ልናደርጋቸው ወደናል።
አቶ ግዛቸው እንደገለጹት፤ የሰሩት የፈጠራ ስራ ሁለገብ የእህል መውቂያ ማሽን ሲሆን፤ ማሽኑም በቆሎን መፈልፈል ስንዴ፣ ገብስ እና ማሽላን መውቃት ያስችላል። እንዲሁም ብዕሩን፣ አገዳውንና ተረፈ ምርቱን በማቀነባበር ለከብቶች መኖ በቀላሉ ለማዘጋጀት ያስችላል። የፈጠራ ስራውንም ሁለገብ ያሉት ከአሁን በፊት በአገር ውስጥም ሆነ በሌሎች አገሮች ያሉ ማሽኖች በቆሎን ለመፈልፈል ወይም ስንዴን ለመውቃት ብቻ የሚያስችሉ እንደነበር በመጠቆም፤ ይህ ግን ሶስት ስራዎችን በአንድ ማሽን ለመስራት እንደሚያገልግል ይናገራሉ።
የፈጠራ ስራውን በስድስት ወራት ውስጥ ሰርተው በማጠናቀቅ በ2009 ዓ.ም ሙከራ ላይ በማዋል ለገበሬው ማሸጋገር እንደተቻለ የሚናገሩት አሰልጣኙ፤ የፈጠራ ስራውን በቀላሉ በአገር ውስጥ የሚገኙ እንደ ላሜራ፣ የተለያዩ ቅርጽና ይዘት ያላቸው ብረታ ብረቶችን፣ አልሙኒየም እና ዲናሞ በመጠቀም እንደሰሩት ገልጸዋል።
የፈጠራ ስራው በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ሲሆን፤ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በሌለበት ቦታ በአነስተኛ ጀነሬተር በመጠቀም ስራ ሳይስተጓጎል ለመውቃት ያስችላል። በመሆኑም በገበሬው ማሳ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ስለማይኖር ገበሬዎች ለውሃ መሳቢያ የሚጠቀሙበትን ጀነሬተር በመጠቀም፤ የጀነሬተሩ ዲናሞ ላይ እየተሽከረከረ የሚፈለፍለውንና የሚወቃውን የማሽኑን ክፍል የሚያንቀሳቅሰውን ቺንጋ በመግጠም በቀላሉ የተለያዩ የእህል ዘሮችን ይወቃል፤ በቆሎን ይፈለፍላል እንዲሁም አገዳና ብዕሩን በመከትከት ለከብቶች መኖ ያቀናብራል።
ገበሬዎች ማሽኑን በቀላሉ እንደ ጋሪ እየገፉ ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ መጠቀም የሚችሉ ሲሆን፤ ነገር ግን ማሽኑን እየገፉ ለማንቀሳቀስ መልካ ምድሩ አመቺ ካልሆነ አራት ሰዎች በአራቱም አቅጣጫ ዳርና ዳር የተዘጋጀውን መያዣ በመጠቀም በቀላሉ ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ መጠቀም ይችላሉ።
አሰልጣኙ እንደተናገሩት፤ በተለያዩ አካባቢዎች ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ የህብረት ስራ ማህበራትን ለማሰልጠን እና ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠት ወደ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ገበሬዎች በደቦ 40 እና ከዚያ በላይ ሆነው በቆሎን በእጃቸው ሲፈለፍሉ ያስተውላሉ። እንዲሁም በአንዳንድ ቦታ ደግሞ በእጅ መፈልፈሉ አሰልቺና ከፍተኛ የሰው ኃይልና ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ፤ አንዳንድ ገበሬዎች በቆሎን በዱላ ሲወቁ ያታያሉ፡፡ በደቦ 40 ሆነው ሙሉ ቀን ሲፈለፍሉ ቢውሉም በዛ ቢባል ከ20 ኩንታል በላይ መፈልፈል አይችሉም ነበር።
በዱላ በሚወቁበት ጊዜ ደግሞ ምርቱ ከአፈር ጋር እየተቀላቀለ፣ እየተፈረካከሰና እየተበታተነ ምርት ይባክናል ጥራቱም ይቀንሳል። እንዲሁም ገበሬዎች ለድካምና ለእንግልት ይዳረጋሉ። በተጨማሪም በደቦ ስራው ለሚሰማሩ ሰዎች ምግብና መጠጥ ማቅረባቸውም ለከፍተኛ ወጪ ይጋለጣሉ ይላሉ።
ስለዚህ ይሄንን የአርሶ አደሩን ድካምና ኪሳራ በማስቀረት የሰው ኃይልና ወጪ በመቀነስ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚጨምር የፈጠራ ስራ ለምን አንሰራም በሚል ተነሳሽነት ይሄን የፈጠራ ስራ ለመስራት መነሳሳታቸውን የሚያስረዱት አቶ ግዛቸው፤ ይሄንን የፈጠራ ስራ በመጠቀም አንድ ወይም ሁለት ሰው ሰብሉን ማሽኑ ውስጥ በመጨመር በአንድ ሰዓት ውስጥ እስከ 40 ኩንታል መውቃትና መፈልፈል ያስችላል። ስለዚህ ገበሬው ጊዜና ወጪውን ቆጥቦ ምርትና ምርታማነቱን ከፍ እንደሚያደርገውም ነው የሚናገሩት።
እንዲሁም ገበሬው ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ የመሳሰሉትን እህሎች ከወቁ በኋላ ገለባውንና ተረፈ ምርቱን እዛው የወቁበት አውድማ ላይ ወዲያውኑ ሳያነሱት ጥለውት ይሄዳሉ። ይሄንን አገዳና ገለባ እንዲሁም ተረፈ ምርት እስኪያነሱት ድረስ አራትና አምስት እንስሳቶች የሚበሉትን በልተው ሌላውን ይረጋግጡታል። በዚህም ቢያንስ 50 እንስሳቶችን በቀላሉ መመገብ የሚችለው ይህ የከብቶች ቀለብ በትንሽ እንስሳቶች ተረጋግጦ ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ስለዚህ ማሽኑ ይሄንን በከንቱ የሚባክን የከብቶች ቀለብ በአግባቡ ለከብቶች ቀለብ ለማዘጋጀት ያስችላል።
በአጠቃላይ ማሽኑ የአርሶ አደሩን የአመራረት ዘዴ በማዘመን የምርት ሂደቱን የሚያፋጥንና ምርታማ የሚያደርግ፤ ለከብቶች ቀለብ በቀላሉ ለማዘጋጀት የሚያስችል የፈጠራ ስራ ከመሆኑ ባሻገር ለጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት የፈጠራ ስራውን አምርተው በመሸጥ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ያስችላል። እንዲሁም አንዳንድ የአርሶ አደር ልጆች ደግሞ ማሽኑን ገዝተው በእርሻ ማሳዎች አካባቢ በማከራየት የስራ እድል እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል የፈጠራ ባለሙያው።
የፈጠራ ስራውን ማንኛውም ሰው ምስሉን በማየት ወይም መመሪያውን አንብቦ በቀላሉ መጠቀም እንዲችል በሥዕል የተደገፈ ማንዋል የተዘጋጀ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ግዛቸው፤ ማሽኑ ሶስት ክፍል ያለው ሲሆን፤ እራሱን የቻለ የበቆሎ መፈልፈያ እና ሌላ ደግሞ እራሱን የቻለ የገብስ፣ የስንዴና የማሽላ መውቂያ እንዲሁም አገዳውንና ገለባውን በመከትከት ለእንስሳቶች መኖ የሚያቀነባብር ሌላ ሶስተኛ ክፍል ያለው መሆኑን ያስረዳሉ።
እርሳቸውም ስለማሽኑ አጠቃቀም እንደገለጹት፤ ማንኛውም ሰው በቆሎውን ወደ ማሽኑ ሲጨምር ማሽኑ ደግሞ በቆሎውን ፈልፍሎ በአንድ በኩል ሲያወጣ ቆሮቆንዳውንና ተረፈ ምርቱን ደግሞ በሌላ በኩል ያወጣል። እንዲሁም ስንዴ፣ ማሽላና ገብስ ሲወቃ ደግሞ እህሉን ወቅቶ በአንድ በኩል ሲያወጣ ተረፈ ምርቱን በሌላ በኩል ያወጣል። ስለዚህ ልክ እንደወፍጮ ቋቱ ላይ ጆንያ በመገደብ በቀላሉ ምርቱን በአንድ በኩል እንዲሁም በሌላኛው በኩል ደግሞ የከብቶቹን መኖ መቀበል ይቻላል በማለት ስለአጠቃቀሙ ያስረዳሉ።
‹‹እንዲሁም ስንዴ በሚወቁበት ወቅት ስንዴ የሚወቁበትን የማሽኑን ክፍል ይከፍታሉ። ስንዴውን ወቅተው ከጨረሱ በዛው የማሽኑ ክፍል ላይ ገብስና ማሽላ መውቃት ይችላሉ። ምክንያቱም ፍሬያቸው ተመሳሳይ ስለሆነ በአንድ ክፍል በተራ በተራ ስንዴን፣ ገብስንና ማሽላን መውቃት ይቻላል። ነገር ግን በቆሎ ለመፈልፈል ከተፈለገ የስንዴውን፣ የገብሱንና የማሽላውን ክፍል በመዝጋት የበቆሎ መፈልፈያ ክፍሉን በመክፈት መፈልፈል ይቻላል። ስለዚህ ገበሬዎቹ የሚሰሩት የሚወቃውን እህልና ለከብቶች ቀለብ የሚዘጋጀውን አገዳ ወይም ብዕር ማሽኑ ውስጥ የመጨመር ስራ ብቻ ነው።›› ይላሉ፡፡
እንደአሰልጣኙ ገለፃ፤ በአጠቃላይ በቀላሉ በማሽኑ ላይ የተገጠመውን ማስነሻ በመጫን መውቃት፤ ወቅቶ ሲጨርስ ደግሞ ማቆሚያውን በመጫን ማቆም ይቻላል። በህጻናት፣ በእንስሳትና ማሽኑን በሚጠቀሙት ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳያስከትል የማሽኑን አገዳ የሚከተክተው፣ የሚወቃው፣ የሚፈለፍለው እንዲሁም እነዚህን ክፍሎች የሚያንቀሳቅሰው ቺንጋ ጨምሮ በአጠቃላይ ሁሉም የማሽኑ ክፍል በላሜራ የታሸገ ስለሆነ፤ በሚሰራበት ወቅት በማንም ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የለም።
የፈጠራ ስራውን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 10 ሺህ ብር የፈጀባቸው ሲሆን፤ አሁን ላይ የመስሪያ ቁሳቁሶች ዋጋው በመወደዱ የማሽኑ ዋጋ ከዚህ ሊያሻቅብ እንደሚችል የተናገሩት ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ፤ ይሄንን ማሽን ከውጪ እናስገባ ቢባል ዋጋው 25 ሺህ ብር ነው። ነገር ግን ከውጭ የሚገባው ማሽን በቆሎን መፈልፈል ወይም ሌሎች እህሎችን መውቃትና አገዳውን ወይም ብዕሩን በመከትከት ለከብቶች መኖ ማቀነባበር ብቻ ነው። ይህ የፈጠራ ስራ ግን ሶስት አገልግሎቶችን ከመስጠቱም በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ያስቀራል።
የፈጠራ ስራውን ለመስራት የተለያዩ መረጃዎችን ከኢንተርኔት ላይ ለማግኘት የሚያስችል ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት በኮሌጁ አለመኖርና የፈጠራ ስራውን ለመስራት እንደግባት የሚያገለግሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለመግዛት የፋይናንስ ስርዓቱ ቢሮክራሲ የበዛበት መሆኑ፤ የፈጠራ ስራውን ለመስራት አስፈላጊ ቁሳቁሶች በወቅቱ ተገዝተው አለመቅረባቸው የፈጠራ ስራውን በወቅቱ ሰርተው ለማጠናቀቅ ተግዳሮት ሆኖባቸው እንደነበር አውስተዋል። እንዲሁም የህብረተሰቡን ትልቅ ችግር የሚቀርፍ ይሄንን የፈጠራ ስራ ሰርተው ለማህበረሰቡ ቢያበረክቱም፤ ነገ ላይ የተሻለ የፈጠራ ስራ ለመስራት የሚያስችል የትምህርት እድልና ድጋፍ አለመደረጉ ሌሎች ችግር ፈች የፈጠራ ስራዎችን ለመስራት ተነሳሽነት እንዳጡ ይጠቁማሉ።
ማሽኑ ወርድና ስፋቱ አንድ ሜትር በ70 ሴንቲ ሜትር እንዲሁም ቁመቱ አንድ ሜትር ከ20 ሴንቲ ሜትር እንደሆነ የሚናገሩት አሰልጣኙ፤ ማሽኑ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ እንዳይከብድና ሰፊ ቦታ እንዳይዝ ቁመቱን በማሳጠርና ስፋቱን በማጥበብ የፈጠራ ስራውን ለማሻሻል እንዳሰቡ ተናግረዋል። በዚህም አርሶ አደሩ ከቦታ ቦታ በቀላሉ ለማንቀሳቀስ አመች ከማድረጉ ባለፈ የፈጠራ ስራውን ለመስራት የሚወጣውን ወጪ ስለሚቀንስ፤ የማሽኑ ዋጋ ተሰርቶ ገበያ ላይ ሲቀርብ ይቀንሳል። ነገር ግን የሚደረግለት ማሻሻያ የማሽኑን የማምረት አቅሙንም ሆነ ፍጥነቱን እንደማይቀንሰው ይናገራሉ።
በአጠቃላይ ይሄንን የፈጠራ ስራ ከሰሩ በኋላ ያሉትን ክፍተቶች በማሻሻልና አዳዲስ እሴቶችን በመጨመር ለማህበረሰቡ ከዚህ በላይ ለመጠቀም ቀላልና አመቺ ከማድረግ ባሻገር፤ በፀሐይ ብርሃን አማካኝነት እንዲሰራ ለማድረግ ከኮሌጁ የኤሌክትሪካል ትምህርት ክፍል መምህራን ጋር በመነጋገር ላይ እንደሆኑ ነው አቶ ግዛቸው የገለፁት።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2011
ሶሎሞን በየነ