አዲስ አበባ፡- በጎነት ማለት ከራስ በላይ ማሰብና መስራት እንደመሆኑ በሌሎች መስዋዕትነት ምክንያት ቆሞ የሚሄደው የዛሬው ትውልድ የነገው ትውልድ የእርሱን መስዋዕትነት የሚፈልግ መሆኑን ተገንዝቦ መስራት እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
ሰባተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ትናንት በዘጠኝ ዘርፎች ለኢትዮጵያ ጉልህ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሰዎችና አንድ በልዩ ዘርፍ የሽልማት ሥነሥርዓት ተካሂዷል።
የዕለቱ የበጎሰው ሽልማት አሸናፊዎችን እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ጀምረው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ፕሬዚዳንቷ፤ በየዘርፉ ለአገር መልካም የሰሩ አስገራሚ የአገር ባለውለታዎች እንዳሉ ለማየት ያስቻላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ይሄን ዓይነት የአገር ባለውለታዎችና አስደናቂ ሰዎች ከመጋረጃ ጀርባ ያሉ መሆናቸውን በመጠቆምም፤ እነዚህን ማውጣት መማር እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በዚህ መልኩ ባለውለታዎችን ፈልጎ የሚያወጣው ይህ መርሃ ግብርም ለመጪው ትውልድ ጥሩ አርዓያነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ፤ አገር በትውልዶች ቅብብሎሽ የምትገነባ ናት። እስካሁን እየተገነባ ያለ እንጂ ተገንብቶ ያለቀ አገር የለም። እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን ግንባታ ባለፈው ትውልድ መሠረት ላይ እየገነባ ስለሚጓዝም ነው። ለአገሩ የሚያስብና ከራሱ ጥቅም በላይ የሚያይ ትውልድ የሚገነባው አገር ጠንካራ መሠረት ሲኖረው ነው። ቀጣዩም ትውልድ ጠንካራ አገር በጠንካራ መሠረት ላይ እየገነባ ይሄዳል።
«በጎነት ደግሞ ከራስ ጥቅም በላይ ማሰብና መስራት መቻል ነው» ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ዛሬ የሚሰራው ሥራ ከራስ ጥቅም አልፎ በተከታታይ የሚመጣው ትውልድ የሚኮራበትና የሚጠቀምበት ከሆነ የበጎ ሥራ ጎዳና ላይ መሆናችንን አመላካች እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ለኢትዮጵያ በየአውደ ግንባሩ ተዋግተው ነፃነትንና ክብርን በደማቸው ያቆዩን እናትና አባቶች ምን አግኝተው ይሆን፤ ብለው በመጠየቅም፤ እነርሱ በግል ካገኙት በላይ አገርና ሕዝብ ወደር የሌለው ጥቅም ማግኘታቸውን፤ በእነርሱ የነፃነት መስዋዕትነት መላው ጥቁር ሕዝብ መኩራቱን ተናግረዋል፡፡
ይህ ሁሉ በጎነት እንደመሆኑ ዛሬም ሁሉም በየተሰማራበት መስክ የሚሰራቸው ሥራዎች የግዴለሽነት ከሆኑ ጉዳቱ ለአገር ነው፤ አገር እየገነባን ሳይሆን እያፈረስን እንሄዳለን፤ በሌሎች እየተጠቀሙ መቀመጥ ሳይሆን የተሻለ ጠንካራ ሥራ መስራት ይገባል፤ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ጠንካራ ስራ ሳይሰሩ ጠንካራ አገር፤ ንጹህ ስራ ሳይሰሩ ንጹህ አካባቢ፣ ታላቅ ተልዕኮ ሳይፈጽሙ ታላቅ አገር ማሰብ ህልም መሆኑን በማውሳትም፤ በሌሎች መስዋዕትነት ምክንያት ቆመን እንደምንሄደው ሁሉ የነገው ትውልድ የእኛን መስዋዕትነት ይፈልጋል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በጎነት ማለት መስዋዕትነትን ለመቀበል መዘጋጀትና መቻል መሆኑን ተገንዝቦ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በሽልማት መርሃ ግብሩ፣ በመምህርነት ዘርፍ -ወይዘሮ ሕይወት ወልደመስቀል፤ በቅርስና ባህል ዘርፍ- አቶ አብዱልፈታህ አብደላ፤ በሳይንስ ዘርፍ -ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሴ፤ በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ – አቶ ነጋ ቦንገር፤ በመንግሥታዊ የሥራ ተቋማት ኃላፊነት ዘርፍ- አቶ ግርማ ወንዳፍራሽ፤ በበጎ አድራጎት ዘርፍ -ዶክተር አብዱላዚዝ ኢብራሂም አሸናፊ መሆናቸው ይፋ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ በኪነጥበብና ፎቶግራፍ ዘርፍ- አቶ በዛብህ አብተው፤ በሚዲና ጋዜጠኝነት ዘርፍ- አቶ አማረ አረጋዊ፤ በዳያስፖራ ዘርፍ- አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ እንዲሁም በልዩ ዘርፍ ተሸላሚ ዘርፍ የጋሞ አባቶች ሽልማታቸውን ተረክበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 27/2011
ጽጌሬዳ ጫንያለው