አዲስ አበባ፡- የትግራይ ወጣት ሴቶች ነፃነትና ክብራቸውን የሚገልጹበት የአሸንዳ በዓል ከመቐለ እስከ አዲስ አበባ በፍቅርና በወንድማማችነት ሲከበር በፈቃድና በውዴታ ደስ በመሰኘት ብቻ ሳይሆን፤ በዓሉን የሚያከብሩት ለአዲስ አበባ ውበትና ተጨማሪ እሴት በመሆኑ እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ተናገሩ። በዓሉ በየዓመቱ ሲከበር የከተማ አስተዳደሩ ሙሉ ድጋፉን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ምክትል ከንቲባ ታከለ፤ በአዲስ አበባ ሚሊኒዬም አዳራሽ በተካሄደ የትግራይ አሸንዳ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ የአሸንዳ በዓል የትግራዋይ እናቶች የጽናትና የጥንካሬ፣ የትግራይ ወጣት ልጃገረዶች በአንድነታቸው ደምቀውና አሸብርቀው በአደባባይ ነፃነታቸውንና ክብራቸውን በአደባባይ ለዓለም የሚያሳዩበት ነው፡፡ በዓሉ በአዲስ አበባ ሲከበርም በፈቃደኝነትና በወንድማማችነት ሲሆን፤ በዚህ መልኩ መከበሩም ለአዲስ አበባ ተጨማሪ ውበትና እሴት የሚሆን ነው፡፡
እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ፤ የአክሱምን ሐውልት ሰርተው ያቆሙ፣ አባቶችና እናቶችን፣ የአሸንዳን ባህልና በዓለም በዚህ ደረጃ ትውልድ ተሻግሮ ማንነቱንና ባህሉን ሳይጥስ ዛሬ ላለው ትውልድ ላደረሱ ሁሉ ክብርና ምስጋና ይግባ ቸው፡፡ በዚህ መልኩ ተጠብቆ የቆየውና ለከተማዋም ተጨማሪ ድምቀት የሆነው የአሸንዳ በዓል በየዓመቱ ሲከበር የከተማ አስተዳደሩ ሙሉ ድጋፉን ያደር ጋል፡፡
«አሸንዳ ውብ ነው፣ ድንቅ ነው፣ ጥበብ ነው» ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ በዓሉ «ሴት እህቶቻችን ማንነታቸውንና ክብራቸውን የሚገልጹበት፤ የተጣሉትን የሚያስታርቁበት፤ ስለ አገራቸው ያላቸውን ክብር በአደባባይ የሚገልጹበት፤ እርቅና አንድነትን የሚሰብኩበት፤ በአለባበሳቸው አጊጠው በጭፈራቸውም ከፍ ብለው ለሕዝብ የሚታዩበት ነው» በማለት አብራርተዋል፡፡ ይህ ባህል በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በዓለም ደረጃ እውነታዎችን እያዘጋጀን ማስተዋወቁን እንደሚቀጥሉም ተናግረ ዋል፡፡
አሸንዳ የትግራዋይ እህቶቻችን በዓል ቢሆንም፤ የኦሮሞው፣ የአማራው፣ የጉራጌው፣ የስልጤው…፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ባህል በመሆኑ እንንከባከበ ዋለን፤ ለትውልድም እናስተላልፈዋለን ሲሉም ቃል ገብተዋል፡፡
ከአሸንዳ ባለፈም እንደ እሬቻ፣ አሸንድዬና ፊቼ ጨምበላላን የመሳሰሉ የሁሉንም ሕዝብ ባህሎች ለአዲስ አበባ ተጨማሪ እሴትና ሀብት ብሎም ተጨማሪ ውበት ስለሆኑ በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ በማገዝና በማደራጀት በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ተወላጅ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ሁልጊዜ የምታደርጉት መልካም ሥራ፤ ሁል ጊዜ የምታከናውኑት አገርን የሚያኮራ የአንድነትና የመተባበር ሥራችሁን በዚሁ ሁኔታ እንዲያስቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በዓሉ በአዲስ አበባ በደመቀ መልኩ እንዲከበር ላደረጉት ድጋፍ የትግራይ ሴቶች ማህበር የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የምስጋና ስጦታ አበርክተውላቸዋል::
አዲስ ዘመን ነሃሴ 27/2011
ወንድወሰን ሽመልስ