አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለሦስት ዓመታት የዘገየውን የዋና መስሪያ ቤት የባለ 32 ፎቅ ሕንፃ ግንባታ በመጪው ዓመት በሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ ለማስጀመር ማቀዱን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ የዋና መስሪያ ቤቱ ሕንፃ የሚያርፍበት ቦታ ላይ ካሳ የተከፈላቸው ሰዎች ከቦታው ሊነሱ ባለመቻላ ቸው የሕንፃው ግንባታ ሦስት ዓመታት ሊዘገይ ችሏል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ለሰዎቹ ምትክ ቦታ ስለተሰጣቸውና አስተዳደሩ በሁለት ሳምታት ውስጥ ቦታውን ለማስረከብ ቃል ስለገባ በመጪው ዓመት የሕንፃ ግንባታው ይጀመራል፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት የሕንፃው ዲዛይን ተሰርቶ በሁለት ነጥብ 89 ቢሊዮን ብር ለማስገንባት ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም የከተማ አስተዳደሩ ቦታውን በወቅቱ ማስረከብ ባለመቻሉ ሕንፃ ግንባታው ለሦስት ዓመታት እንደተጓተት ገልጸው የግንባታው መዘግየትም ድርጅቱን ለተጨማሪ የግንባታ ወጪና ጊዜ እንደዳረገው ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ ራስ ሆቴል ፊት ለፊት ባለው ቦታ ላይ በመጪው ዓመት የመጀመሪያ ወር ላይ ለሚያስገነባው ሕንፃ ተቋራጩን ለመለየት ጨረታ እንደሚያወጣና የሕንፃ ግንባታውንም እንደሚጀመር፤ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥም እንደሚጠናቀቅ አቶ ነፃነት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት 102 ቅርጫፎች ያሉት ሲሆን ከ137ሺ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞቹም የተለያዩ የመድን ዋስትና አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 27/2011
ጌትነት ምህረቴ