ከትናንት በስቲያው ቅዳሜ የዱከም ጤና ጣቢያ ግጥር ግቢ በታካሚዎች ተጨናንቋል፡፡ በሕክምና ክፍሎቹ በረንዳ ላይ የተሰለፉ ታካሚዎች ስማቸው እየተጠራ ወደ ሕክምና ክፍሉ ውስጥ ዘልቀው ይገባሉ፡፡ የጥርስ፣ የወገብና፣ የነርቭ ህመም ያለባቸው ታካሚዎች በነፃ ሕክምና እያገኙ ሲወጡ ተመልክተናል፡፡
ባለቤትነቱ የደቡብ ኮሪያ የሆነውና በዱከም የሚገኘው ኢኮስ (EKOS) የብረታብረት ፋብሪካ አስተባባሪነትና ድጋፍ ከደቡብ ኮሪያና ከኮሪያ ሆስፒታል በመጡ 22 የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን በዱከም ጤና ጣቢያ ለኅብረተሰቡ ነፃ የሕክምና አገልግሎት በመሰጠት ላይ ነው፡፡
የዱከም ነዋሪ የሆኑት አቶ ሲሳይ ኢሮ በኮሪያ የሕክምና ቡድን ነፃ ሕክምና ይሰጣል ተብሎ በማስታወቂያ ሲነገር ሰምተው የጥርስ ህመማቸውን ለመታከም እንደመጡ ገልጸውልናል፡፡ በገንዘብ ችግር ምክንያት ህመማቸውን ችለው ለወራቶች እንደቆዩ አስታውሰው ‘በኮሪያ የሕክምና ባለሙያዎች ነፃ ሕክምና ይሰጣል’ ሲባል ጊዜ ሳያጠፉ ወዲያው የተቦረቦረ ጥርሳቸውን ለማስወለቅ ወደ ጤና ጣቢያው እንደመጡ ነግረውናል፡፡
የሕክምና ባለሙያዎቹ አገልግሎት አሰጣጥና ትህትና በጣም እንደማረካቸውና ጥርሳቸውን በቀላሉና ስቃይ በሌለበት ሁኔታ እንዳወለቁላቸው ገልጸዋል፡፡ «በጣም የሚገርመው» አሉ አቶ ሲሳይ «ከሦስት ዓመት በፊት አንድ ሺ ብር ከፍዬ ጥርሴን አስወልቄያለሁ፡፡ በጣም ህመም ነበረው፡፡
ህመሙና የክፍያው መብዛት ብቻ ሳይሆን የጊዜ ቀጠሮውና እንግልቱም ቀላል አይደለም፡፡ በአንጻሩ የኮሪያዎቹ የሕክምና ባለሙያዎች የተጎዳውን ጥርስ ሲያወልቁ ህመም የለውም፤ ደምም አይፈስም፤ በጥቅሉ ዘመናዊ ሕክምና በነፃ ነው ያገኘሁት» ሲሉ ደስታቸውን አጋርተውናል፡፡
«ተፈልጎ የማይገኝ ዕድል ነው ያገኘሁት» የሚሉት አቶ ሲሳይ ጥርስ ለማስነቀል በትንሹ ሦስትሺህና ከዚያ በላይ ብር ያወጡ እንደነበር አመልክተው በኢኮስ አማካኝነት በነፃ ሕክምና መሰጠቱ ፋብሪካው የኅብረተሰቡን ችግር ለመጋራት ያለውን እንቅስቃሴ አጎልቶ ያሳያል ብለዋል፡፡
ሌላዋ ሕክምናውን አግኝተው ከጤና ጣቢያው ግቢ ሲወጡ ያገኘናቸው ወይዘሮ ፀሐይ ማህመድ ወገባቸውና እጃቸውን ለማንቀሳቀስ ሲቸገሩ እንደነበር አውስተው ሕክምናውን ከአገኙ ወዲህ ግን ማንቀሳቀስ መቻላቸውን፤ ሕክምናው ከዚህ በፊት አይተዋቸው በማያውቋቸው ዘመናዊ መሣሪያዎች መደግፉና በአጭር ጊዜም ውጤት ማየታቸውን ነግረውናል፡፡ በነፃ የተሰጣቸው የፊዚዮ ቴራፒ አገልግሎት ከገንዘብና ከእንግልት አኳያ ሲታይ በጣም የሚያስደስት እንደሆነ መስክረዋል፡፡
«ከሕክምናው በላይ የሚያስደስተው የሕክምና ባለሙያዎቹ ትህትና ነው» የሚለው ወጣት ከሊል ፊጤንሳ «የወገብ ሕክምና በዘመናዊ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ አገልግሎቱን አግኝቻ ለሁ፡፡
በጤና ጣቢያው የማይሰጡ የሕክምና ዓይነቶች ከአቅራቢያችን በሚገኘው ኢኮስ ብረታ ብረት ፋብሪካ አማካኝነት በነፃ በጤና ጣቢያው አገልግሎቱ ለገጠሩና አቅም ለሌለው ኅብረተሰብ ክፍል መሰጠቱ ከምንም በላይ ያስደስታል፡፡ ቀዬህ ድረስ መጥተው አገልግሎቱን ስታገኝ እርካታ ነው የሚሰማህ» ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።
ከሊል ልክ እንደ ኢኮስ ሁሉም ተቋማት ለኅብረተሰቡ በተለያዩ መስኮች ድጋፍ ቢያደርጉ ድርጅቶቹንና ማህበረሰቡን በማቀራረብ በኩል ለተሻለ ዕድገት እንዲሰሩ የትስስር ገመድ ይሆናቸዋል የሚል አቋም አለው፡፡
የነርቭ፣ ፊዚዮቴራፒ እና የጥርስ ሕክም ከጤና ጣቢያው አቅም በላይ በመሆናቸው እንደማይሰጡ የሚገልፁት የዱከም ጤና ጣቢያ ዳሬክተር አቶ ታምራት ማሞ በኢኮስ ድጋፍና አስተባባሪነት እነዚህ ሕክምናዎች ለኅብረተሰቡ በአቅራቢያው መሰጠታቸው ኢኮስንም ሆነ ባለሙያዎቹን ሊያስመሰግናቸው የሚገባ ተግባር ነው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የፊዚዮቴራፒና የነርቭና የጥርስ ሕክምናዎች በቀላሉ የሚገኙ አይደሉም፡፡ ዋጋቸውም ውድ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ አንድ ጥርስ ለመትከል 20ሺ ብር ወጪን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አኳያ እነዚህ ሕክምናዎች ለኅብረተሰቡ በነፃ መሰጠታቸው ትልቅ እገዛ ነው፡፡ የቡድኑም እዚህ መምጣትና ይህን ዓይነቱን ዘመናዊ አገልግሎት መስጠቱ የጤና ጣቢያው የሕክምና ባለሙያዎች የልምድና የእውቀት ልውውጥ እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል፡፡
በኢኮስ ብረታ ብረት ፋብሪካ የማስታወቂያና የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሚስተር ሊሂንግ እንደገለጹት ፋብሪካው ከኮሪያ ሆስፒታል ጋር በመተባበርና ከውጭ የሕክምና ባለሙያዎችን በማስመጣት ፋብሪካው የሚገኝበት የዱከም ነዋሪ የነፃ ሕክምና ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ይህም ፋብሪካው ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ፋብሪካው ድጋፍ የሚሰጠው ነፃ ሕክምና የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም ቀጣይነት እንደሚኖረው የገለፁት ኃላፊው ለአራት ቀናት የሚሰጠው የነርቭ፣ የፊዚዮ ቴራፒ፣ የስኳር፣ የጥርስ ነቀላና ተከላ የነፃ ሕክምና አገልግሎቶች ከአንድ ሺ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
ሚስተር ሊሂንግ የነፃ ሕክምና አገልግሎቱ በጅማ፣ ድሬዳዋና ሐረር ለመስጠትም ዕቅድ መኖሩን ጠቁመው፣ ፋብሪካው ዱከም አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኙ 38 አርሶ አደሮች የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ለማድረግ ተቋማቸው ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ለአካባቢው ኅብረተሰብ የውሃ አቅርቦትን ለማሟላትና የቴኳንዶ ስልጠናም ለመስጠት ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያና ኮሪያ በደም የተሳሰረ ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት ኃላፊው ፋብሪካው ከኢትዮጵያና ኮሪያ ረጅም ግንኙነት መገለጫዎች አንዱ እንደሆነ፤ ወደፊትም ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በመሆን በማህበራዊ አገልግሎቶች ዘርፍ ላይ አተኮሮ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 27/2011
ጌትነት ምህረቴ