– ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ኮሚሽን በ2011 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ባጋጠሙት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች አምስት ቢሊዮን 314 ሚሊዮን 225ሺ 550 ብር የሚገመት ንብረት ማዳኑን አስታወቀ፡፡ በበጀት ዓመቱ በደረሰው አደጋም ከ230 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡
በኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ስለሺ ተስፋዬ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ በተጠቀሱት ስፍራዎች 525 የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ ከአደጋዎች መካከል 363 ያህሉ ቃጠሎ ሲሆኑ 162 የሚሆኑት ደግሞ ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ናቸው፡፡ ከአደጋዎቹ ውስጥ 43 በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ሲከሰቱ የተቀሩት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰቱ ናቸው፡፡
በበጀት ዓመቱ ባጋጠሙት የእሳት አደጋዎች 230 ሚሊዮን 8መቶ 33ሺ 300 ብር የሚገመት ንብረት የአደጋው ሰለባ መሆኑን የገለፁት አቶ ሽመልስ፤ ኮሚሽኑ በደረሰው ድንገተኛ ጥሪና ባደረገው ፈጣን የመከላከል እርምጃም ሦስት ቢሊዮን 379ሚሊዮን 875ሺ 550 ብር የሚገመት ንብረትን ከቃጠሎ ለማዳን ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ባጋጠሙ 162 ድንገተኛ አደጋዎች 239 ሚሊዮን 903ሺ ብር የሚገመት ንብረት ለውድመት የተጋለጠ ሲሆን ከዚህ መሀልም ግምቱ ዘጠኝ ሚሊዮን 70ሺ ብር ገደማ የሚገመት ንብረትን ደግሞ ሰለባ ከመሆን ለማትረፍ መቻሉን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 525 የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ቢመዘገቡም ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባና ኦሮሚያ ውስን ዞኖች በደረሰው ድንገተኛ ጥሪና ባደረገው ፈጣን ምላሽ በአጠቃላይ አምስት ቢሊዮን 314 ሚሊዮን 225ሺ 550 ብር የሚገመት ንብረትን ከአደጋው ለማትረፍ ተችሏል፡፡
አደጋው ከአምናው ተመሳሳይ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር በእሳት ቃጠሎ 33 በመቶ ጭማሪ ሲታይ በሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ደግሞ ቁጥሩ በ41 በመቶ መቀነሱን አስታውቀዋል፡፡
እንደባለሙያው ከሆነ፤ በ2011 በጀት ዓመት በደረሱ የእሳት ቃጠሎዎች የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉንና 81 በሚሆኑት ላይም የአካል ጉዳት አጋጥሟል፡፡ ከደረሱ 363 የእሳት ቃጠሎዎች መካከል ደግሞ 124 የሚሆኑት በመኖሪያ ቤቶች ላይ የተከሰቱ ናቸው፡፡
በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ ድንገተኛ አደጋዎች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በተቆፈሩ ጉድጓዶችና ወንዞች ውስጥ ከመግባት ጋር ተያይዞ የደረሱ 32 አደጋዎች ሲሆኑ 19 ሰዎች ኩሬ ውስጥ በመግባት ሕይወታቸውን እንዳጡ ተረጋግጧል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታም በኮንስትራክሽን፣ በሊፍት፣ በአፈር መደርመስና መሰል አደጋዎች 24 ሰዎች ሲሞቱ 29 የሚሆኑት ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ኮሚሽኑ በቅርብ ጊዜ በ171 ሚሊዮን ብር 26 ዘመናዊ የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪዎችን ስለመግዛቱ ያስታወሱት አቶ ሽመልስ፤ በቀጣይም በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያው የሚጋጥሙ ከባድ የእሳት አደጋዎችን በሄሊኮፕተር ለመቆጣጠር የሚያስችል ዕቅድ ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2011
መልካምስራ አፈወርቅ