
– በአዲስ አበባ ለግንባታ የሚውል 100 ሄክታር መሬት ይፈልጋል
አዲስ አበባ፡- የክላስተር ህንፃዎችን ለማደስ 100 ሚሊዮን ብር ወጪ የማድረግ ዕቅድ እንዳለው የአዲስ አበባ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ክላስተር ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡ በበጀት ዓመቱ ለግንባታ የሚውል 100 ሄክታር መሬት ለመረከብና 79ነጥብ3 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሺቅ በድሩ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ኮርፖሬሽኑ በ2012 በጀት ዓመት በከተማዋ ለሚገኙ 127 ህንፃዎች ዕድሳት የሚውል 100 ሚሊዮን ብር ወጪ ያደርጋል፡፡ ህንፃዎቹ ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት የሰጡ በመሆናቸው ከመሠረተ ልማት ማሟላት ጀምሮ ዕድሳት ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
እንደ አቶ አሺቅ ገለፃ፤ በኮርፖሬሽኑ ስር ካሉ 127 ህንፃዎች አብዛኞቹ ፍሳሽ መስመር መበላሸት፣ የተቀባው ቀለም መወየብና እንዲሁም የክላስተሮች ተረፈ ምርት አወጋገድ ዘመናዊነት የጎደለው በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል፡፡ በተጨማሪም የትራንስፎርመሮች ቅያሬና ለአደጋ በማያጋልጡ ሥፍራዎች መትከል፣ ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመሮችን ማደስና ብሎም ህንፃዎቹን ለሥራ አመቺ በሆነ መንገድ ማስተካከል ስለሚያስፈልግ ለዕድሳቱ 100 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡
የከተማዋ ዕድገትና የአባላት ፍላጎትም በየወቅቱ እያደገ በመምጣቱ ኮርፖሬሽኑ የመስሪያ ህንጻዎችን በራሱ ወጪ ገንብቶ ለተጠቃሚዎች የማስተላለፍ እቅድ እንዳለው ያብራሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ለማስፋፊያና አዳዲስ ግንባታዎችን ለማከናወን ለ2012 በጀት ዓመት በጥቅሉ 100 ሄክታር መሬት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
‹‹በከተማዋ የመሬት ጥበት መኖሩን እንገነዘባለን፡፡›› ያሉት አቶ አሺቅ፤ መንግስት ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች በሳይንሳዊ መንገድ ለመምራት የወሰነ በመሆኑ ተገቢውን ካሳ በመክፈል መሬት የማግኘት ዕድል መኖሩን አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም ዘርፉ አገሪቱ ለወጠነችው የምጣኔ ሀብት ዕድገት የጀርባ አጥንት በመሆኑ ትኩረት እንደተሰጠው አመልክተዋል። አርሶ አደሮችም ሆኑ የልማት ተነሺዎች በዘላቂነት ሕይወታቸውን የሚመሩበት ብሎም ከኮርፖሬሽኑ የሥራ እንቅስቃሴ ጋር የተናበበ ሕይወት እንዲኖራቸው በትኩረት እንደሚሰራም አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ አሺቅ ከሆነ፤ የተቋሙ ስትራቴጂክ እቅድ በ2009 ዓ.ም ተዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን፣ አሁን መቀየር እንዳለበት ታምኖበታል፡፡ በተቋሙ በዓመት ከሚነሱ
የመልካም አስተዳደር ችግሮች ውስጥ 80 በመቶ ለሚሆኑት እልባት የመስጠት ውጥን ተይዟል፡፡ በተጨማሪም 16 ክላስተር ማዕከላት የይዞታ ማረጋገጫ መረከብና ከፕላን ጋር ተቃርኖ ያላቸውን ይዞታዎች ህጋዊ መስመር እንዲይዙ ያደረጋል፡፡ 22 የክላስተር ማዕከላትም ጥበቃ እንዲደረግላቸው ውጥን ተይዟል፡፡
32ሺ61 ካሬ ሜትር ክፍት ቦታ ለአምራቾች የማስተላለፍ እቅድ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ከይገባኛል ነፃ የሆነ 93ነጥብ3 ሄክታር መሬት በመረከብ ለተገቢው ሥራ የእንዲውል ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም 158ሺ742 ካሬ ሜትር ላይ ቫትን ሳይጨምር 79ነጥብ4 ሚሊዮን ብር የመሰብሰብ እቅድም ተይዟል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለፃ፤ የሰሠው ኃይልና መሠረተ ልማት ባለመሟላታቸው ያልተላለፉ ህንፃዎች መኖራቸውን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ከሌሎች ተቋማት ጋር በሚፈጥረው ቅንጅታዊ አሠራርን ይጠይቃል፡፡ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ አመለካከትና ሌሎች ችግሮች ተቋሙን እየተፈታተኑት ነው፡፡
ለዚህም በክላስተር አስተዳደርና ልማት በአገር ውስጥ የካበተ ልምድ ባለመኖሩ ከውጭ አገር ልምድ የመቅሰም ውጥን ተይዟል፡፡ ተቋሙ የአደረጃጀትና የአሰራር ማንዋሎችና የሥራ መመሪያዎች ላይ ክፍተት ያለበት በመሆኑ ተቋሙ መፍትሄ ያበጃል ብለዋል፡፡
ወየአዲስ አበባ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ክላስተር ልማት ኮርፖሬሽን በ2009 ዓ.ም የተቋቋመ የከተማ አስተዳደሩ የልማት ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር