
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ200 ሺ በላይ የሚሆኑ የቫት (ካሽ ሬጂስተር) ማሽኖች ጊዜ ያለፈባቸውና ለማጭበርበርም ክፍት በመሆናቸው በአዲስ ቴክኖሎጂ ሊቀይራቸው ጥረት እያደረገ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር እና የገቢዎች ሚኒስቴር ከክልል የዘርፉ ኃላፊዎች ጋር ትናንት ውይይት ባደረጉበት ወቅት የገቢዎች ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በእያንዳንዱ ነጋዴ እጅ ያለው የቫት ማሽን ለደረሰኝ ማጭበርበር እና ለአሰራር ክፍተት እያጋለጠ ይገኛል። በመሆኑም ማሽኑን በአዲስ ቴክኖሎጂ መቀየር አስፈላጊ ሆኗል። ያደጉ አገራት የሚጠቀሙባቸውን የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እና ዘመኑ የሚጠይቃቸው አሰራሮችን የያዘ ቴክኖሎጂ በቀጣይ እንዲተገበር ጥናት እየተደረገ ይገኛል።
የቫት መሳሪያውን ለመቀየር የሚደረገው ጥረት እስኪጠናቀቅ ድረስ በማሽኑ አማካኝነት የሚሰሩ ህገወጥነቶችን መከላከል የሁሉም ክልሎች እና መስተዳድሮች ኃላፊነት መሆኑን ወይዘሮ አዳነች አሳስበዋል። በተለይም በስራ ላይ የሚገኙ እና ስራ ያቆሙ ማሽኖችን በመለየትና ስለሃሰተኛ ደረሰኝ ማጭበርበሮች የኢንተለጀንስ ስራ በማጠናከር ልየታ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በዚህ ረገድ የፌዴራልና የክልል ቢሮዎች በቅንጅት መረጃ እየተለዋወጡ በመስራት ችግሩን ሊከላከሉ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ገዙ በበኩላቸው፤ አሁን ያለው የቫት ማሽን ምናልባትም ከኋላቀርነቱ የተነሳ በኢትዮጵያ ብቻ እያገለገለ የሚገኝ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ቴክኖሎጂው ከ20 ዓመታት በፊት ህንድ ሀገር ጥቅም ላይ የነበረና ለደረሰኝ ማጭበርበር ክፍት የሆነ አሰራርን የያዘ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በዚህም መሰረት በርካታ ነጋዴዎች በሶፍትዌር የታገዘ የቫት ደረሰኝ ማጭበርበር ድርጊቶችን ሲፈጽሙበት መያዛቸውን አመልክተዋል፡፡ በየጫት ቤቶቹ እና በየጉራንጉሩ በጥቅም ግንኙነት የተሳሰሩ ነጋዴዎችም ሃሰተኛ ማሽኖችን በመጠቀም የውሸት ደረሰኞችን ሲቆርጡበት እንደነበርም አልሸሸጉም፡፡
እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ፤ በክልልና በፌዴራል ደረጃ ከተመዘገቡ የቫት ማሽኖች ውስጥ በስራ ላይ ስለመሆናቸውና ስላለመሆናቸው የማይታወቁ በርካታ መሳሪያዎች አሉ። አንዳንዶቹም በነጋዴው እጅ ሆነው የሃሰት ደረሰኝ ይሰራባቸዋል። በዚህ ረገድ ከነጋዴ እጅ 500 እንዲሁም ከአቅራቢዎች ላይ ደግሞ 250 የቫት ማሽኖች መጥፋታቸው ታውቋል።
በዚህም ምክንያት በየጊዜው የሚከሰተው የታክስ ይቀነስልኝ እና የደረሰኝ ማጭበርበር ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ለአብነት በ2011 በጀት ዓመት ግብር ካሳወቁ 25ሺ523 ነጋዴዎች መካከል 8ሺ702ቱ ኪሳራ ውስጥ ነን ብለው አሳውቀዋል። በመሆኑም ጉዳዩ የተከሰተው በራሳቸው ወይም በሌሎች ነጋዴዎች የደረሰኝ ማጭበርበር ምክንያት መሆኑን በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል።
የሶማሌ ክልል የገቢዎች ቢሮ ዋና አማካሪ ሙሄዲን አብዲ እንደገለጹት፤ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች የወጡ ሰዎች ጭምር በቫት ማሽኖቹ አማካኝነት የደረሰኝ ማጭበርበር ስራ ላይ ስለመሳተፋቸው ማስረጃ ተገኝቷል። የቫት ማሽኖቹን ደረሰኝ ይዘት በመውሰድ እስከውጭ አገራት አሳትመው የሚያመጡ አጭበርባሪዎች ተይዘዋል።
በሶማሌ ክልል 8ሺ የቫት ማሽኖች መመዝገባቸውን የተናገሩት አቶ ሙሄዲን፤ ይሁንና ነጋዴዎች ግብራቸውን እያሳወቁ የሚሰሩት ግን በሶስት መቶ የቫት ማሽኖች ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት የቫት ደረሰኝ የያዙ ነገር ግን ትክክለኛውን ግብይት ሳይሆን እንደፈለጉ ዋጋ በማስተካከል የሚቆረጡ ደረሰኞች ወደመንግስት ቢሮ በየጊዜው ይደርሳሉ። በመሆኑም ችግሩን ለመከላከል የማሽኖቹን ቴክኖሎጂ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ሁሉ እስከዚያው ድረስ ግን ሃሰተኛ ደረሰኞችን እያመሳከሩ የመለየት ስራው እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2011
ጌትነት ተስፋማርያም