
አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጃፓን የቶሺባ ኢነርጂ ሲስተም ሶሉሽንስን መጎብኘታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቲካድ 7 ጉባኤ ላይ መሳተፋቸውም ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጃፓን የቶሺባን ኢነርጂ ሲስተም ሶሉሽንስ ፋብሪካ በጎበኙበት ወቅት በእንፋሎት ተርባይ የማምረቻ ጣቢያው ላይ ስለሚከናወኑ ሥራዎች ገለፃ የተደረገላቸው መሆኑ ተጠቁሟል። በጉብኝቱም የቶሺባ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት፤ በተለይም በጂኦተርማል ኢነርጂ ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጥሪ ማቅረባቸውን የፅህፈት ቤቱ መረጃ ጠቁሟል።
በተያያዘ መረጃም የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እና የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በቲካድ 7 ጉባዔ መሳተፋቸው ተጠቁሟል።
ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በተሳተፉበት የቲካድ 7 ልዩ የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና መረጋጋት ጉባኤ ላይ ዶክተር አብይ አሕመድ በቀጣናው ስላለው የሰላምና መረጋጋት ለውጥ አንስተው የአካባቢው አገራት መሪዎች በዘላቂ ሥራ ፈጠራ ላይ እንዲያተኩሩ ጥሪ ማቅረባቸው ታውቋል::
በተጨማሪም ለዘላቂ ሰላም ምሰሶ በሆነው የመደመር እሳቤ ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት መነሳት አስፈላጊ መሆኑን አስመልክቶ ንግግር ማድረጋቸውን ከፅህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል::
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2011
ምህረት ሞገስ