
አዲስ ዘመን።- የአገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች፣ በየአካባቢው ያሉ በግለሰብ የሚመሩ የወጣት ኢመደበኛ አደረጃጀቶች ተቋማዊ እንዲሆኑ ስርዓት ካልተበጀላቸው ለአገር ከፍተኛ አደጋ እንደሚሆኑ ተጠቆመ።
የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ መንግስት በቅንነት ሽማግሌዎችን እና የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትን እያቀረበ ነው። አንዳንድ የምሁራን ማህበር እየተባሉ ኢመደበኛ በሆነ መልኩ የሚሳተፉ አሉ።
በተለያዩ አካባቢዎች ሌሎችም መደበኛ ያልሆኑ የወጣት አደረጃጀቶች አሉ። ወደፊትም ሌሎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ነገር ግን ከማናቸውም አደረጃጀቶች ጀርባ የግለሰቦች ፍላጎቶች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም። ያንን መዘወር የሚፈልጉ የፖለቲካ ሃይሎች ይኖራሉ። እነዚህ አደረጃጀቶች ከጠነከሩ ማዕከላዊ መንግስቱ ያዳክማሉ።
ዶክተር የሺጥላ፤ “የሃይማኖት ተቋማት ስራቸው በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተው መነገድ እና ማትረፍ አይደለም” ካሉ በኋላ፤ የሃይማኖት ተቋማት ሥራቸው መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት ነው።
የሃይማኖት ሚና የማህበረሰቡን የሞራል እሴት ጠብቆ ታማኝ ዜጋ ለመፍጠር ትልቅ ሚና መጫወት ቢሆንም፤ ይህንን መስመር አልፎ ወደ ፖለቲካው ወደ ኢኮኖሚያዊ ወደ ሌሎች ተሳትፎዎች እግራቸውን እያስገቡ ነው። ይህ ደግሞ የጎራ መደበላለቅ እና የፍላጎት ግጭት ያስነሳል ብለዋል።
የሃይማኖት መሪዎች ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ካልቻሉ ሃይማኖቱን እንደመሳሪያ ተጠቅመው ‹‹መንግስት እኛ ላይ ይሄን ስላደረገ እና ጫና ስላሳደረብን›› እያሉ ህዝቡን ተነሳ ይላሉ። ይህ የሃይማኖት ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል። የባህል ተቋማት የማንነት ግጭት ለማስነሳት እንደሚገፋፋት ሁሉ የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ደግሞ የሃይማኖት ግጭትን ሊያስነሳ ይችላል ብለዋል።
ስለዚህ የተወሰኑ የልሂቃን ግለሰቦችን ፍላጎት ለማሳካት የተደራጁ ኢ መደበኛ አደረጃጀቶች ግባቸው መንግስትን በማስገደድ የሚፈልጉትን ዓላማ ማስፈፀም ላይ በመሆኑ፤ ይሄ በደንብ ትኩረት ተሰጥቶት ሊታሰብበት እንደሚገባ አመልክተዋል።
እነዚህ ኢመደበኛ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ አደረጃጀቶች በምንም መልኩ በፖለቲካው እና በኢኮኖሚው ውስጥ መግባት የለባቸውም። ይህንን ለመከላከል ተቋማዊ አሰራር ሊዘረጋላቸው እንደሚገባም ዶክተር የሺጥላ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2011
ምህረት ሞገስ