445 ሚሊየን ብር በጀት የተያዘለት የቃሊቲ መናኸሪያ የግንባታ ስራ በቅርቡ የሚጀመር መሆኑ ተገለፀ።
የቃሊቲ መናኸሪያ የግንባታ ስራ በዘንድሮው በጀት ዓመት 184 ሚሊየን ብር በመመደብ ወደ ስራ ሊገባ መሆኑን የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ባለስልጣን አስታውቋል።
በተለያዩ ጊዜያት የግንባታ ስራው ይጀመራል እየተባለ ዛሬም እልባት ያላገኘዉ የቃሊቲ መናኸሪያ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች፣ አሽከርካሪዎች እና ተሳፋሪዎችን ለተለያዩ ችግሮች ሲዳርግ ቆይቷል።
ለአመታት የተስፋ ስንቅ ከመሆን ያለፈ ዛሬም ፍሬW አልታየንም የሚሉት የችግሩ ተጠቂዎች፥ ችግሩን እንቀርፋለን የሚሉ አካላትም ከቃል መግባት የዘለለ ምንም ተግባር አለመፈፀማቸውን ይናገራሉ።
የችግሩ ተጠቂዎች ቅሬታ መሰረት በማድረግም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በቅጥር ጊቢው በመገኘት የችግሩን ሁኔታ ተመልክቷል።
በተደረገው ምልከታም በመናኸሪያው ቅጥር ግቢ ውስጥ ያለው አቧራ ከመጸዳጃ ቤት ችግር እና ከመናሪያዉ ጥበት ጋር ተዳምሮ ለተጠቃሚዎች ደረጃውን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ይግዛዉ ዳኜ፥ ችግሩን ለመቅረፈፍ ባለሰልጣን መስሪያ ቤቱ በመናኸሪያው የሚታየዉን የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታ ለማሻሻል የተለያዩ መፍትሄዎችን ሲያፈላልግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በ2010 በጀት ዓመት ግምባታውን በአዲስ መልክ ለማከናወን ታስቦ የነበረ ቢሆንም፥ በጨረታ መዘግየት ምክንያት ፕሮጀክቱ ለዘንድሮ መተላለፉን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
በዚህ መሰረትም ሙሉ ግምባታው 445 ሚሊየን ብር የሚፈጀው የቃሊቲ መናኸሪያ ግንባታን ዘመናዊ በሆነ መልኩ ለማከናወን ለ2011 በጀት ዓመት 184 ሚሊየን ብር በመመደብ በቅርቡ ወደ ስራ የሚገባ መሆኑን አክለዋል።
በ1 ዓመት ከ6 ወር የግምባታ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደስራ ይገባል የተበላው የቃሊቲ መናኸሪያ በቴኬኖሎጂ የታገዘ እና ዘመናዊነቱን በጠበቀ መልኩ ተገምብቶ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።