በማረቆና መስቃን አካባቢ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ አመራሮችንና ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል መጀመሩን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አንደገለጸው ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የማረቆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በለጠ ደራሮንና የመስቃን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሚፍታህ ሸምሱን ጨምሮ ሌሎች የወረዳዎቹ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው።
በፖሊስ ኮሚሽኑ የማዕከላዊ ዞኖች የፀጥታ ኮማንድ ፖስት ተጠሪ ኮማንደር እንዳለ አበራ እንደተናገሩት፥ ከአስተዳዳሪዎቹ በተጨማሪ የሁለቱ ወረዳዎች አስተዳደርና ፀጥታና ፖሊስ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በህዳር ወር መጀመሪያ በተከሰተው ግጭት ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ቁጥር 69 መድረሱንም ነው ኮማንደር እንዳለ የሚናገሩት።
በዚሁ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ መስከረም ወር ላይ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘም ለዚሁ ጉዳይ በተቋቋመ ግብረሃይል ጉዳያቸው የተጣራ 115 ተጠርጣሪዎች ላይም የዕስር ማዘዣ መውጣቱንና በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ሰላምን በማስጠበቅና የህግ የበላይነትን በማስከበር ከፀጥታ ሀይሉ ጋር እንዲተባበር በፖሊስ ኮሚሽኑ የማዕከላዊ ዞኖች የፀጥታ ኮማንድ ፖስት ተጠሪ ኮማንደር እንዳለ አበራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሁለቱ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት ከ43 ሰዎች በላይ ህይወት ሲያልፍ፤ ከ32 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ መፈናቀላቸውም ይታወሳል።