አዲስ አበባ የበዛ ነዋሪዋ ተከራይ ነው፡፡ ያሉት መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪው በቂ እንዳልሆኑ አከራዮች ገብቷቸው ተከራይን እንዳሻቸው ያደርጋሉ፡፡ ለሚያከራዩት ቤት የፈለጉትን ዋጋ ይተምናሉ። ለፈለገ ሳይሆን ለፈለጉት ብቻ ያከራያሉ፡፡ አቤት አንዳንድ አከራይማ ግፉ፡፡ ባለ ትዳር አይወድም! በተለይ ልጅ ያለው ተከራይማ የሚከራይ ቤት ማግኘት ቤት የመሥራትን ያህል ይከብድበታል፡፡ አከራዮች ላጤ የሆነ ነው ምርጫቸው። ቆሞ ቀር ልያደርጉን እኮ ነው ጎበዝ ፡፡ ኧረ እንተሳሰብ ተው!
ትናንት እኛ ግቢ ስብሰባ ነበር፡፡ ያው ተከራይ የሆነ መሰብሰብ ግዴታው ስለሆነ ባንፈልግም ተገኘን፡፡ እኛ ግቢ ተከራይ መሆን የበዙ የተከራይ መብቶች ያስነጥቃል፡፡ የግቢው በር ኳኳታ ከቤት ሠራተኛቸው አልፎ የቤቱ ባለቤት አከራያችን ጆሮ ከደረሰ በቃ ምንም ቢደክመን ማረፍ ቢያምረንም «እያማራችሁ ይቅር !አልጋው የእናንተ ይሁን እንጂ ቤቱ የኔ ነው» ብለው አንኳኩተው ይሰበስቡናል፡፡ «እንዴት ብትደፍሩኝ ነው እንዲህ የምታንኳኩት» ነው የስብሰባው አጀዳ የዚያን ቀን።
ስብሰባ ላይ ያልተገኘ ስብሰባው ሲያልቅ ቢተኛም ቢሆን ተቀስቅሶ «ቤቱን ለዕቃ ማስቀመጫነት ስለምንፈልገው ቤት ፈልግ» ይባላል፡፡ ነገር ግን ያ ተከራይ ሲለቅ አንድም ቀን ለዕቃ እንፈልገዋለን የተባለው ቤት ዕቃ ገብቶበት አያውቅም፤ ሌላ ተከራይ እንጂ። ለነገሩ አከራያችን «ዕቃ» እያሉ የሚጠሩት እኛ ተከራዮችን መሆኑ ዘግይቶም ቢሆን ገብቶኛል፡፡ ዕቃ ስለመሰልናቸው አይደል እንደፈለጉ የሚያደርጉን። አልላቀቅ ያለን ድህነታችን የተቋቋምንበት የአብሮ መኖርና መረዳዳት እሴቶቻችንን የተነጠቅንበት ክፉ ዘመን ወይ ነዶ! የትኛው ትውልድ ያለበትን ዕዳ እየከፈልን ይሆን?
ማታ ተሰበሰብን ምን ተሰበሰብን እላለሁ ለነርሱ ዕቃ አይደለን አጠረቀሙን፡፡ አከራያችን ባለቤታቸውን ጨምሮ ከ8 ልጆቻቸው ጋር በፍሰሐ «የተከራዮች ዕድሜ ያርዝምልኝ! ቤት ሠሪዎችን ያጥፋልኘ!» እያሉ ለእርሳቸው ልመና ለኛ እርግማን የሆነን ተማፅኖ ጠዋት ማታ ከፍ ባለ ድምፅ ስያሰሙ እኛ ተከራዮች አሜን የማለት ያህል በመደመም እናደምጣለን፡፡ በነገራችን ላይ መንግሥትንም እየረገሙ ነው፡፡ ቤት በመሥራቱ ላይ ይሳተፍ የለ፡፡ እንደውም የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት የቤት ግንባታው የሚጓተትበት በኛ አከራይ የቤተ ሠሪዎች ያጥፋልን እርግማን ሰለባ ሆኖ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡
እኛ እርግማን የምንለው ፀሎታቸው ፈጣሪ ይሰማቸዋል መሰል የእርሳቸው ኑሮ እያደር ሲጎመራ፤ ሲያብብ የኛ እያደር መኮስመኑ በዝቷል። እኛ ተከራዮቹ ከአከራያችን ከስምንት ልጆች ጋር አብረን ቤት የለንም ብለን ለኮንዶሚንየም ተመዝግበን ቁጠባው አቅቶን አቅማችን ደክሞ አቁመናል። የአከራያችን ልጆች የእነርሱ በሆነና ባከራዩልን ቤት ኪራይ ገንዘብ ለኛ የሚገባንን ኮንዶሚንየም ለመውሰድ ሳያቋርጡ ይቆጥባሉ፡፡ አከራያችን ለጤናቸው በመስጋት ስጋን እስኪተው ቀዩን ከጮማ አማርጠው ጥብስና ቁርጡ ሲሰለቻቸው ወጡን አዛንቀው በቅቤ እያሻመዱ እኛ ተከራዮችን በሽታ እያጠገቡ በድሎት ኑሮን በርቀት እንቁልልጭ ይሉናል። ልጆቻቸውን ምግብ በቃኝ ባሉ ጊዜ በግድ «ካልበላህ» ብለው በሶፍት እየገረፋ ያስለቅሱብናል።
ዛሬ አከራያችን የሰበሰቡን አንዱ ተከራይ «ሲያንኳኳ ረበሸኝ» በሚል ከንቱ ምክንያት ቢሆንም የቤት ኪራይ ዋጋ ሊጨምሩ መሆኑም ጭምጭምታ ቀድመን ሰምተን ነበር፡፡ እናም ዛሬ ክፈቱልኝ ብሎ ያንኳኳው ተከራይ ልክ ልኩን ነግረው ሲያበቁ የቤት ኪራይ ዋጋ በእያንዳንዳችን ላይ ሊጨምሩ መሆኑን እግረ መንገዳቸውን አረዱን። አከራያችን የቤት ኪራይ ዋጋ በየ6 ወሩ ምክንያት እየፈለጉ መጨመር ልማድ አድርገዋል። በነገራችን ላይ ተከራዮች በሚያሳዩት አንዳንድ ሁኔታዎች ውድ የሆነ ዕቃ መግዛትና መሰል ለውጦች ካዩ የቤት ኪራይ ዋጋ የሚጨምሩበትም ጊዜ አለ፡፡
በየመንደሩ ያሉ ቤት አገናኝ ደላሎች ከአከራይ ጋር ተግባብተው ቤቶቹን የመተመንና የቆየን ተከራይ ማስወጣት ዋጋ ጨምሮ ለሌላ የማከራይት ሙሉ መብት ተጎናፅፈዋል። አከራይ ተጨምሮ ይከራይለት እንጂ የተከራይ ቤት ማስለቀቅ ምኑም ሆኗል፡፡ አዲስ ተከራዮችን እንዲህ የእንጀራ ልጆች አድርጋ ትቅር። አከራዮች ግን ተከራዮች እንጀራቸው አይደሉ? ሰው እንዴት እንጀራውን ያንገላታል። ወይ ምርጫ ማጣት!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2011
ተገኝ ብሩ (ሻሚል)