ፌስቡክ እነሆ የአንድ ጎረምሳ ዕድሜ አስቆጠረ፤ ፐ! ለካ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስለደረሰ ነው እንዲህ ልቡ ያበጠው! የጎረምሳ ባህሪ ታውቃላችሁ አይደል? በቃ የፌስቡክ ባህሪ እንደዚያ እየሆነ ነው። እስኪ እስከሚሸመግል እንታገሰው። የምር ግን ፌስቡክ እኮ እንደዋዛ15ዓመት ሆነው።
ምናልባት በኢትዮጵያ መቼ እንደተጀመረ በትክክል ባይታወቅም በመስራቹ አገር አሜሪካ ግን የፊታችን ጥር 27 ቀን 15ኛ ዓመቱን ያከብራል። በይፋ የተከፈተው ጥር 27 ቀን 1996 ዓ.ም ነው (አቆጣጠሩን ወደራሳችን አምጥቸዋለሁ)፡፡ አይ! አተረጓጎም ላይ አናምንህም ካላችሁኝ ደግሞ በፈረንጆች ‹‹ፌብርዋሪ›› 4/2004 ነው (ዓ.ም አይባልም አይደል ለፈረንጅ አቆጣጠር?) እና 15 ዓመት ሲሞላው ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ! የጎረምሳነት ባህሪው።
ጎረምሳ ያየውን ሁሉ ማድረግ ያምረዋል፣ የእምቢተኝነት ባህሪ አለው፣ ከቤተሰብ ወጣ ብሎ ብቻውን ይሆናል (ይችኛዋን አስምሩልኝ)፤ እናም እነዚህ ሁሉ ባህሪያት ፌስቡክ ላይ እየታዩ ነው። ገና እንደተጀመረ ሰሞን ብርቅ ነበር፤ አገልግሎቱም ሰውን ከሰው ማገናኘትና ፎቶ መለጠፍ ነበር፤ አለፍ ሲል የተቃራኒ ጾታ «መጀናጀኛ» ሆነ። ያኔ እንዲህ ትኩረት አይሰጠውም ነበር (ልጅ ነበር ማለት ነው) አሁን ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች በእርሱ ሆነው እረፍ!
ለመሆኑ አዛውንት ሲሆን ምን መልክ ይኖረው ይሆን? ብዬ ሳስብ ለካ አዛውንት አይሆንም (የራሴው ትንበያ ነው)። እመኑኝ በዚህ አያያዛችን ፌስቡክ አዛውንት ሆኖ አናየውም። በዚህ 15 ዓመታት ውስጥ ይሄ ከሆነ ከ15 ዓመታት በኋላ ፌስቡክ አይኖርም። ‹‹እንዴት?›› ማለት ጥሩ ነው።
አሁን እንዲህ ፌስቡክ ላይ ቀልባችንን ያጣነው እኮ በምክንያት ነው። ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮቻችንን ፌስቡክ ላይ ስለምናገኛቸው ነው። እስኪ በአንድ ጽሑፍ ላይ የሚሰጡ አስታያየቶችን አስተውሉ፤ የሚለጠፉ ቀልዶችን ልብ በሉ፤ የሚጻፉ ወጎችንም ተመልከቱ፤ አባባሎችንና ተረቶችን ልብ ብላችኋል? ሁሉም የማህበራዊ ሕይወታችን ውጤቶች ናቸው። እንግዲህ በዚህ ከተግባባን አሁንም ተከተሉኝ።
በየካፌው፣ በየሥራ ቦታው፣ በየመጓጓዣው ብቻ በየትኛውም አጋጣሚ ሁሉ(ምግብ ስንበላ ሁላ ማለት ነው) ግንኙነታችን ከፌስቡክ ጋር ብቻ ሆኗል። በተለይ ደግሞ ካፌ ውስጥ ብዙ ቀን እንደ ሞኝ አፌን ይዥ የተገረምኩባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። ሰው ካፌ የሚገናኘው ለምንድነው? ለሻዩ ወይም ለማኪያቶው እኮ አይደለም፤ ይልቅ ከዚያ በላይ ለመጫወት ነበር አይደል?
ግን ካፌ ውስጥ ስታዩ አንድ ጠረጴዛ ላይ ሆነው አይተያዩም፣ አይነጋገሩም። ሁሉም ስልኩ ላይ የተጣደ ነው የሚመስለው። አጠገቡ ምን እንደሚከናወን አያይም፤ በአካባቢው ምን እንደሚከናወን አያስተውልም። ስብሰባ ቦታ ላይ ማንም ከቀልቡ ሆኖ የሚባለውን አይሰማም፤ የተባለውን ረስተውት መሰለኝ ስብሰባዎች ይራዘማሉ፤ ይደጋገማሉ፤ (ለዚህ ይሆን እንዴ ስብሰባ የበዛው?) በመጨረሻም ለውጥ አይኖራቸውም። አንዱ አንዱን ሳይሰማ ሲወጡ አይቶ ይወጣል(ወይ ጣጣ!)
በቤተሰብ፣ በጓደኛሞችና በሥራ ቦታ ላይ ፌስቡክ ሁሉንም ሰው ብቸኛ እንዳደረገ ደጋግሞ የተባለ ነገር ነው። አሁን እኔን ያሳሰበኝ በዚህ አያያዝ ከ15 ዓመት በኋላ ፌስቡክ አሁን የያዘውን መልክ ይይዛል ወይ ነው። ምክንያቱም አሁን እየተጠቀምንበት ያለነው የማህበራዊ ሕይወታችን ነጸብራቅ ነው። እስከአሁን ባለን እርሾ ነው የምንጽፈውም፣ የምናነበውም።
አሁን እንግዲህ ሁሉም አሻንጉሊት እየሆነ ነው፤ ሰዋዊ የሆነው ግንኙነት እየቀረ መጥቷል። ስለዚህ ማህበራዊ ጉዳይ ከየት ይመጣል? ኧረ እንዲያውም ገና የጋራ መግባቢያ ቋንቋም ልናጣ እንችላለን። በነገራችን ላይ ሰሞኑን አንድ ታዋቂ መጽሔት ላይ ያነበብኩት ጽሑፍ በጣም ነበር ያናደደኝ። ምርጥ የምርመራ ዘገባ ይዞ የተጻፈው ግን በፌስቡክ ቋንቋ ነው። ምንም እንኳን ያንን ድንቅ የምርመራ ዘገባ ይዞ በዚህ መተቸት ከባድ ቢሆንም ወዴት እየሄድን እንደሆነ ግን ግልጽ አድርጎ ያሳየናል።
በእያንዳንዱ አንቀጽ ውስጥ የፌስቡክ ቋንቋ ነው ያለው። ብዙ ቦታ ላይ በ‹‹ሁ›› ፋንታ ‹‹ው››ን ነው የሚጠቀም። አሁን ዋናው ፍራቻ ለጊዜው የአጻጻፍ ሥርዓትን ማበላሸቱ ብቻ አይደለም፤ ጭራሹንም የሰው ልጅ ለሰው ልጅ አዲስ እንዳይሆን ነው የፈራሁት። ኧረ ጎበዝ ይሄ ነገር አስፈሪ ነው! አስባችሁታል? አሁን የቤት እንስሳት የምንላቸው እኮ ተላምደው እንጂ የዱር እንስሳት ነበሩ አሉ።
እኛ ሰዎችም እኮ ዋሻ በምንኖርበት ጊዜ አሁን ያለውን የሰው ልጅ ማህበራዊ ሕይወት አልነበረንም። ስለዚህ ይሄ መለያየት እየሰፋ በሄደ ቁጥር የሰው ልጅ ለሰው ልጅ አስደንባሪና አስፈሪ ፍጡር ሊሆንበት ይችላል። ጎበዝ ወደ አሻንጉሊትነት ሳንቀየር ልናስብበት ይገባል፤ የአዛውንቱን ዘመን ማምጣት ይበጀናል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2011
ዋለልኝ አየለ