ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ባደገበት ዓመት ለዋንጫ ክብር የበቃ እንደ ጅማ አባ ጅፋር ዓይነት ክለብን አፍርታለች፣ ለፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ያልሆነ፣ በሻንፒዮንስ ሊጉም ብርቱ ተፎካካሪ በመሆን ለዋንጫ ፉክክር የደረሰው ጅማ አባቡናም ከእርሷው ማህፀን የወጣ ነው፡፡ በብሔራዊ ቡድኖች ታሪክ መስራት የቻሉና እየሰሩ ያሉ ተጫዋቾችንም ከማፍራት አልተቆጠበችም፤ በልምላሜዋና በቡና ሀብቷም ትታወቃለች፣ የደቡብ ምዕራቧ ጅማ ከተማ፡፡ ይሁን እንጂ ከተማዋ ዕድሜ የለገሳትን ስምና ታሪክ ያህል በስፖርቱ ዘርፍ ጎልቶ የሚጠቀስ ገድል አላት ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ ለዚህ በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ቢችሉም፣ ከጅማ ስታዲየም ባለፈ ሊጠቀስላት የማይችለው ጅማ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች ችግሯን በቀዳሚነት ማንሳት ይቻላል፡፡
ከሰሞኑ ከወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የተሰማው መልካም ዜና ግን በከተማዋ የሚታየውን ይሄን የስፖርት ማዘውተሪያዎች ችግር ከማቃለል አኳያ አንድ እርምጃ ያስጉዛል የሚል እምነት አሳድሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ቢሆን፣ ሰሞኑን አስገንብቶ ያስመረቃቸው እነዚህ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እያከናወናቸው ካሉ የማህበረሰብ አገልግሎቶች ባለፈ፤ የህብረተሰቡን ችግሮች ለይቶ መፍትሄ ማቅረብና አካባቢያዊ ልማትን ከማገዝ አኳያ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ያሳዩ ናቸው ተብሎለታል፡፡ እኛም በዛሬው የስፖርት አምድ እትማችን፤ ዩኒቨርሲቲው በስፖርቱ ዘርፍ እያከና ወናቸው ያሉ ሥራዎችንና በቀጣይም ለማከናወን ባቀዳቸው ተግባራት ዙሪያ በዩኒቨርሲቲው የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና የስፖርት ጂምናዚዬም አስተባባሪ ከሆኑት አቶ አማኑ ኤባ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጅማ ዩኒቨርሲቲና ስፖርት እንዴት ይገለጻሉ?
አቶ አማኑ፡- የጅማ ዩኒቨርሲቲና ስፖርት የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ዩኒቨርሲቲው በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲው የሚገነቡ በርካታ የስፖርት መሰረተ ልማቶችም የዚሁ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከድሮም ጀምሮ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት የሚታወቅ ነው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ መቀዛቀዞች ቢታዩም፣ በዩኒቨርሲቲው በሠራ ተኞች፣ በኮሌጆች፣ በተማሪዎች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲውና በከተማው መካከል የሚደረጉ ትልልቅ ውድድሮች ነበሩ፡፡ እናም ስፖርት በዩኒቨርሲቲው በዚህ መልኩ በትልልቅ ውድድሮች የሚዘወተር እንደመሆኑ፤ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎችም መጥተው ከእኛ ልምድ ይወስዳሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲልም ለስፖርቱ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራ ነበር፡፡ ተቋርጦ የነበረውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ውድ ድርም በ1996 ዓ.ም እንዲቀጥል ማድረጉና በዚሁ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው ውድድሩን እንዲያዘጋጅ መደረጉ የዚሁ ማሳያ ሲሆን፤ አሁንም ያስገነባቸውና እያስገነባቸው ያሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶቹ ዩኒቨርሲቲው ከስፖርት፤ ስፖርትም ከዩኒቨርሲቲው ላለመነጣ ጠላቸው ገላጭ ነው፡፡ ከዚህ ውድድር ጀምሮም ዩኒቨርሲቲው በየውድድሮቹ በከፍተኛ ሞራል ይሳተፍ ነበር፤ ከፍተኛ ውጤቶችንም አስመስ ግቧል፡፡ በ2000ዓ.ም እንደ አዲስ ሲጀመርም ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ፉክክር ነበር ያደረገው፡፡ ከዚህ ጀምሮ ያሉትን ውድድሮችም ዩኒቨር ሲቲው በተሳትፎም ሆነ በውጤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ከፍተኛ ተጠቃሽ ነው፡፡
እነዚህ ውጤቶችና ተነሻስነቱ ደግሞ በቅርቡ ለተመረቁት የስፖርት መሰረተ ልማቶችም በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀር ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰሩ በማስቻል በኩል የድርሻቸውን አበርክተዋል፡፡ ዩኒቨርሲ ቲው በተለይ በ2007 ዓ.ም ማሸነፉን ተከትሎ የተፈጠረው ሞራልና ከፍተኛ ተነሳሽነት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መርቀው የከፈቷቸው የስፖርት አካዳሚዎችና ማዘውተሪያዎች እውን እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ከእነዚህም በመቀመጫ 40ሺ ሰው የሚይዝ ስታዲዬም አንዱ ሲሆን፤ ሁለት ጂምናዚዬሞችም አሉን፡፡ አንዱ ቀደም ሲልም እያስተማርንበት ያለው የተለያዩ ውድድሮችን ማድረግ የሚችል ሲሆን፤ መቀመጫዎች ያለውና የባድሜንተን፣ የቅርጫት፣ የእጅና መረብ ኳስ ውድድሮችን ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የውሃ ዋና ገንዳም አለን፡፡ አሁንም «ሚኒ» ስታዲዬም ወይም «ሲቪክ» ማዕከል ተብሎ የተገነባውና በተመሳሳይ በርካታ ውድድሮችን ማድረግ የሚያስችለው ነው፡፡
ከአዲሱ ስታዲዬም ባለፈም «አባ ጅፋር ሜዳ» እያሉ የሚጠሩት ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ ሜዳ አለ፡፡ ይሄም በስነስርዓቱ ተገንብቶ ተማሪዎችም እየሰሩ ያሉት እዚሁ ሜዳ ላይ ነው፡፡ ከእነዚህ ባለፈም የቅርጫት ኳስና የመረብ ኳስ እንዲሁም የሜዳ ቴኒስ ሜዳዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እውን መሆናቸው ደግሞ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ለስፖርቱ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱንና እየሰራ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው ስፖርቱን ለማሳደግና ለመደገፍ በዚህ መልኩ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን እያከናወነ ከሆነ፣ እናንተ እንደ ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ዩኒቨርሲቲው የስፖርትና ስፖርተኞች ማዕከል እንዲሆን ከማስቻል አኳያ ምን ሰርታችኋል? ምንስ አስባችኋል?
አቶ አማኑ፡- ቀደም ሲልም እነዚህ መሰረተ ልማቶች ሳይገነቡም ጭምር ከከተማው ማህበረሰብ ጋር በስፖርት ዙሪያ እየሰራን ነው ያለነው፡፡ የእኛ መምህራንም እየሄዱ በአመጋገብ (ኒውትሬሽናል)፣ በሥነልቡና፣ በማስተባበር (ኮርዲኔሽን) ና በተለያዩ ቴክኒካል ኮሚቴዎች ውስጥ ጭምር እየገቡ እየሰሩ ነው ያሉት፡፡ ሆኖም እነዚህ የድጋፍ ሥራዎች ወደ አካዳሚ መምጣት ስላለባቸው ከ2008/9 ዓ.ም ጀምሮ ዩኒቨርሲቲው ቀደም ብሎ የከፈተው አካዳሚ አለ፡፡ ለዚህም የባህር ዳርን፣ አርባ ምንጭን፣ አዲስ አበባንና የጥሩነሽ አካዳሚን ባለሙያዎች በመጎብኘት ልምድ ተወስዷል፡፡ የእነርሱ አደረጃጀት እንዴት ነው፤ እንዴትስ ነው እየሰሩ ያሉት፤ ምን ምን አላቸው፤ እነርሱ ካላቸው ነገርስ እኛ ምን ለየት ያለ ነገር ሊኖረንና በምን መልኩስ ለየት አድርገን ልንከፍት ይገባል፤ የሚሉት ታይተዋል፡፡ እናም እነዚህን ልምዶች ወስደንና አደረጃጀቶችን ሰርተን ለበላይ አመራሩ አቅርበናል፡፡ የበላይ አመራሩም እነዚህን እያየ ነው ያለው፡፡
አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲው በስፖርቱ መስክ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ እየሰጠን ነው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም ለበላይ አመራሩ የቀረበው የአካዳሚ አደረጃጀት ታይቶ ሲፈቀድና ሥራ ስንጀምር በአደረጃጀቱ ውስጥ የተካተቱ የተለያዩ ዘርፎች (ዲስፕሊኖች) አሉ፡፡ በዚህም አካባቢውን መሰረት በማድረግ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የእግር ኳስን የመሳሰሉትን ስፖርቶች ከታች ጀምሮ (ከ13፣ 15 እና 17 ዓመታ በታች እያልን) ለማሳደግና ለዚህም ባለሙያ ቀጥረን ለመስራት ነው ያሰብነው፡፡ የምንመርጣቸው ልጆችም ከዚሁ ማህበረሰብ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ እርምጃ ባለው ነገር ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለን እናምናለን፡፡
ከዚህ አኳያ በእግር ኳስ በኩል አንድ የኮሪያ ድርጅት አለ፡፡ በዚህም ከ11 ዓመት በታች ወደ 30 ልጆች አሉ፡፡ ሆኖም እኛ ገና በደንብ ስላልተደራጀንና የበላይ አመራሩም አካዳሚውን ስላላጸደቀልን ባለው ሁኔታ ለእነዚህ በሙያ ድጋፍ ስላለብን የሙያና የሜዳ ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ እነዚህ ልጆች ከውጭ አሰልጣኝ ተቀጥሮላቸው ከእኛ አሰልጣኞች ጋር በመሆን እየሰለጠኑ ሲሆን፤ ምግብ በሳምንት ሁለት ጊዜ እንዲያገኙም እየተደረገ እየሰሩ ነው ያሉት፡፡ ይህ ግን በቂ ነው ማለት ሳይሆን እንደ መግቢያ እየተጠቀምንበት ነው፡፡ የቋሚ አካዳሚውን በተመለከተ ግን ይሄን ያክል ታዳጊዎችን እንቀበላለን ብሎ ለመወሰን ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም በባለሙያ ተወስኖ ስለሚከናወን ሥራ ሲጀመር ማሳወቁ የተሻለ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጅማና አካባቢውም ሆነ እንደ አገር ስፖርቱ ችግር ያለበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ታዲያ እናንተ እንደ ዩኒቨርሲቲው የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ባለሙያ እነዚህን ችግሮች በጥናት ለይቶ መፍትሄ ከማስቀመጥ አኳያ ምን ያህል ሰርታችኋል?
አቶ አማኑ፡- አሁን በምናየው ነገር በስፖርቱ ጉዳይ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ በእነዚህ ነገሮች ላይም እኛ እንደ ትምህርት ክፍል ገና ወደ አደረጃጀት ውስጥ ገብተንና ጥናት ሰርተን ለመፍትሄ የምንሰራበት መንገድ ላይ ነው ያለነው፡፡ ነገር ግን የእኛ ባለሙያዎች በበርካታ ስፖርታዊ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፉ፤ ከአትሌ ቲክስና እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ጋር እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፣ አሁን እግር ኳስ ፌዴሬሽን እየሰራ ያለው ሪፎርም ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ እናም እንደ ትምህርት ክፍል ገና መንገድ ላይ ብንሆንም በባለሙያዎች በኩል ግን ችግሮችን ከመለየትና መፍትሄ በማፈ ላለግ በኩል ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር እየተሳተፍን ነው፡፡
ከዚህ አኳያ፣ በቅርቡ በጅማ ከተማ በአትሌቲክስ፣ በእግር ኳስና በሌሎች የተለያዩ ሙያዎች የተለያዩ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ በእነዚህ ስልጠናዎች ባለሙያዎቻችን ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ እኔም ባሉት ነገሮች ላይ በአስተባባሪነት (ኮርዲኔተር) ተሳትፌያለሁ፡፡ በውሃ ስፖርቶች ስልጠናም የእኛ ባለሙያ ነው እየሄደ ስልጠና የሚሰጠው፡፡ በዚህ መልኩ ያለው ተሳትፎ ሰፊ ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የእኛ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችም በአራቱ የኳስ ጨዋታዎች (በእግር አኳስ፣ በመረብ ኳስ፣ በቅርጫት ኳስና በእጅ ኳስ) ከፌዴሬ ሽኖች ጋር በመተባበር ስልጠና እንዲያገኙ እያደረግን ነው፡፡ ከካፍ የመጡ ባለሙያዎች ለጅማ ከተማና አካባቢው አሰልጣኞች የ«ሲ» ላይሰንስ ስልጠና እንዲሰጡ አመቻችተናል፡፡ ይህ ሂደት ግን በወቅታዊ ሁኔታዎች እየተቋረጠ ሲሆን፤ እስካሁን እያበረከትን ያለውን ድራሻ የበለጠ ለማሳደግና ለማጠናከር በተለያዩ መስኮች ሶስተኛ ዲግሪ ያላቸውን ባለሙያዎች እያፈላለግን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የጅማ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ዘርፉ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ሊገለጽ የሚችል ውጤት ለማምጣት ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ነው፡፡ እንደ ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ይሄን ከማገዝ አኳያ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛላችሁ?
አቶ አማኑ፡- እንዳልከውም የጅማ ዩኒቨርሲቲ የላቀ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ነው እየሰራ ያለው፡፡ በዓለምም ታዋቂ ለመሆን ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለዚህ ከሚሰራባቸው ዘርፎች ውስጥ ደግሞ ስፖርቱ አንዱ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ መሰረተ ልማት እየተሰራ ያለውም ለዚሁና ማኔጅመንቱም ለስፖርቱ ትልቅ ትኩረት ስለሰጠው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ካሉት በተለይም ደቡብ ምዕራብ ቀጣናዎች የታወቀው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይሄንን ባለ ሶስት ፎቅ ስታዲዬም ሲያስገነባም፤ አካዳሚ ለመሆን ሲያስብም ዩኒቨርሲቲው ለስፖርቱ ዕድገት ያለውን ጉዞ ለማጎልበት ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው የላቀ ለመሆን ካስቀመ ጣቸው ግቦች ጋር ስፖርቱ በዚህ መልኩ ሲገነባም እኛ እንደ ስፖርት ሳይንስ ዲፓርት መንት የራሳችንን ትልቅ ሚና መጫወት እንፈልጋለን፡፡ በዚሁ አግባብ ነው እየሰራን ያለነው፡፡ ለምሳሌ፣ እየሰራ ባለው አካዳሚ ፊዚዮ ቴራፒና ኒውትሬሽን አለ፡፡ እነዚህ ዲፓርትመንቶችም አሉ፡፡ ፊዚዮሎጂና አናቶሚ የሚባሉም የህክምና ዘርፎችም አሉ፡፡ ከእነዚህ ጋር ተገናኝተን፤ ከፍተኛ አመራሩ በፈቀደው መሰረትም አቅሙና ሙያው ያላቸውን መምህራን ከውጭ እያፈላለግን ነው፡፡ በዚህ መልኩ መሰረተ ልማቱ ሲሟላና ትላልቅ ባለሙያዎችም ከመጡ በኋላ፤ በህክምና ዘርፉ (ፊዚዮ ቴራፒና ኒውትሬሽን በመሳሰሉትም) በከፍተኛ ደረጃ ለመስራት ነው አቅማችንን እያሰባሰብን ያለነው፡፡ እነዛን ለመስራት ደግሞ መጀመሪያ አካዳሚው በደንብ መደራጀት አለበት፤ የቤተ-ሙከራ ክፍሎች በደንብ መደራጀት አለባቸው፤ በዚህ ረገድም ወደ 75 በመቶ ሥራውን ጨርሰናል፡፡ ከፍተኛ አመራሩም በከፍተኛ ደረጃ እየረዱን ነው ያሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- እናንተ እንደ ስፖርት ሳይንስ ባለሙያ ቀጣይ በጅማ እና አካባቢዋ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ስፖርት ውጤት አንድ እርምጃ ወደፊት ከማስጓዝ አኳያ የራሳችሁን አሻራ ማሳረፍ የሚያስችላችሁ ምን ሥራ አከናወናችሁ? ቀጣይስ ምን ለመስራት ተዘጋጅታችኋል?
አቶ አማኑ፡- እነዚህ የሚሰሩት በባለሙያው ብቻ ሳይሆን በስፖርቱ የሚሳተፉ በከተማው ያሉ የተለያዩ አካላት አሉ፡፡ በቀጣይም ከእነርሱ ጋር ለመስራት ነው ያሰብነው፡፡ ብቻችንን እዚህም መድረስ አንችልም፡፡ በቀጣይም ስፖርት እንደ አካዳሚም ብቻ ሳይሆን እንደ ገቢ ምንጭም እንዲያገለግል ነው ዩኒቨርሲቲው የሚጠቀ መው፡፡ ለምሳሌ፣ አካዳሚው የተገነባበት ቦታ ለአካባቢው ህብረተሰብ እንዲያገለግል በሚያመች መልኩ ነው፡፡ ምክንያቱም የእኛ ዩኒቨርሲቲ እዛጋ ሲሆን፣ የጅማ ከተማና የጅማ ዞን ሀብት የሆኑት ጅማ አባጅፋርና ጅማ አባቡና ክለቦች አሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም ቀድሞ የተገነባ ጅምናዚዬም አለ፤ ይህ ጅምናዚዬምም ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን አገልግሎት እየሰጠ ያለ ነው፡፡ እናም ይሄን ጂምናዚዬም አሁን ላይ ለስታፍ ብቻ በማድረግ ለአካባቢው ማህበረሰብ ሌላ ለመክፈት አስበናል፡፡ እናም ከአካዳሚው ባለፈ እነዚህንና መሰል ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ሥራዎችን ለመስራት አቅደናል፡፡ የመዝናኛና የስልጠና ማዕከሎችን ለማዘጋጀትም አስበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲው ያስገነባቸው የስፖርት መሰረተ ልማቶች ለህዝቡ አገልግሎት የሚሰጡ የህዝት ሃብት እንደመሆናቸው እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ ጠብቆ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማስቻል ምን ታስቧል? ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ዕድሉን ልስጥዎ፡፡
አቶ አማኑ፡- እነዚህን መሰረተ ልማቶች ዩኒቨርሲቲው ቢያስገነባቸውና ቢቆጣጠራ ቸውም ግልጋሎታቸው ግን ለጅማ ከተማና የአካባቢው ህዝብ ነው፡፡ እናም እነዚህን መሰረተ ልማቶች በጋራ ነው መጠበቅና መቆጣጠር ያለብን፡፡ ከዚህ አኳያ እነርሱም የእኛ ንብረት ነው ብለው እንዲያስቡ በቅርበት እየሰራን ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን መሰረተ ልማቶች እንዴት መያዝና መቆጣጠር እንዳለብን እነርሱም በደንብ ያውቁታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከከተማው ባለድርሻዎች ጋርም እየተገናኘን እየሰራን ነው፡፡ በዚህም ከእነርሱ ጋርም ግንዛቤውን ፈጥረን አብረን እንሰራለን፤ ቁጥጥርም እናደርጋለን፡፡
ይሁን እንጂ ይሄን መሰረተ ልማት ከመጠበቅ አኳያ በትምህርት ክፍሉ ስር አንድ የመሰረተ ልማት ጥበቃ ክፍል ማቋቋም ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ንብረቶች በአግባቡ ተጠብቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ካስፈለገ በዋናነት እነርሱን የመጠበቅ ኃላፊነት የሚወስድ ክፍል ያስፈልጋል፡፡ እናም በትምህርት ክፍሉ ስር «ፋሲሊቲ ማናጅመንት» በሚል አንድ ክፍል ለማቋቋም ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ይህ ክፍል በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስር ያሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን እንዲቆጣጠር፤ በሥርዓቱ እንዲይዝ የሚያደርግ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የስፖርት ሜዳው 20 እና 30 የሚሆን ተንከባካቢ ያስፈልገዋል፡፡ ሌሎቹም በተመሳሳይ፡፡ እናም አንድ ክፍል ይደራጅ ብለን ስናስብ እነዚህን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ እነዚህ መሰረተ ልማቶች ስፖርቱን ለማስፋፋት ወሳኝ እንደመሆናቸው፤ ይህ አደረጃጀት ሳይጸድቅም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ከዋና ፌዴሬሽንና ከሌሎችም ጋር በመሆን ለመስራት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ምክንያቱም እነርሱ ለእኛ፣ እኛም ለእነርሱ አጋዥ በመሆናችን እየተጋገዝን መስራት አለብን ብለን እየተንቀ ሳቀስን ነው፡፡
ሆኖም ስፖርት ያለ ህብረተሰቡ ተሳትፎ የትም አይደርስም፡፡ ስፖርቱን ለማሳደግ የግዴታ ህብረተሰቡ መሳተፍ አለበት፤ ከፍተኛ አመራሩም መሳተፍ አለበት፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲም እኛ ሁሌም ለዚህ ፍላጎት አለን፤ በዚህ ረገድ ደግሞ ትልቁ ግብዓታችን የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራር አዎንታዊ ምላሽ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች አዎንታዊ ድጋፍና ፍላጎት ካላቸው ስፖርቱን ትልቅ ቦታ ማድረስ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከጊዜዎት ላይ ቀንሰው ለቃለ ምልልሱ ስለተባበሩኝ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ አማኑ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8.2011
ወንድወሰን ሽመልስ