
«መጉላላቱ የተከሰተው ወደ ክፍያ ሥርዓቱ ለመግባት የአንድ ዙር ጊዜ በመጓተቱ ነው»
– የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
አዲስ አበባ፡- የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያችንን ለመክፈል ወደ ክፍያ ማዕከላት ስንሄድ መጉላላትና እንግልት እየደረሰብን ነው ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎች አስታወቁ። የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ፤ መጉላላቱ የተከሰተው ወደ ክፍያ ሥርዓቱ ለመግባት የአንድ ዙር ጊዜ በመጓተቱ መሆኑን አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሰሜን አዲስ አበባ ዲስትሪክት ቁጥር 7 አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተገኝተው ወረፋ እየጠበቁ ያሉና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ለአገልግሎት ክፍያ ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ሰልፍ በመያዝ ቢጠባበቁም በቀጠሮ እየተሰናበቱና የቀጠሯቸው ዕለትም መስተናገድ ባለመቻላቸው መጉላላትና እንግልት እየደረሰባቸው ይገኛል።
«‘‘የመክፈያ ደረሰኝ አልመጣልንም’’ እየተባልን ረጃጅምና አሰልቺ ሰልፎችን ይዘን የምንጠባበቅበት ጊዜም አለ» የሚሉት እኒህ ቅሬታ አቅራቢዎች የቀጠሩን ሠራተኞች በሥራ ሰዓት ወጥተው በመሄዳቸውም ወረፋ ሲደርሳቸው መክፈል አለመቻላቸውን አስረድተዋል።
በረጃጅም የወረፋ ሰልፎች ምክንያትና ሰልፎቹን በሥርዓት የሚመራ አካል ባለመኖሩ ለድብድብ የሚጋበዙ ሰዎች ጉዳት እያደረሱ ስለመሆኑ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተስፋ ባለመቁረጥ ተሰልፈው ያለ አገልግሎት ወደቤታቸው እንደሚመለሱም ተናግረዋል።
‘‘በማዕከሉ የሚስተናገደውን ህብረተሰብ ቁጥር ያገናዘበ በቂ የሰው ሃይል ባለመኖሩ ምክንያት ምሳ ሳንበላ ተሰልፈን እንውላለን፤ እንደዛም ሆኖ ሳንስተናገድ እንሄዳለን፤ አቅመ ደካሞችና የሚያጠቡ ሴቶችም ለእንግልት እየተዳረጉም ነው’’ ብለዋል ቅሬታ አቅራቢዎቹ።
ከዚህ በፊት በ ‘ለሁሉ’ የክፍያ ማዕከል ክፍያ ሲፈፅሙ ከ1 እስከ 5፣ ከ6 እስከ 10፣ ከ11 እስከ 17 እና ከ26 እስከ 30 ባሉ ቀናት በሶስት ምድብ ይከፍሉ ስለነበር እንዲህ አይነት መጉላላትና እንግልት ደርሶባቸው እንደማያውቅ የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ክፍያው ወደማዕከላት ሲመጣ ግን ሁሉም ክፍያ በአንድ ጊዜ በመደረጉ ሥርዓት እንዳይዝ አድርጎታል ብለዋል።
ቅሬታውን ይዘን የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌን አነጋግረናል። ሥራ አስኪያጁ የተነሱት ቅሬታዎች መኖራቸውን አምነው ችግሩ በዋናነት የተፈጠረው የክፍያ ሥርዓቱን ከ ‘ለሁሉ’ ወደ ኤሌክትሪክ አገልግሎቱ እንዲሆን ለማድረግ በነበረው ሥራ ምክንያት ወደ ሥርዓቱ ለመግባት የአንድ ዙር የመክፈያ ጊዜ በመጓተቱ መሆኑን አስረድተዋል።
«በክፍያ ማዕከሉ ከሠራተኞች ቅጥር ጋር በተያያዘ እጥረት መኖሩም ለመጉላላቱ አንደኛው ምክንያት ነው» ያሉት አቶ በቀለ፤ ሠራተኞቹ በሥራ ሰዓት ይወጣሉ የተባለው ግን የተሳሳተ መረጃ እንደሆነ ተናግረው፤ ችግሩን ለመፍታት የቅጥር ሂደቱን የማስተካከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ደንበኞች ክፍያቸውን ሲፈፅሙበት የነበረው አራት የክፍያ የጊዜ ሰሌዳ በሚቀጥለው ወር በአግባቡ ተግባራዊ ስለሚሆን ችግሩ እንደሚፈታ ተናግረው፤ ደንበኞች በየማዕከላቱ የሚለጠፉ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቶችን በማንበብ ከአላስፈላጊ እንግልት ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 11/2011
ድልነሳ ምንውየለት