ሰሞኑን ስለ ሌብነት በሰፊው እየሰማን ነው፡፡ በተለያየ የመንግስት ተቋማት ቁጥሩን ለመጥራት የሚከብድ ምናልባትም ብዙዎቻችን ፃፉት ብንባል እንኳ የሚከብደን የብር መጠን ምዝበራ እንደተፈፀመ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እያደመጥን እንገኛለን፡፡ ይህን መነሻ በማድረግም በማህበራዊ ድረገፆች፣ በህዝብ መገልገያ ትራንስፖርት ውስጥ፣ በካፌዎች፣ ብቻ ምን አለፋችሁ ሰዎች ሰብሰብ ብለው በምታዩበት ቦታ በጉዳዩ ላይ ትንተና ሲሰጥ እንሰማለን፡፡ ሁሉም ሌብነትን ሲያወግዝም ይታያል፡፡ ትክክልም ነው! ነገር ግን ችግሩ ብዙ ጊዜ የምንናገረው ሌሎች መስማት የሚፈልጉትን እንጂ ትክክለኛ ማነታችንን ባለመሆኑ ዞር ሲባል እኛም የችግሩ ተሳታፊ ሆነን እንታያለን፡፡
ለችግሩ መፍትሔ ተጠያቂነት ላይ በርትቶ መሥራት እንደሆነ የሚያነሱ ቢኖሩም እኔ ግን ትውልድን በመልካም ሥነምግባር ማነጽ ላይ ነው እላለሁ፡፡ ግን በየት በኩል? ከላይ እንዳነሳሁላችሁ ሁላችንም የችግሩ ተጋሪ ነን፡፡ የላይኛው የመንግስት መዋቅር ጋር ሳናንጋጥጥ እንኳ በቅርባችን ያሉ ወረዳዎች ላይ ከደሃዋ እናት መቀነት አስፈትቶ የሚበላው የኛው የቤተሰብ አካል አልያም ጎረቤታችን ነው፡፡ እንደውም እኮ ሌብነትን በአባባልም እንደግፈዋለን፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› ስለዚህ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የእርሱ ያልሆነን ነገር ማገበስበስ መልካም እንደሆነ እንጂ ጎጂነቱን ያላሳየነው ያልቀረጽነው ትውልድ እንዴት እጁ ንጹህ ሊሆን ይችላል?፡፡ ከቤተሰብ እስከ ማህበረሰብ በጥቅሉ ትውልድን በመልካም ጎዳና የመምራት ከዛም አልፎ ለአንድ አገር ከማህበራዊ እስከ ፖለቲካዊ ለውጥ የማምጣት አቅም ያለው ኪነጥበብ ነው፡፡
መቼም ብዙዎቻችን የቻርሊ ቻፕሊን በእንቅስቃሴ የታጀቡ አስቂኝ ትዕይንቶች ተመልክተናል፡፡ ቻርሊ በፊልሞቹ የካፒታሊዝም ስርዓትን በሰፊው በመተቸት ለደሃው ህብረተሰብ የቆመ ጥበበኛ እንደሆነም እንዲሰማኝ የሚያደርገኝ ይኸው ነው፡፡ ኪነጥበብ ትውልድን ከመቅረጽ አልፎ ለአገራዊ ለውጥ ትልቅ ፋይዳ አለው ያልኩትም ለዚሁ ነው፡፡ ወደ አገራችን የጥበብ ሥራዎች ደግሞ ልምጣ፡፡ ዕውነት ነው በአገራችን በርካታ ትውልድ የማይረሳቸው ጥበበኞች ተወልደው አልፈዋል፡፡ ወደፊትም በሥራዎቻቸው ስንዘክራቸው እንኖራለን፡፡ አሁንም ደግሞ በተለያዩ ሥራዎቻቸው የማንወደውን እንድንወድ የማድረግ ኃይልን የተጎናጸፉና የአስተሳሰብ አድማሳችንን ያሰፉልን ብዙዎች እንዳሉ አልክድም፡፡ በቤታቸው ውስጥ አጋጣሚውን አጥተው ከሥራዎቻቸው ጋር እየተያዩ የሚኖሩም እንዲሁ፡፡
ምቹ ሁኔታ ስላላቸው ብቻ ደግሞ አጋጣሚውን ተጠቅመው ከባህር ማዶ የዘረፏትን የሚያስ ኮመኩሙን የፊልም ባለሙያዎች፣ ዘፋኞች እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃኖች የአየር ሰዓት እየገዙ ፕሮግራሞችን የሚያስተላልፉልን ዕውቅ ሰዎች እየበዙልን ነው፡፡ በዚህ መሰል ተግባር ታዲያ በሥራዎቻቸው የምናደንቃቸው የምናከብራቸው የምንወዳቸው ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነው ስናያቸው ቆይ ግን ለምን ይህን መሰል ሥራ ይሰራሉ? የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡ ከሰራቂው በላይ የድርጊቱ ተባባሪ የሆኑት ደግሞ አሉን የምንላቸው ባለሙያዎች መሆናቸው ሀዘንን ይጭራል፡፡ ከፊልሞቻችን ውጪም በዘፈኖች ላይ በቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ ደግሞ እኮ ግርም የሚለው ራሳቸው ከባህር ማዶ እየቀዱ የሚሰሩት ሥራ እንዳይቀዳባቸው ማስጠንቀቃቸው ነው፡፡ ‹‹የሌባ ዓይነደረቅ…›› አይደል አባባሉስ፡፡
የድርጊቱ መብዛትም የኪነጥበብ ባለሙያዎቻችን ‹‹ቱባ ባህል›› አለን የሚለውን አባባል ለመድረክ ንግግር ብቻ ነው የሚጠቀሙባት እንዴ ያስብላል፡፡ በአገሪቱ ያልተሰሙና ያልተደረሰባቸው ባህሎች ከማሳየት ይልቅ የኪነጥበብ ባለሙያዎቻችን የስርቆትን ደጅ የመጥናታቸው ምክንያቱ አልገባሽ ይለኛል፡፡ ይህ አንድም ተመልካችን የመናቅ አባዜ የሚመስል ድርጊት በተለያየ መልኩ የሚገለጽ በመሆኑም ዘፈንና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞቻችን ላይ ቅኝቴን በሰፊው በሌላ ጊዜ ይዤላችሁ እንደምመለስ ቃል እየገባሁ ለዛሬ ግን በአንድ ፊልም ላይ አተኩሬ ላስቃኛችሁ፡፡
አዲስ የአማርኛ ፊልም ወጣ ሲባል በሲኒማ ደጃፍ ተሰልፈው ከሚመለከቱት ውስጥ ነኝ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው ያየሁትን የባህር ማዶ ፊልም በቋንቋዬ ሰርተው ልቤን ሰብረው እመለሳለሁ፡፡ እኔም ተስፋ አልቆርጥ ደጋግሜ ተሰልፌ እገባለሁ እመለከታለሁኝ፡፡ በ1990ዎቹና ቀደም ያሉ አልያም ቀረብ ያሉ እንግሊዝኛ ፊልሞች በራሴው ሰዎችና ቋንቋ ተሰርቶ የቀረበልኝን ፊልም አይቼ እወጣለሁ፡፡ ፊልሞቹን ቀደም ብዬ ተመልክቻቸዋለሁና በድጋሚ በአማርኛ ስመለከታቸው ቀጣይ ምን እንደሚሆን እያወኩኝ ነው፡፡ ይህን ስል መቼም አቋርጣ ለምን አትወጣም? እንደምትሉ አልጠራጠርም፡፡ ግን ገና ለገና አዲስ ነገር ጨምረውበት ይሆን ብዬ በጉጉት አየዋለሁ፡፡ አገራችንም ቴክኖሎጂን በመቅዳት ላይ አተኩራ ትሰራለችና ለእኛ በሚጠቅም መልኩ የተጨመረበት ነገር ይኖር ይሆናል በሚል ተስፋ ቁጭ እላለሁ፡፡ ግን መጨረሻውን የማውቀው ያው ፊልም ሆኖ ያርፈዋል፡፡ ከጅማሬ እስከ መጨረሻ ተመሳሳይ ታሪክ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ አይቼ እወጣለሁ፡፡
በቅርቡ ታዲያ አዲስ የወጣ የአማርኛ ፊልም ተመለከትኩ፡፡ ምንም እንኳ ይህን ፊልም የሥራ ሁኔታዬ ሳይፈቅድልኝ ቀርቶ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ተሰልፌ ባልመለከተውም በጣም ላየው ከፈለ ኳቸው ውስጥ ግን አን ዱ ነበር፡፡ እናም ሳል መለከተው ከሲኒማ መውረዱን እንደሰማሁ ነበር ወዲያውኑ በበየነ መረብ ላይ የተመለከትኩት፡፡ በፊልሙ ላይ በመሪ ተዋናይነት የሚሳተፉት ከነባሮቹ እጅጉን ታዋቂ የሆነው የምናከብረው ሰለሞን ቦጋለ ሲሆን፤ ሌላኛዋ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ካሉ ታዳጊዎች ተርታ ሆኗ ዕውቅና እያገኘች ያለችው ዮአዳን ኤፍሬም ናት፡፡ አልማዝ ኃይሌና አብራር አብዶም በዚሁ ፊልም ላይ ይተውኑበታል፡፡ ይህም ፊልሙን ገና ሳልመለከተው ጥሩነቱን እንድገምት ካደረገኝ ምክንያት ውስጥ ይካተታል፡፡
‹‹አብ’ሳላት›› የፊልሙ መጠሪያ ሲሆን፤ ታሪኩ አንድ አባት ያለ እናት በማቀማጠል የሚያሳድጋት ልጁ ሕይወት ላይ ያጠነጥናል፡፡ ጥቂት ደቂቃዎችን እንደተመለከትኩኝ ፊልሙ ከባህር ማዶ ሙሉ በሙሉ የተቀዳ እንደሆነ አወቅኩኝ፡፡ ፊልሙ የተወሰደው “If Only” ከተሰኘው የእንግሊዝኛ ፊልም ነው፡፡ አማርኛውም ሆነ እንግሊዝኛው ፊልም የሚያጠነጥነው የሚመጣውን የማወቅ “Deja vu” ላይ ነው፡፡ በእንግሊዝኛው ላይ በሁለት ፍቅረኛሞች የተሰራው ታሪክ በተመሳሳይ መልኩ በአማርኛው ላይ አባትና ልጅ ተደርገው ይጫወቱታል፡፡
እአአ በ2005 የተሰራውና ጄኔፈር ላቭ ሄዊት በመሪ ተዋናይነት የምትጫወትበት ታሪክ ከጅማሮው እንዲህ ነው፡፡ ሥራ ሥራውን የሚለው ፍቅረኛዋ እርሷ በሕይወቷ የሰጠችውን ቦታ ሳይሰጣትና ትኩረት ሲነፍጋት ይታያል፡፡ ሁልጊዜም ነገሮችን በትክክለኛ ጊዜያቸው ከማድረግ ይልቅ እንዳረፈደ ነው፡፡ እናም የሙዚቃ መምህርት የሆነችውና በተማሪዎቿ እጅግ ተወዳጇ ፍቅሩ በነበራት ትልቅ ፕሮግራም ላይ ይዘገያል፡፡ ወደዛው ለማምራት ሲያቀናም ኮንትራት ያሳፈሩት አሽከርካሪ ከዛን ዕለት በፊት አይቷቸው ባያውቅም ስለ ሕይወቱ ግን ይነግሩ ታል፡፡ እናም በፍቅር ሕይወ ቱ ያለበትን ችግር ያነሱለትና ዛሬን ብቻ እንደምትኖር አድርገህ ውደዳት በሚል ትልቅ ምክርን ይመክሩታል፡፡ እርሱም ምክሩን ተቀብሎ ወደ ስፍራው ይሮጣል፡፡ አርፍዶ መድረሱ ብዙም ያላስከፋት ፍቅሩን ከስፍራው ቶሎ እንዲወጡ እየጨቀጨቀ አላስቆም አላስቀምጥ ይላታል፡፡ ራት እየበሉም ስለግንኙነታቸው ብትጠይቀው የሰጣት ምላሽ ልቧን ይሰብረዋል፡፡
አንድ ቀን እንኳ ለሁለታቸው የሚሆን ጊዜ ካለ ብላ በትዕግስት የጠበቀችው ፍቅሩ በእንባ እየታጠበች ጥላው ትወጣለች፡፡ ከውጭ የቆመ ኮንትራት አገልግሎት የሚሰጥ ታክሲ ውስጥ በመግባትም ይገባ እንደሆነ ትጠይቀዋለች፡፡ እርሱ ግን ያመነታል፡፡ ከሰዓታት በፊት ምክር የለገሱት በዕድሜያቸው ጠና ያሉ አባት ዳግም ፍቅሩን ጭነው ትመጣለህ ወይስ ልትቀር አሰብክ የሚል ጥያቄን ያቀርቡለታል፡፡ እርሱ ግን እዛው ሳይገባ ይቆማል፡፡ እንባዋን አርግፋ የተለየችው ፍቅሩን የያዘው ተሸከርካሪ ጥቂት እንደተጓዘ ይጋጭና ሕይወቷ ያልፋል፡፡ እናም እንደዛው በሃዘን እንደተቆራመደ ከእንቅልፉ ሲነቃ የፍቅሩን ድምጽ ዳግም ይሰማዋል፡፡ በሆነው ሁኔታም ይደናገጣል፡፡ ነገር ግን እንደዛ ሲያስጨንቀው የነበረ ህልም መሳይ ዕውነት ዳግም ይከሰትበታል፡፡ እርሱም ያየውን ዕውነት ለመቀየርና ፍቅሩን ከሞት ሊያድን የሚያደርገው አጣብቂኝና ጭንቀት የተሞላበት ትዕይንት ያሳያል፡፡
በፊልሙ ላይ በምድር ላይ በተሰጠን ጥቂት ጊዜ ዛሬን ማደራችንን አናውቅምና ደስተኛ ሆነንና ለሌሎች ኖረን ማለፍን ያስተምራል፡፡ እንዲሁም የምንፀፀትበት ውሳኔ ከመወሰንና ከማርፈድ መቆጠብ እንዳለብን ያሳያል፡፡ ይህን ሙሉ በሙሉ የወሰደው አማርኛ ፊልማችን ‹‹አብ’ሳላት›› ታዲያ አያውቁትም ብለው ሰርቀው ማቅረባቸው ልብን ከመስበር በላይ ምን ስያሜ ሊሰጠው ይችላል?፡፡ የእነርሱ የልፋት ውጤት ባልሆነ ሥራ ጊዜያችንን ብሎም ገንዘባችንን ከመመዝበራቸው አልፎ ሥነልቦናችንንም ይጎዱታል፡፡ ይህን እንደው እንደማሳያ አነሳሁ እንጂ በዘፈኖች እንዲሁም በፊልሞች ላይ ቅጂ ተንሰራፍቷል፡፡ ተግባሩ ሆን ተብሎ እንደሚፈፀም ማሳያው ደግሞ አንዳንዶቹ ላይ ጭራሽ ከአንድ ፊልም አልፈው ሶስትና አራት ፊልም ጨምቀው አንድ አማርኛ ፊልም ያቀርቡልናል፡፡ “The Vow” “Remember Me” እንዲሁም “The Note Book” ከሚሉ ፊልሞች ሀሳቦችን ወስዶ ለዕይታ የቀረበው ‹‹ላስታውስሽ›› ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡
ወደ አነሳሁት ሃሳብ ስመልሳችሁ በአገራችን ዕውነትም እንደሚባለው ቱባ ባህል አለን፡፡ ገና ያልተነኩ በርካታ ሥራዎችም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥ ባለሙያዎቻችን አገራቸውን አማትረው የተደበቁ ባህሎችን ወግና ትውፊቶችን አውጥተው የሚታወቁትንም አጉልተው ከመሥራትና ሌሎች ወደ እኛ መመልከት እንዲችሉ የሚያደርግ ሥራ ከመሥራት ይልቅ ባህር ማዶ ልባቸው ቀድሞ ሄዷል፡፡ እና እስኪ ሁሉም በዚህ መልኩ በስርቆት ተሳታፊ እየሆነ እንዴት ትውልዱን ከታች ከፈተና ከሚጀመረው የኩረጃ ስርቆት ልንታደገው ከፍ ብሎም ስርቆት አገር አጥፊ እንደሆነ ልናስተምረው ይቻለናል?፡፡
ትውልዱ በሁሉም መስክ የምናስተምረው ሌብነትን ሆኖ መልካም ዜጋን መጠበቅ ዳጉሳ ዘርቶ ማኛ ጤፍ እንደመጠበቅ ይሆናልም ባይ ነኝ፡፡ በመሆኑም የተሻለ ትውልድን ለማፍራት ሁሉም የሌሎችን ችግር ብቻ ከማጉላት ይልቅ የራሱ ድርሻ ለይቶ ከችግር ፀድቶ የቀጣይ የአገሪቱን ተረካቢ ዜጎች የሚቀረፁበትን ጎዳና ሊጠርግ ይገባዋል መልዕክታችን ነው፡፡ ለወዳጅ ዘመዶቼ ሁሉ ጥሩ ፊልም ብዬ እንዲመለከቱት ከምጋብዛቸው ውስጥ አንዱ የሆነውን ዋናው “If Only” የተሰኘውን የእንግሊዝኛ ፊልም በመጋበዝ ላብቃ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8.2011
ፍዮሪ ተወልደ