ፕሬዚደንት ሊንደን ቢ ጆንሰን እ.አ.አ በ1930 የአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ኮንግሬስ ማን ሆነው በመመረጥ ወደ ነጩ ቤተመንግስት የገቡት በወጣትነት ዘመናቸው ነበር ይባላል፡፡ ኮንግረስማኑ በወቅቱ ለምክር ቤት አባልነት ተመርጠው ቢመጡም በኋላ የኃያሏ ሀገር አሜሪካ ታላቅ ሰው ወይም ፕሬዚደንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ በስልጣን ዘመናቸው በሀገሪቱ ታሪክ በአዎንታዊነት ሊጠቀሱ የሚችሉ አሻራዎችንም አኑረዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ በ1970ቹ ዓመታት የስልጣን ዘመናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ አንድ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ” ክቡር ፕሬዚደንት በፕሬዚደንትነት ዘመንዎ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ምን ለውጥ መጣ?” የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው እንደነበረ ይነገራል፡፡
ፕሬዚደንቱም ለጠያቂው የሰጡት ምላሽ ” በመገናኛ ብዙኃን ውስጥ ላላችሁ፣ሁላችሁም የምለው ነገር ቢኖር የሀገራችን ፖለቲካ ወደ በጎ አቅጣጫ የተለወጠው በናንተ አማካይነት ነው፡፡ በም/ቤቶቻችንና በከተሞቻችን መካከል የነበሩትን የልዩነት መጋረጃዎች በመቅደድ አዲስ ሰዎችን ፈጥራችሁልናል፡፡ እነርሱም በናንተ የተቀረጹና የናንተ ፍጡራን ናቸው” ብለው ነበር፡፡ፕሬዚደንቱ መገናኛ ብዙኃን በዘመኑ የተጫወቱትን ሚና የሚያጎላውን አስተያየት የሰጡት ጋዜጠኞች በሀገረ አሜሪካ ይጫወቱ የነበረውን አዎንታዊ ሚና በትክክል በማመዛዘን ይመስለኛል፡፡ በእርግጥም ነው፡፡ አንባቢም ይህንኑ እንደሚጋራ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡
እንደ አንድ በጎ አሳቢ ኢትዮጵያዊ ራሴን ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ አርቄ ሳማትር ዘመኑ የኢትዮጵያዊነት ስለመሆኑ በእርግጠኝነት ብሩህ ተስፋ ጎላ ብሎ ይታየኛል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሀገርና ኢትዮጵያውያን ደግሞ እንደ ህዝብ ዳግም የተወለዱበት፣ ዳግም ከፍ ያሉበትና ዳግም የታደሱበት ዘመን መጀመሩም እየተበሰረ ነው፡፡ ይህም ትንሣኤ በመላ ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ በፍቅር የተሞላ፣ በአንድነት የታጀበ፣ አሳታፊና በጋራ ስለ ጋራ ሀገራችን የምናስብበት ይሆናል፡፡
በዓመቱ አዳዲስ ሀገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ይፋ ይሆናሉ ተብሎ ስለሚጠበቅም ሰላም፣ እርቅ፣ ፍቅር፣ ምህረትና አንድነት ለመጀመሪያ (ለመጀመሪያ ጊዜ የሚለው አባባል በሀገራችን ፋሽን የተደረገ ቢሆንም) ጊዜ በይፋ የታወጀበትና ከሁሉም ነገር በላይ ደግሞ የተወደሰበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ጣፋጭ ንግግሮች የተበደለም ሆነ የበደለ በጋራ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት ከመበቃቀል ይልቅ መፈቃቀርን መሠረት ባደረገ ሁኔታ በህይወት አብረው መኖር ሲችሉ እንደሆነ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በህትመት ሚዲያ በየደቂቃዎቹ ይሰራጩ በነበሩና ልብን ብቻ ሳይሆን አጥንትን ሰርስራው ይገቡ በነበሩ መልዕክቶች የደስታ ሣቅና ለቅሶ እየተፈራረቀብን ስለመከታተላችን ሁላችንም ምስክሮች ነን፡፡ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ወገኖቻችንና ሀገራችንን የሚወዱ ወዳጆቻችን ሁሉ ልባዊ መቀራረብን፣ አድናቆትንና የተሟላ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን የፈጠሩበት ጊዜ ተደምሮና ደምቆ መጥቶልናል፡፡
በክርስቲያኑም ሆነ በሙስሊሙ፣ በተፎካካሪዎችም ሆነ በደጋፊ ፖለቲከኞች መካከል በሀገራዊ ስሜት ፍቅር የታወጀበት ዘመን ነው ብሎ በይፋ መናገርም መነጋገርም ተጀምሯል፡፡ ይህንን ረጅምና አድካሚ የአንድነትና የፍቅር ጉዞ እየተራመድን፣ የአንድነትና የሰላም መዝሙር እየዘመርን፣የመከባበርንና የመቻቻልን ዘፈን በጋራ እየዘፈንን በልበ-ሙሉነት ወደፊት መራመድ የሚጠበቅብን ይመስለኛል፡፡ ይህንን ጉዞ በአንድነትና በፍቅር ካልተጓዝን አዲስ ዘር መዝራት፣ ማብቀልና ማጨድ አንችልም፡፡ ብናበቅልም በጭንጫ ላይ የበቀለ ዘር ስለሚሆን የምንፈልገውን ዐይነት ወይም መጠን ምርት አናገኝም፡፡ አዲስ ትውልድ መፍጠርም ሆነ ማነጽ አንችልም፡፡ እኛ የምንለው አስተሳሰብ ብቻ ትክክል ስለሆነ በግድ ተቀበሉን በሚል ፈሊጥ የማንፈልገውን ወከባ “ከምንፈልገው በላይ” ሲጭኑብን ከኖሩና ለዝንተ-ዓለም ሊጭኑብን ከሚፈልጉ ከደነዘዙ አንደበቶች ራሳችንን “ነጻ መውጣት የጀመርንበት” ወቅት እንደሆነም ከጅምሩ መረዳት እንችላለን፡፡
ውሸትን እውነት በማስመሰል ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንዳትኖርና መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ለዝንተ-ዓለም ደኃና ተመጽዋች ሆኖ እንዲኖር በአደባባይ ላይ ደባ ሲሰራብን ኖሯል፡፡ በተባረከ የኢትዮጵያ ምድርና በተወዳጁ የኢትዮጵያ ህዝብ መካከል እየኖሩ ይህንን ዘመን አይሽሬ በደልና ሴራ መፈጸም በምድርም በሰማይም ተቀባይነት የሌለውና ቀጣዩ ትውልድ በዚህ ሁኔታ ላለመከተል ቃል የሚገባበትና በጥንቃቄ ሊያወግዘው የሚገባ ሂደት መስሎ ይታየኛል፡፡ ይህንን ሚና ለመጫወት ደግሞ መገናኛ ብዙኃን ትልቅ አቅምም ኃይልም ኃላፊነትም አላቸውና፡፡ መኖር ብቻ ሳይሆን የመጫወትም ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህንን ድርሻ ለመወጣት ግዴታ እንደሌለባቸው አድርገው የሚከራከሩ “ልህቃን” እንዳሉ ባውቅም እኔ ግን መገናኛ ብዙኃን ሲባሉ ብቻቸውን ሜዳ ላይ የሚሮጡ ተቋማት ሳይሆኑ በህብረተሰቡ መካከል የሚኖሩና ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ አሰራሮችን ይከተላሉ የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን ክርክር እንደሚያስነሳ እረዳለሁና እስቲ መማማር የሚያስችል አስተያየት እንለዋወጥ፡፡
ዛሬ በሀገራችን የተጀመረው ጉዞ ጅምሩ ለኔ በግሌ የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣድ ያስታውቃል ከሚባለው በላይ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ከሰዎች ጋር ሳወራ፣ ጋዜጣ ሳነብ፣ቴሌቭዥን ስመለከት ሬዲዮ ሳዳምጥ፣ወዘተ….ወዘተ የጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ወኔና ስሜት እየተሰማኝ መጥቷል፡፡ ስሜቱ የሁላችንም መሆኑን ዘነጋሁ ልበል ይሆን!? እንዴት ተደርጎ!! እያንዳንዳችን እንደ ግለሰብ፣ እንደ ቡድን፣ እንደ ማህበረሰብ በሰላም አድረን፣ በሰላም ውለን፣ በሰላም ገብተን፣ በሰላም ወጥተን፣ በሰላማዊ ስራ ላይ ሆነን ወደፊት ለመሄድም ሆነ ያለፈውን ታሪክ ወደኋላ መለስ ብለን ለማየት ከምንም ነገር በላይ መረጃ እንፈልጋለን፡፡ መረጃ ኃያል መሣሪያ ነው፡፡ ከኒውክሊየር የጦር መሣሪያ በላይ ይፈጥናል፤ ከኒውክሊየር የጦር መሣሪያ በላይ ያጠፋል፡፡ ያወዛግባል፡፡ ያጣላል፡፡ ያስታርቃል፡፡ በዕውቀትና በአግባቡ ከተጠቀምን ደግሞ የሰው ልጆች የሰላም፣ የአንድነት፣ የመገነባባትና የደህንነት ቁልፍ መሣሪያ በመሆን ያዋህደናል፡፡ ያግባባልም፡፡ መረጃ በዕውቀትና በወቅቱ ከተጠቀምነው ሀብትም፣ ህይወትም፣ ደህንነትም በመሆን ነፍስ ይዘራል፡፡ መረጃ ድልድይ በመሆን በቃላት ወይም በቋንቋ ከምናውቀው በላይ የብስና ውቅያኖስ ያሻግራል፡፡ ከሀገር ወደ ሀገር ሰላማዊ ተግባቦትን መፍጠር የሚያስችል ድንበር ተሻጋሪ ወዳጅነትን ይመሠርታል፡፡
ጠቢቡ ሰለሞን በመጽሐፈ ምሳሌ እንዲህ ብሎ ነበር፡- ” ሞትና ህይወት በምላስ እጅ ናቸው፡፡ የሚወዷትም ፍሬዋን ይበላሉ፡፡” እነዚህ በጠቢቡ ሰለሞን ጭምር የተነገሩ ቃላቶች በምላስ አማካይነት የሚወጡ ቃላቶች ናቸው፡፡ ቃላቶቹ ያዘሉት ደግሞ መልዕክቶችን ወይም መረጃዎችን ነው፡፡ መረጃዎችን የሚያሰራጩት ደግሞ የመረጃ ባለሙያዎች በዋነኛነትም ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ ጋዜጠኞች ተጠሪነታቸው ለህዝብ ነው፡፡ ይህንን ተጠሪነት ደግሞ ሌሎች “የህዝብ ተጠሪዎች” ወይም ወኪሎች ነን የሚሉ አካላት በሆነ መንገድ ” እየነጠቁባቸው ነው” ማለቱ ሌላ ትርጉም ያሰጠኝ ይሆን! ትክክለኛውን ጭብጥ ለማንም ለምንም ሳያዳሉ በህዝባዊ ወገናዊነት እንዳያንጸባርቁ ጫና ይፈጠርባቸዋልና፡፡ በራሳቸው የህሊና ዳኝነትና ነጻነት እንዲሰሩ ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ጋዜጠኞች በራሳቸው የህሊና ዳኝነት በተለይም ደግሞ በነጻነት መስራት አለባቸው ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ሃሳቡ አከራካሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ፍጹም ነጻነት (ቶታል አብሶሉቲዚም) የለም የሚለው ደግሞ ሁላችንንም ያስማማናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በህብረተሰቡ መካከል እየኖርን ወደ ህብረተሰቡ በማንኛውም የመገናኛ መሣሪያ የምናሰራጫቸው መረጃዎች በአንድም ወይም በሌላ መንገድ አንዱን ጎንተል ማድረጉ አይቀርምና ነው የነጻነቱ ጉዳይ አከራካሪ የሚሆነው፡፡ ወደንም ሆነ ሳንወድ በራሳችን ህሊና ትክክል ነው ብለን በምናስበው ጭብጥ ላይ (እንደየ ብስለታችን) ስለምንዘግብ ህብረተሰቡ ጋዜጠኛው ያደላል ወይም የተዛባ መረጃ አሰራጭቷል ወደሚያሰኝ ድምዳሜ ሊደርስ ይችላል፡፡ ይህንን ደግሞ በሚታይና በሚጨበጥ መረጃ ማረጋገጥ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ይቻላልም ደግሞ፡፡
ኢትዮጵያዊነት የመገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ይሁን ሲባል ዘመኑ ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ሌሎች ደባል አጀንዳዎችን ይዘን መራመድ ለሁላችንም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እያመዘነ ስለመምጣቱ እኛው ራሳችን በዕድሜያችን እማኞች ሆነን እያየን ነው፡፡ ባለቤት አልባ መረጃዎች ከባላቤት አልባ ቋቶች በተለይም ደግሞ በፌስ ቡክ አማካይነት እየተነበቡ ህዝቡ ትክክለኛውንና ትክክል ያልሆነውን ለይቶ ማወቅ ወደማይችልበት ( ለነገሩ አሁን እየጠራ ቢሆንም ) ሁኔታ እየመራ ነው፡፡ አንብቦ ማመዛዘን ለሚችልና በአካዳሚያዊ ዕውቀቱ ለበሰለ ሰው ብዙም አስጨናቂ ላይሆን ይችላል፡፡ በተለይም እውነትንና ውሸትን አንጥሮ በማያውቀው ህብረተሰብ መካከል ነጩ ጥቁር፣ ጥቁሩ ቢጫ እየሆነ ነው፡፡
በሀገራችን እየመጣ ያለው ለውጥ ተስፋ የሚያሰንቅ ሆኖ እያለና አብዛኛው ከሚባለው ህዝብ በላይ የሚደግፈው ሆኖ ምንም በማያውቁ በተለይም ወጣቶች ዘንድ የውሸት ናዳ እያወረዱ ሰላም ማሳጣት፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ መረጋጋት እንዳይኖር ማድረግ፣ የኢትዮጵያዊነት መጠናከር የእግር እሳት ለሆነባቸው ወገኖች መሣሪያ መሆን መስዋዕትነት ሳይሆን ህዝብን መበደል ነው፡፡ ይህንን አጀንዳ ለህዝቡ ማሳወቅ የመገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ይሁን ማለት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለሀገራችን ደህንነትና የህዝቦች አንድነት ጠቃሚ ያልሆኑ መረጃዎች እያመረቱ ለሚያድሩና ለሚውሉ ግለሰቦች/ቡድኖች መሣሪያ መሆን ከምንም ነገር በላይ የህሊና ወንጀል ነው፡፡
ይህንን እውነታ በየጊዜው ለህብረተሰቡ ማሳወቅ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ግዴታም ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ወቅታዊ አጀንዳም መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሊመጣ የሚችለው ለውጥ ሁሉ እንደ ቀድሞው በፉከራና ቀረርቶ ሳይሆን በፍቅር፣በሰብዓዊነት፣ በመቻቻል፣በኢትዮጵያዊነት መሆን እንዳለበት ሚዲያዎቹ መስራት አለባቸው፡፡ ከዚህ ውጪ የሚመጣውን ግድያ፣ዝርፊያ፣ዘለፋ፣ ነውጠኝነት፣ የመንጋ ፍርድ፣…እኛ እርስ በርስ በታሪክ ያልነበረብንን ጥላሸት መቀባትና መተላለቅን የሚያስከትል ስለመሆኑ እያስተዋልን ነው፡፡ መጻፍና የሚጻፈውን ጭብጥ አንጥሮና አብጠርጥሮ ማወቅ ይገባናል፡፡ የዜግነትና የሰብዓዊ ፍጡርነት ግዴታ ነዋ! ኢትዮጵያዊነትም የመገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ይሁን! አካባቢያዊና ሀገራዊ ህገ ወጥነት ወደ አስተማማኝና ትክክለኛ መረጃ አዘል ሀገራዊ አንድነት ይመለስ፡፡ እስከሚቀጥለው ሰላም እንሁን፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8.2011
ወ/አማኑኤል ጉድሶ