በአንድ ድርጅት ውስጥ 30 ሠራተኞች ያሉት አሠሪ ነበር። ሠራተኞቹ ወጣቶችና ታታሪ ቢሆኑም ተባብሮ የመሥራት ልምዳቸው ዝቅተኛ ነበር። እንዲሁም አዳዲስ ሃሳቦችን ቶሎ ለመቀበል እና ለመማርም ዝግጁ ቢሆኑም እውቀታቸውን አስተባብሮ ለአንድ ዓላማ በማዋል ረገድ ክፍተት ስለነበረባቸው የድርጅቱን ባለቤት ያሳስበው ነበር።
ከዕለታት በአንዱ ቀን አሠሪው ሠራተኞቹ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ተባብሮ መፍትሔ እንዴት መፈለግ እንደሚችሉ ሊያስተምሯቸው ስልጠና አዘጋጀላቸው። ሠራተኞችም በሃሳቡ ተስማሙና የስልጠናው ቀን ተወሰነ፡፡ በስልጠናው ቀን አንድ ጨዋታ እንደሚጫወቱ ተነገራቸው። ሠራተኞቹ ስልጠና እንጂ ጨዋታ ለመጫወት ባለመዘጋጀታቸው ግራ ተጋቡ።
የስልጠናው አዳራሽ በጣም በሚያምሩ ቀለማት የተዋበና አየር የተሞላባቸው በርካታ ፊኛዎች ያጌጠ ነበር። አዳራሹ ስብሰባ ከማስተናገድ ይልቅ ለጨዋታ የሚመች ሆኖ ነበር የተዘጋጀው። ሁሉም ሠራተኞች በነገሩ ስለተገረሙ እርስ በእርስ በመንሾካሾክ ላይ ነበሩ።
ሁሉም ሠራተኞች ወደ አዳራሹ ገብተው አንድ አንድ ፊኛ እንዲያነሱና እንዲያፈነዱት ተነገራቸው። ሁሉም ሠራተኞች በታዘዙት መሰረት የያዙትን በአየር የተሞላ ፊኛ እንደታዘዙት አፈነዱት። ሁኔታው በጣም የሚያዝናና ነበር። በድጋሚ ተመሳሳይ ፊኛ እንዲያነሱ እና በእስኪቢርቶ እላዩ ላይ ስማቸውን እንዲፅፉ ታዘዙ። ፊኛው እንዳይፈነዳም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተነገራቸው።
ሁሉም የጨዋታው ተሳታፊዎች በያዙት ፊኛ ላይ ስማቸውን በጥንቃቄ ለመጻፍ ሲሞክሩ ፊኛው በአየር ስለተወጠረ አብዛኛው በመፈንዳቱ የተወሰኑት ስማቸውንም ሳይፅፉ ቀሩ። ፊኛው ለፈነዳባቸው ሠራተኞች በድጋሚ ዕድል ተሰጣቸው። ለሁለተኛ ጊዜ ዕድል ቢሰጣቸውም ያልተሳካላቸው ነበሩ፡፡ በድጋሚ ዕድል ተሰጥቷቸው ስማቸውን መጻፍ ያልቻሉት በጨዋታው ህግ መሰረት ከውድድሩ ተሰረዙ።
በሁለተኛው ዙር ስማቸው የተጻፈበት ፊኛን በመሰብሰብ፤ በአንድ ከፍል ውስጥ እንዲቀመጥ ተደረገ። ከዚያም ለሁለተኛው ዙር ላለፉት ሠራተኞች እንዲህ የሚል ትዕዛዝ ተሰጣቸው «ፊኛው በተቀመጠበት ክፍል ትገቡና ስማችሁ የተጻፈበትን ፊኛ ብቻ ታነሳላችሁ። ፊኛዎቹ መፈንዳት የለባቸውም» በማለት አስጠነቀቃቸው። ሁሉም ሠራተኞች ፊኛው በሚገኝበት ክፍል ውስጥ ገብተው ስማቸው የተጻፈበትን ፊኛ ለማግኘት በጥንቃቄ መፈለግ ጀመሩ። ክፍሉ ጠባብ እና በፊኛ የተሞላ በመሆኑ የራሳቸው ስም የተጻፈበትን ለማግኘት አስቸጋሪ ሆነባቸው። ብዙ ፊኛዎች ፈነዱባቸው። የራሳቸውን ስም ለማግኘት ባደረጉት ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ ረጅም ደቂቃ በመውሰዱ የተሰጣቸው ጊዜ ሲያልቅ ስማቸው የተጻፈበትን ፊኛ ለማግኘት አልቻሉም ነበር።
ሦስተኛ ዙር የጨዋታ ህግ ምን እንደሚሆን ለማወቅ ጉጉት አደረባቸው። አሠሪያቸው እንዲህ አላቸው «አሁን ሁላችሁም ክፍል ውስጥ ትገቡና ያገኛችሁትን ፊኛ በማንሳት ስሙ ለሚመለከተው ሰው ትሰጡታላችሁ» ሁሉም ሠራተኞች ከፊት ለፊታቸው ያገኙትን ፊኛ በማንሳት የተፃፈውን ስም ተመልክተው ለጓደኛቸው መስጠት ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ፊኛዎቹን በፍጥነት ለሁሉም ደረሱ። ሁሉም በሁለት ደቂቃ ውስጥ የራሳቸው ስም ያለበትን ፊኛ ማግኘት ቻሉ። በነገሩም በጣም ተደነቁ።
አሠሪው ጨዋታው ማለቁን አሳውቆ «ይህ ማለት ለችግሮቻችን ትክክለኛውን መፍትሔ የምናገኝበት መንገድ ነው። ሁላችንም ነገሮችን ሳናገናዝብ በራሳችን ጥረት ብቻ መፍትሔ እንፈልጋለን። መገንዘብ ያለብን ነገር፤ እርስ በእርስ በመረዳዳት እና ነገሮችን በመጋራት፤ ለችግሮች መፍትሔ ማምጣት እንደምንችል ነው» በማለት አስተማራቸው። ሁሉም ሠራተኞች በሁኔታው ተገርመው ትክክለኛውን መፍትሔ ስላገኙ ተደሰቱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመስሪያ ቤታቸው በመደጋገፍ እና በጋራ በመሥራት ስኬታማ ሆኑ። ድርጅቱንም ትርፋማ አደረጉት።
ይህ ለብዙዎቻችን ትልቅ ትምህርት ያለው ጨዋታና ስልጠና ነው። ከጨዋታው በላይ የተላለፈው ትምህርት በሁላችንም ህይወት ይሠራል። ምክንያቱም ሀገር በአንድ መስሪያ ቤት ትመሰላለች። የብዙ አሠሪዎችም ሆኑ መሪዎች የሠራተኞቻቸውን የሥራ ባህሪ የመረዳት ክፍተት ይታይባቸዋል። ሠራተኞችም ለአንድ ዓላማ በሚደረገው የሥራ ክፍፍል ውስጥ ከመተባበር ይልቅ ራሳቸውን ደብቀው ይታያሉ። ራሳቸውን ከሌሎች ባልደረቦቻቸው የተሻሉና የላቁ ሆነው ለመገኘት ሥራቸውን በተናጠል ያከናውናሉ። ይህ ደግሞ የግለሰብ እውቅና እንጂ የድርጅትን ትርፋማነት ወይም ውጤታማነት ለማምጣት የሚያስችል አይሆንም። አንዱ የሠራውን መልካም ሥራ ከመደገፍ ይልቅ ለማፍረስ የሚበረቱም አይታጡም።
ሰሞኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲህ ብለው ነበር፤ «ይህ ህዝብ አብሮ ኖሯል፤ ተዋልዷል፤ ደም አስተሳስሮታል እና! ይህ ቀን አልፎ ነገ አብሮ መኖሩ ስለማይቀር መሪና ድርጅት ያልፋሉ ህዝብና ታሪክ ግን በዘመናት መካከል ይቀጥላሉና በሚያልፍ የመሪነት ዘመናችን የማያልፍ የታሪክ ጠባሳ እንዳንተው ልንጠነቀቅ ይገባል›› በርግጥም ከመተባበር ውጪ አማራጭ አይኖርም።
ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለአንድ ዓላማ በአንድ መንፈስ ተባብረው ሲሠሩ ብቻ ነው ዕድገትና ብልጽግና ሊያስመዘግቡ የሚችሉት። ካልሆነ ግን የቱንም ያህል የጥቂቶች ጥረት ሀገርን አንደ ሀገር ሊያሳድጋትና ሊያበለፅጋት አይችልም። አንዱ ለሀገሩ ተቆርቁሮ ተግቶ ሲሠራ ሌላው የሚዘርፍና የሚያፈርስ ከሆነ ሀገር ልትገነባ አትችልም። በመሆኑም ለጋራ ሀገራችን በጋራ አስበንና ተባብረን ችግሮቿን ተቸግረን፤ በስኬቶቿም አብረን ልንደሰት ይገባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2011
機票 價格比較了一下發現HOPEGOO很便宜,這網站也很方便容易用,有中英文介面。之後會推薦我的朋友來這邊訂!
機票 價格比較了一下發現HOPEGOO很便宜,這網站也很方便容易用,有中英文介面。之後會推薦我的朋友來這邊訂!