• ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሐዘን መግለጫ አስተላልፈዋል
አዲስ አበባ ፦ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ባደረባቸው ህመም በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ህክምና ሲደረግላቸው ቆይተው፤ ታህሳስ 5 ቀን 2011 ዓ.ም በተወለዱ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
በአመራር ብቃታቸውና በአባታዊ መልካም ባህሪያቸው ተወዳሽ የነበሩት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ከ1994 ዓ.ም እስከ 2006 ዓ.ም ለሁለት ጊዜ ኢትዮጵያን በፕሬዚዳንትነት መርተዋል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ታህሳስ 19 ቀን በ1917 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱ ሲሆን፤ በልጅነታቸው የቤተክህነት ትምህርት ተምረዋል፤ በ1926 ዓ.ም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ ዘመናዊ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ በ1936 ዓ.ም ከገነት ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የምክትል ሌፍተናንት ምሩቅ ነበሩ። በ1938 ዓ.ም የኢትዮጵያን አየር ኃይል በመቀላቀል ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ ኮርሶችን ተከታትለዋል።
ከአስራ አምስት ቀን በኋላ 95ኛ የልደት በዓላቸውን ለማክበር ተቃርበው የነበሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ፤ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ በመንግሥታዊ፣ አስተዳደር ስራና ኃላፊነቶች በ1933 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች የሬዲዮ መገናኛ ክፍል ባልደረባ ነበሩ። በ1940 ዓ.ም በአየር መቃወሚያና በረራ መቆጣጠሪያ ማዕከል ረዳት መምህር፣ በ1947 የኤርትራ የሲቪል አቪዬሽን የበላይ አዛዥ፣ በ1951 ዓ.ም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዳይሬክተር፤ በ1953 ዓ.ም የፓርላማ አባልና ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የፓርላማ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በሌሎች መንግስታዊና መንግሥት ያልሆኑ የአስተዳደር ኃላፊነቶችም ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከሰሩባቸው የስራ ኃላፊነቶች መካከልም የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የቦርድ አባል፣ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ ንግድ ልዑክ ወኪል፣ የጊቤ እርሻ ልማት ማኅበር መስራችና ዳይሬክተር፣ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የቦርድ ዳይሬክተርና በዚሁ መስሪያ ቤት በዓለም አቀፍ ሎጅስቲክስ ዲፓርትመንት የበላይ ጠባቂ በመሆን ሀገራቸውን አገልግለዋል። በ1983 ዓ.ም ለም ኢትዮጵያ በተሰኘውና በአካባቢ ጥበቃ ላይ በሚሰራው ማኅበር የቦርድ ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል። ግርማ ወልደጊዮርጊስ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነበሩ፡፡
በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፕሬዚዳንቱ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በኢፌዴሪ መንግሥት እና በራሳችው ስም ገልፀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ «የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የኢፌዴሪ መንግሥትን ለሁለት ጊዜ በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ፣ በልዩ ልዩ ኃላፊነት ለሀገራቸው ረዥም ዘመን የሠሩ፤ በዕውቀታቸውና በሙያቸው ለሕዝባቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰጡ፣ የታታሪነት፣ የቅንነትና፣ የሕዝባዊ አገልግሎት ሰጭነት ተምሳሌት ነበሩ» በማለት ገልፀዋቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2011
ተገኝ ብሩ