አትሌት ሻምበል በላይነህ ዲንሳሞ ሰኔ 21/1957 ዓ.ም በደቡብ ክልል፣ ሲዳማ ዞን የተወለደ ሲሆን፤ በአትሌቲክስ ታሪኩ የማራቶን ሯጭ ነው፡፡ በላይነህ በ1980 ዓ.ም በሮተርዳም ማራቶን በ2፡06፡50 የሰበረው የማራቶን የዓለም ክብረወሰን ለአስር ዓመታት በማንም ሳይደፈርና ሳይሰበር የቆየ ውጤት ባለቤት ነው፡፡ በማራቶን ታሪክ ሦስተኛውና ረጅም ጊዜ ሳይሰበር የቆየ ሆኖ የተመዘገበለት ሲሆን፤ በግልና በአገር ውክልናው ውጤት ተወዳድሮ ካጠናቀቃቸው ስምንት የማራቶን ውድድሮች ሰባቱን በአሸናፊነት ሲያጠናቅቅ አንዱን በሁለተኝነት ማጠናቀቅ የቻለ የማራቶን ጀግና አትሌት ነው፡፡
ክብረወሰን በሰበረባት የኔዘርላንዷ ሮተርዳም ከተማ አራት ጊዜ ከማሸነፉም በላይ ሦስቱ ድሎቹ ተከታታይነት የነበራቸውና ሦስቴ በውድድሩ በተከታታይ በማሸነፍ ብቸኛው አትሌት ነው፡፡ በላይነህ ባለፉት ከሃያ ዓመታት በላይ በየትኛውም መገናኛ ብዙኃን ታይቶ አያውቅም። በሩጫ ዘመኑ አዝናኝና አሳዛኝ ክስተቶችን በማስተናገድ የስፖርት ቤተሰቡ አሁንም ድረስ ያስታውሰዋል።
ከሃያ ዓመታት የአሜሪካን አገር ቆይታው በኋላ ወደ አገሩ ተመልሶ አዲስ አበባ ይገኛል። አዲስ ዘመን ጋዜጣም ለአንድ ሰዓት ያህል ከበላይነህ ጋር የነበረው ቆይታ የሚከተለውን ይመስላል።
አዲስ ዘመን፡-በላይነህ ዲንሳሞ ለረጅም ዓመታት ምናልባትም ከሃያ ዓመታት በላይ ከመገናኛ ብዙኃን ርቀሃል፣ ምክንያቱ ምንድነው?
አትሌት በላይነህ፡፡- ቀደም ሲል ውድድር ላይ በነበርኩበት ወቅት አሜሪካን አገር ገብቼ ለመኖርና ልጆቼን ለማሳደግ ፍቃድ ጠይቄ ነበር፣ ማን እንደሆንኩኝ ካወቁ በኋላ ፍቃድ ሰጡኝ፣ በዚህም እኤአ ከ2003 በኋላ ልጆቼንና ቤተሰቦቼን ይዤ በአሜሪካን አገር ቦስተን ከተማ ኑሮዬን አደረኩኝ፡፡ አልፎ አልፎ ግን ወደእዚህም እመጣለሁ፡፡ አሁን የመጣሁት ለግል ጉዳይ ነው፣ በእርግጥ ያለፈው አዲስ ዓመት ሲከበር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በውጭ ለምንኖር ኢትዮጵያውያን በዓሉን አብረን እንድናከብር ባደረጉት ጥሪ መሰረት ተገኝቼ ነበር፣ ሚሊኒየም አዳራሽ በነበረው ሥነ ሥርዓት ላይ ነበርኩኝ፣ ግን የመገናኛ ብዙኃን ያወቁኝ አልመሰለኝም፡፡
በወቅቱ ብዙም ስላልቆየሁኝ ያገኘኝም አልነበረም፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በመጎብኘቴ በማህበራዊ ሚዲያው አማካኝነት በተሰራጩ ዜናዎች ሰዎችን እያገኘሁ ነው፡፡ በሚዲያ ደረጃ እናንተን ሳገኝ ከሃያ ዓመት በኋላ ይሄ የመጀመሪያ ነው፡፡ የተለያዩ ታሪኮቼን ግን የሚሠሩ ሚዲያዎች እንዳሉ አስተውያለሁ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያ ስመጣም በጊዜው በነበረው ሁኔታና የአስተዳደር ጉዳይ ደስተኛ ስላልነበርኩኝ ቃለመጠይቅ ለመስጠት ፍቃደኛ አልነበርኩም፡፡ አሁን ይህን ቃለመጠይቅ ስሰጥ ግን በተፈጠረው ለውጥ ደስተኛ በመሆኔና ሁሉም ወደሚፈልገው መስመር እየመጣ በመሆኑ ደስ ብሎኝ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አትሌቲክስ ካቆምክ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ፣ አሁንስ በምን አይነት ሕይወት ውስጥ ትገኛለህ?
አትሌት በላይነህ፡- እኤአ 1996 ከአትላንታ ኦሊምፒክ በኋላ ነው ያቆምኩት፣ ካቆምኩ በኋላ ግን ዝም ብዬ አልተቀመጥኩም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የማራቶን ረዳት አሠልጣኝ ሆኜ ለሦስት ዓመታት እየሠራሁ ባለሁበት ወቅት ነው ወደ አሜሪካን ያቀናሁት፣ ወደ አሜሪካ የሄድኩት በዋናነት ልጆቼን ለማስተማር ነው፣ ፈጣሪ ይመስገን ልጆቼ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፤ ሁለቱ ተመርቀዋል አንዷም በኮምፒዩተር ሳይንስ በሚቀጥለው ሰኔ ትመረቃለች፣ ልጆቼን ከማስተማር ጎን ለጎን እዚያው አገር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የመምና የሜዳ ተግባራት(ትራክ ኤንድ ፊልድ) አሠለጥናለሁ፤ እንደማንኛውም ሰውም ሌሎች ሥራዎች እሠራለሁ፡፡ በቅርቡ ግን ወደ አገሬ ቤተሰቦቼን ይዤ በመመለስ በሙያዬ ይሁን በሌሎች ነገሮች ለመሥራት ፍላጎት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደቀደመው የአትሌቲክስ ሕይወትህ ስንመለስ በአንድ ወቅት እቤትህ ላይ ቦምብ ተወርውሮ ነበር፣ የተለያየ የማስፈራሪያ ደብዳቤም ገንዘብ ካላመጣህ በሚል ይደርስህ ነበር ይባላል፣ እስቲ ስለዚህ ነገር አጫውተኝ፡፡
አትሌት በላይነህ፡- በሕይወቴ በመጥፎ ትውስታ ከማልረሳቸው ሁለት ነገሮች አንዱ በህፃንነቴ የገጠመኝ የእናቴ ሞት ሲሆን፣ ሌላኛው ይሄ ጉዳይ ነው፣ እኔ የኢትዮጵያ ባለውለታና አገሬን ለማስጠራት የምሮጥ ሰላማዊ ሰው ነኝ፣ አገራችንን ካስጠሩት ከነ አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴና ምሩፅ ይፍጠር ቀጥሎ የመጣሁ አትሌት ነኝ፡፡
እኔ የአገሬ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የማድረግ እንጂ ፖለቲከኛ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም፣ እኔ የኢትዮጵያ ልጅ ነኝ የተፈጠረው ነገር ግን በጣም አሳዛኝ ነው፣ ሃምሳ ሺ ብር እንዲሁም አንድ ሺ የአሜሪካን ዶላር ካላመጣህ በቅድሚያ ቤትህን ከዚያም ቤተሰብህንና አንተን እናጠፋሃለን የሚል ዛቻ አዘል ደብዳቤ ደረሰኝ፣ ስልኮችም ተደወሉልኝ፣ በፌዴሬሽን በኩል የሚያውቁኝ ዘመድ ሆነው በመቅረብ ለጥበቃዎች የዛቻ ደብዳቤ ያስቀምጡ ነበር፣ ወቅቱ የባርሴሎና ኦሊምፒክ የቀረበበት ነበር፣ እኔም ጉዳዩን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል አሳወኩኝ፣ የማራቶን ክብረወሰን በሰበርኩበት ወቅት ኢትዮጵያ የኮሚኒስት አገር በመሆኗ ብቃቴ ጥግ የደረሰበት ጊዜ ቢሆንም መሳተፍ አልቻልኩም፣ የባርሴሎና ኦሊምፒክም እንዳያመልጠኝ ሰግቻለሁ፣ የሚጠይቁኝ ያህል ገንዘብ እንደሌለኝ በመግለፅ ከሽልማት ያገኘሁትን ገንዘብ ሰብስቤ ቤት እንደገዛሁ ለመናገር ሞከርኩኝ፣ እውነቱን ለመናገር በወቅቱ የኪራይም ይሁን ሌላ ቤትና ቦታ አልተሰጠኝም፣ በአንድ በኩል ይሄን ሳስብ የተረሳሁ ይመስለኛል፣ ያም ሆኖ ያገኘሁትን ገንዘብ አውጥቼ ቦሌ አካባቢ ቤት ገዝቻለሁ፣ እለቱ መስከረም 6/1984 ዓ.ም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ እኔ ዜና እያየሁ ባለቤቴ ደግሞ ሁለተኛ ልጄን ነፍሰጡር ሆና ሌላ ክፍል ውስጥ ስልክ እያናገረች ነበር፣ ትንሿ ልጄ ስሟ ክብረወሰን ይባላል(ሮተርዳም ማራቶን ክብረወሰን ከመስበሬ ከሳምንት በፊት ነው የተወለደችው ለዛም ነው ስሟ ክብረወሰን የተባለው) ከጥበቃችን ጋር ግቢ ውስጥ ትጫወት ነበረ፣ ይሄን ጊዜ ነው ግቢዬ ውስጥ ቦንብ የተወረወረው፡፡
የፈጣሪ ፍቃድ ሆኖ የተጎዳ አልነበረም፣ ቦምቡ ሲወረወር ግቢ ውስጥ የነበረው መናፈሻ ዛፍ ላይ መጀመሪያ በማረፉ እቤቱን የጎዳውና ያፈራረሰው ፍንጥርጣሪው ነው:: መኪኖችም ተጎድተዋል፣ ቤቱን እንደገና ሳድስ ማንም ያገዘኝ አልነበረም፣ ፖሊስ የለም መጥቶ ያነጋገረኝ ሚዲያም የለም፣ የዛን ጊዜ ከባለቤቴ ጋር ያለቀስንበትና እጅግ ያዘንበት ነበር (እንባ እየተናነቀው)፣ ከዚያ በኋላ ቤት ውስጥ በነበረው ካሜራ የተቀረፀውን ብዙ ሰው አይቶታል፣ አይዞ ያለን ባይኖርም ፈጣሪ ይመስገን ተርፈን ይሄው ዛሬ እዚህ አለን፡፡ ከዚያ ወዲያ ረጅም ጊዜ ልምምድ ባለመሥራቴ በባርሴሎና ኦሊምፒክ እንዳልሳተፍ ያደረገኝ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ሞራሌ እንደወደቀ ቤተሰቦቼም በፍርሃት ተዘፍቀው እየተሰቃዩ እኔ ለውድድር ብሰለፍ ክብሬን ማስደፈርና ተሳታፊ ከመባል በዘለለ የማተርፈው እንደሌለ አውቄ በራሴ ፍቃድ ወደ ባርሴሎና ላለመሄድ ወሰንኩ፡፡ በጣም የማዝነው አገሬንና ወገኔን እንዳላኮራሁ አይዞህ ባይ ማጣቴና ከኦሊምፒክ ውድድር በመውጣቴ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አሳዛኝ ስሜት እንውጣና በቶኪዮና ፎኮካ ማራቶን የማይረሱ ገጠመኞች ነበሩህ፣ እነሱን አጫውተኝ፡፡
አትሌት በላይነህ፡- በ1978 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ውድድር ጃፓን ቶኪዮ ላይ ስሳተፍ የገጠመኝ ነገር በአስቂኝነቱ የማስታውሰው ነው፡፡ ወደ ውድድሩ ስንሄድ አሠልጣኝ ንጉሴ ሮባ በአገልግል ዶሮ ወጥ አሰርቶ ይዞ ነበር፣ ጃፓን እንደገባን አገልግሉን ይዤ ወደ ፎቅ ለመውጣት ሊፍት (አሳንስር) ላይ ወጣን፤ የሊፍቱን አይነት በአገራችን አላየሁትም ከህንጻው ውጪ ነው፣ እዚያ ላይ ሆኜ የከተማውን ውበት መብራቱን፣ፎቁን ስመለከት አዞረኝ፣ ያለሁበት አላውቀውም ሳላስበው ወገቤ ከድቶኝ ልወድቅ ስል ጋሽ ንጉሴና ሌሎች ጃፓናውያን ተረባርበው አተረፉኝ፡፡
በውድድሩ ሁለተኛ ሆኜ አጠናቀቅኩ፣ ያን ጊዜ ብራዚላዊው ካርሎስ ሎፔዝ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ነበር፣ ተወዳዳሪው ሁሉ ይፈራዋል እኔ ግን አልፈራሁትም፣ ውድድሩ ላይ በተወሰነ ኪሎ ሜትር የቆርቆሮ ጁስ ነበር፣ አንስቼ ልጠጣ ስል ይከለክሉኛል፣ ለካስ ሁሉም አትሌት የራሱ ስም ያለበትን ነበር እያነሳ የሚጠጣው ፣ እኔም ሰላሳ ኪሎ ሜትር አካባቢ የራሴን አግኝቼ አነሳሁ፣ አጠጣጡን እንደ ውሃ መስሎኝ ስሞክር ለካስ የሚጨመቅ ነበር፣ ከዚህ ጋር ስታገል ጁሱ ከነጭራሹ ከእጄ ወድቆ እሱን ለማንሳት ጥረት ሳደርግ ሌሎች ከኋላ መጥተው ቀድመውኝ ሄዱ፣ መጠጡን ትቼ የቀደሙኝን እንደ ምንም ከአራተኛ ተነስቼ ሁለተኛ ሆኜ ጨረስኩኝ፡፡ የታንዛኒያው ኢካንጋ በአስራ ዘጠኝ ሰከንድ ቀድሞኝ ነው አንደኛ የሆነው። ያኔ ውድድሩን የጨረስኩበት ሰዓት 2፡08፡29 የኢትዮጵያ ክብረወሰን ነበር።
ሌላው በጣም ያዘንኩበት ማራቶን በዚሁ በጃፓን ፎኮካ ማራቶን ነው፤ በውድድሩ ከፊት ስመራ ቆይቼ ከፊት ለፊቴ መንገዱን ሲመራኝ የነበረው ሞተረኛ ወደ ማቆሚያ ሲሄድ ተከትዬው ሄድኩኝ፤ መሳሳቴን ያወኩት በስፍራው የነበሩ ሰዎች በጩኸትና በምልክት ሲያሳዩኝ ነው፤ እንደገና ትክክለኛውን መንገድ ይዤ ስሮጥ ጃፓናዊው ሺቡታኒ ቀድሞኝ ገባ፤ በጣም አዘንኩኝ ሁለተኛ በመሆኔ ዋንጫ አበረከቱልኝ እኔ ግን የልባችሁን አድርሳችሁ ብዬ አልቀበልም አልኩኝ፤ ከዚያ ግን ዋንጫው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተላከልኝ መቼስ ምን አደርጋለሁ ተቀበልኩኝ።
አዲስ ዘመን፡- አትላንታ ኦሊምፒክስ ምን ተፈጠረ?
አትሌት በላይነህ፡- አትላንታ ኦሊምፒክ ተሳትፌያለሁ፣ በወቅቱ ወደእዚያ የሄድነው ቀደም ብለን ነው፣ ያመሆን አልነበረበትም ፣ ከውድድሩ ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ ወደ ስፍራው ሄድን፣ ሙቀቱ እጅግ ከፍተኛ ስለነበረ መሄድ የነበረብን ሁለትና ሦስት ቀን ብቻ ቀደም ብለን ነበር፣ በዛ ሙቀት ውስጥ አቋማችን ወረደ፣ ከግማሽ በላይ ውድድሩን ስመራ ነበር ከዚያ ግን መቀጠል አልቻልኩም አቋርጬ ወጣሁ፣ ከአትላንታ ስመለስ ቀደም ብሎ ክፍለ አገር እያለሁ እግር ኳስ ስጫወት ወድቄ እግሬ ላይ የሚያመኝ የነበረ ጉዳት አገረሸብኝ ፣ የገጠር ልጅ ስለነበርኩኝ በወጌሻ ነበር ታክሜ የዳንኩት፣ ከጊዜ በኋላ ግን ህመሙ ተነሳብኝ ለዚያም ነው በገዛ ፍቃዴ ሩጫ ለማቆም የወሰንኩት፣ ከዚያም በአሠልጣኝነት ለማገልገል ወሰንኩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከአትላንታ በኋላ በተለይም በሲድኒና አቴንስ ኦሊምፒኮች እነ ኃይሌና ቀነኒሳ አስደናቂ ታሪክ ሲያስመዘግቡ ተመልክተሃል፣ ምን ተሰማህ?
አትሌት በላይነህ፡- አትላንታ ላይ ከኃይሌ ጋር አብረን ነበርን፣ ሲድኒ ላይ ያንን ድንቅ ታሪክ ሲሠሩ ግን እጅግ በጣም ነው የተደሰትኩት፣ እኔ የኦሜድላ ክለብ ዳይሬክተርም የአትሌቶች ተወካይም ነበርኩኝ፣ ኃይሌን ወደ ሩጫው ዓለም በመግባት እቀድመዋለሁ፣ እኔ ማራቶን ስሮጥ ኃይሌ ተማሪ ነበር፣ አሰላ ለልምምድ ስሄድ አውቀዋለሁ፣ በዚያን ወቅትም ከእኔ ጋር አልፎ አልፎ ልምምድ ይሠራ ነበር፣ በጣም እንቀራረባለን ወደ አዲስ አበባ ሲመጣም ኦሜድላ ነበር የገባው፣ እኔ ውጪም ስለነበርኩኝ እንደበፊቱ ባይሆንም አሁንም እንገናኛለን፣ አሜሪካ ሲመጣ እኔም እዚህ ስመጣ እንገናኛለን፡፡
አዲስ ዘመን፡-አትሌቶች የፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች እየሆኑ ነው፣ ከኃይሌ ቀጥሎ አሁን ደራርቱ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሆናለች ፣ ይሄን እንዴት አየኸው?
አትሌት በላይነህ፡- በጣም ደስ የሚል ነው፣ በጽንሰ ሃሳብ ብቻም ሳይሆን በተግባር የተፈተኑ አገራችንን ያስጠሩ ጀግና አትሌቶች ፌዴሬሽኑን በሚመሩበት ጊዜ እያንዳንዱን የአትሌቶች ችግር ያውቃሉ፣ ሳይናገሩ ገና ችግራቸው ምን እንደሆነ ያውቃሉ፣ ምክንያቱም በውስጡ አልፈዋል፡፡
አሁን ጥሩ ነገር አለ ፤ ወጣት አትሌቶችም ተነሳሽነታቸው ይጨምራል፣ አሁን የአትሌቶችን መብት ለማስከበር ይሠራሉ ብዬ አስባለሁ፣ በኛ ጊዜ ማስታወቂያ መሥራት አንችልም፣ ልብስ መልበስ አንችልም፣ አሸንፈን ያገኘነውን ገንዘብ እንኳን ሰላሳ በመቶ ተቆርጦ ለማግኘት ቀላል ፈተና አልነበረም፡፡ ሰው ፍጹም አይደለምና አሁንም ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ ፣ በኛ ጊዜ የነበሩ ችግሮች ግን አሁን አይታዩም፣ አሁን የሚስተካከሉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ እነሱን በመወያየት መፍታት ይቻላል፣ ፌዴሬሽኑ አዲስ ቢሮ ቀይሯል።
ይሄንን ለመጀመሪያ ጊዜም አሁን ጎበኘሁት፣ በጣም የተደራጀ የተማሩ ሰዎች ያሉበት፣ በፋይናንስም በሌሎችም ነገሮች ጥሩ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፣ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ግን ፌዴሬሽኑ፣ አትሌቱና አሠልጣኙ የበለጠ መሥራት አለበት፡፡ ለምሳሌ የማራቶን ክብረወሰን በኛ እጅ አይገኝም፣ እኔ ለአስር ዓመት ይሄን ክብረወሰን ይዤ ቆይቻለሁ፣ አበበ ቢቂላ ይህን ክብረወሰን ከሰበረ ከሃያ ሦስት ዓመት በኋላ ነው እኔ የያዝኩት፣ ኃይሌም ከእኔ በኋላ ክብረወሰኑን ወደኛ መልሷል፣ አሁንም ይህን ክብረወሰን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ የሚሆኑ አትሌቶች አሉን ዋናው ነገር አሠልጣኞች፣ አትሌቶችና ፌዴሬሽን በተጠና መንገድ በየትኛው ውድድር ይህን ማድረግ ይቻላል ብለው መዘጋጀት ነው፡፡ በሴቶች በኩልም የሚመዘገቡ ውጤቶች ጥሩ ናቸው፤ ኬንያውያን በምን በልጠውን ነው በእኛ እጅ የነበረውን ክብረወሰኑን የያዙት?፤ ይህን ክብረወሰን ለማስመለስ ሁላችንም ተመካክረን መዘጋጀት አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ጭምር ማራቶንን ከ2፡00 ሰዓት በታች ለማጠናቀቅ ጥረት ሲደረግ ይታያል፤ አንተ ይሄን ትደግፋለህ? ማራቶንን በተፈጥሯዊ መንገድ ልክ እናንተ እንደምትሮጡበት ዘመን ሮጦ ከ2፡00ሰዓት በታች መግባት ይቻላል ብለህ ታምናለህ?
አትሌት በላይነህ፡- አዎን ይቻላል፤ ምክንያቱም አሁን የእኛ አትሌቶችም ይህን ሰዓት እየተጠጉ ነው፤ በደንብ ተዘጋጅቶ ዝም ብሎ መሮጥ ሳይሆን በየትኛው ውድድር መሮጥ አለብኝ ተብሎ ከታሰበ ይቻላል። የአሠልጣኝ፤ የአትሌቱና የፌዴሬሽኑ ቅንጅት ያስፈልጋል፤ ለየትኛው ማራቶን ነው ለክብረወሰን መዘጋጀት ያለብን? በምን ወቅት? የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል።
በዚህ መንገድ ከተቀናጀ ማራቶንን ከ2፡00 ሰዓት በታች ማጠናቀቅ የማይቻልበት ምክንያት የለም። አሁን እንደዛ አይደለም አትሌቱ ብዙ ቦታ ጉልበቱን ጨርሶ ክብረወሰን በሚሰበርበት ውድድር ይደክማል፤ ለምሳሌ ብዙ ክብረወሰን የሚሰበርበት በርሊን ለጥ ያለ ሜዳ ነው፤ እኔ እንኳን ክብረወሰን ስሰብር ሮተርዳም ላይ ሁለት ዳገታማ ድልድዮችን አቋርጬ ጭምር ነው፤ ይህን ክብረወሰን ማን ሊያስመዘግብ ይችላል የሚለውን ለይቶ ውድድር እንዲቀንስ በማድረግ በርሊን ላይ መሞከር ይቻላል።
የስነ ልቦና ዝግጁነት ማድረግም ወሳኝ ነገር ነው። ይሄ በወንዶች ብቻ አይደለም፤ ሴቶች እዚህ ክብረወሰን ውስጥ አልገቡም ሊታሰብበት ይገባል፤ አቅሙና ብቃቱ ያላቸው ተለይተው በቂ ዝግጅትና ሥልጠና በመስጠት ማሳካት ይቻላል። ባህላችን የሆነውን የማራቶን ክብረወሰን ለመመለስ መንፈሳዊ ቅናት ሊኖረን ይገባል።
እኔ አሠልጣኜ ንጉሴ ሮባን እኛ እንደዚህ እየሮጥን ለምን ክብረወሰን መስበር አቃተን ብዬ እጠይቀው ነበር፤ እሱም እኔ እንጃ እንለፋለን ግን አይሳካልንም ይለኝ ነበር፤ ያኔ እኔ ክብረወሰን ለመስበር በውስጤ ዝግጅት ጀምሬያለሁ፤ በብሔራዊ ቡድን ዝግጅት እናደርጋለን፤ በግሌ ደግሞ አሠልጣኜ ሳያውቅ በቀን ሦስት ጊዜ ዝግጅት እያደረኩኝ ነበር፤ እኔና አትሌት አበበ መኮንን የተለያዩ ውድድሮች በማሸነፋችን የመኮንንነት ማዕረግ ተሰጠን፤ ይህን ሹመት በማስመልከት አስኮ በሚገኘው የመኮንኖች ክበብ ሚኒስትሮች፤ ጄነራሎች ፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች የክብር እንግዶች ባሉበት ትልቅ ዝግጅት ተደረገ፤ እንደ ልጆቻቸው አድርገው ያሳደጉን የፖሊስ አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጄነራል ወርቁ ዘውዴ አብረውን ነበሩ፤ ንግግር እንድናደርግ ወደ መድረክ ተጋበዝን፤ አበበ የራሱን ተናግሮ ጨረሰና እኔ ተከተልኩኝ፤ የተሰጠኝ ማዕረግ ትልቅ ውለታ ስለሆነ ደስ ብሎኛልም ከብዶኛልም አልኩኝ፤ ይህን ውለታ እንዴት እመልሳለሁ ብዬ በማሰብ ከስቻለሁ ብዬ ስናገር አዳራሹ በሳቅ ተናጋ፤ እኔ አሁን እንደ በፊቱ ለማሸነፍ ብቻም ሳይሆን የምዘጋጀው ክብረወሰን ለማስመዝገብ ነው ብዬ አልኩኝ፤ ከአበበ ቢቂላ የተወሰደው የማራቶን ክብረወሰን እመልሳለሁ ስል ተናገርኩ፤ አዛዤ መጥቶ አቀፈኝ አዳራሹ በሙሉ በደስታ ተዋጠ፤ ንግግር አድርጌ ስመለስ ግን ጓደኛዬ አበበ መኮንን አስደነገጠኝ፤ ምን ነካህ አብደሃል እንዴ በላይነህ አለኝ፤ በምን ብትተማመን ነው በጀነራሎች፤ በሚኒስትሮችና ጋዜጠኞች ፊት ክብረወሰን እሰብራለሁ ብለህ አፍህን ሞልተህ የምትናገረው አለኝ፤ እኔም ደነገጥኩኝ ነገር ግን ለዚህ ያበቃኝ ፈጣሪ ያውቃል እንዴት እንዳደኩኝ አውቃለሁ ከዚህ በኋላ መመለስ አልችልም እሠራለሁ አልኩኝ ለራሴ።
ከፕሮግራሙ በኋላ ወደ ቤት ስመለስ ባለቤቴ የመጀመሪያ ልጃችን ክብረወሰንን ነፍሰጡር ነበረች፤ ውሎዬን ሳወጋት ስሜታዊ ሆኜ ክብረወሰን እሰብራለሁ በማለቴ መደንገጤን ነገርኳት፤ ያለውን የማይፈፅም ወታደር፣ ወታደር አይደለም፤ ባለቤቴ አይዞህ ፈጣሪ ያውቃል አለችኝ፤ በዚያን ወቅት ነፍሰጡር ሆና ሌሊት ስለሚያማት እሷን ለመንከባከብ በቂ እንቅልፍ አልነበረኝም፤ እሷ ግን በራሴ ወጪም ቢሆን ሆቴል ገብቼ ተጨማሪ ልምምድ እንድሠራ መከረችኝ፤ ለዚህም እናቷ እኔን ተክተው እንዲንከባከቧት ለማምጣት ተወያየን፤ በዚህም ወክማ ገብቼ በራሴ ገንዘብ ለአንድ ወር ያህል ጠዋትና ማታ እንዲሁም የብሔራዊ ቡድን ሥልጠና ሲኖር በቀን ሦስት ጊዜ ልምምድ እየሠራሁ፤ ጊዜውም ደርሶ ሆላንድ ሮተርዳም ማራቶን 1980 ዓ.ም ክብረወሰኑን መስበር ቻልኩኝ።
በወቅቱ ጅቡቲያዊው አሜን ሳላ የሚባል አትሌት በውድድሩ ክብረወሰን አስመዘግባለሁ ብሎ የሃምሳ ሺ ዶላር ውል ተዋውሎ ነበር፤ እኔ አገሬን ለማስጠራት እንጂ ስለ ገንዘቡ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም፤ በዚህ የተነሳ ለእኔ ብዙ ትኩረት አልተሰጠኝም ነበር፤ እሱም በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ክብረወሰን እንደሚሰብር ፎከረ፤ እኔም ጅቡቲያዊው አትሌት ክብረወሰን ከሰበረ እኔ የማልሰብርበት ምክንያት የለም ብዬ መለስኩኝ፤ ዝግጅቴን እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው አቋሜና ብቃቴ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አሠልጣኜ ንጉሴ ራሱ በትክክል አያውቅም፤ ኢትዮጵያውያን በተግባር እንጂ በወሬ አያምኑም ብዬም ጋዜጠኞች ሌላ ጥያቄ እንዳያነሱ አደረኳቸው። እስከ ሰላሳ አምስት ኪሎ ሜትር ድረስ ከሌሎች አትሌቶች ጋር ተፎካከርን ሰላሳ ስምንተኛው ኪሎ ሜትር ላይ ግን የጅቡቲውን አትሌት ትቼው አፈተለኩኝ፤ እሱም ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የቀድሞ ክብረወሰኑን አሻሻለ። እኔም ለመንግሥትና ለህዝብ የገባሁትን ቃል ፈፀምኩኝ። ስመለስም በፖሊስ ኦኬስትራ ታጅቤ የጀግና አቀባበል ተደረገልኝ። አዛዤም ያለውን የሚፈፅም ልጅ አገኘሁ ብለው በደስታ አቅፈው ተቀበሉኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ወጣት አትሌቶች በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች ልምድ ሳይኖራቸው ወደ ማራቶን እየገቡ ትንሽ ተስፋ አሳይተው በዛው ሲጠፉ እንመለከታለን፤ እነዚህን አትሌቶች ምን ትመክራቸዋለህ?
አትሌት በላይነህ፡- እኔ እንደ አትሌትም እንደ አሠልጣኝም የምመክራቸው ነገር አለኝ፤ ሁሉም አትሌት ተመሳሳይ ተሰጥኦ የለውም፤ አንዳንዱ በአጭር ሌላው ደግሞ በረጅምና በማራቶን የተፈጥሮ ክህሎት ይኖረዋል፤ ስለዚህ ውጤታማ ሆኖ ለመዝለቅ መጀመሪያ ተሰጧችንን መለየት ነው፤ ገና ሳይበስሉ አጥንታቸው ሳይጠነክር ወደ ማራቶን መምጣት እጅግ የሚጎዳ ነው፤ አምስትና አስር ሺ እያሉ ትንፋሻቸውን አዳብረው አጥንታቸውም ጠንክሮ ወደ ማራቶን ቢመጡ ትክክለኛው አካሄድ ነው፤ ማራቶን አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ነው ይህን ሮጦ ለማጠናቀቅ ቢያንስ ከ2 ሰዓት ተኩል በላይ ይፈልጋል፤ ይህን ሁሉ ሰዓት ሮጦ ለመጨረስ በቀን ብዙ ሰዓት ልምምድ መሥራት ያስፈልጋል፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ አቅሙም ጉልበቱም እድሜውም ወሳኝ ነው፤ አሁን ሩጫ ሳይንሳዊ ነው፤ አንዱ ለጊዜው ስለተሳካለት ሌላው ዘሎ መግባት የለበትም፤ እንዲህ ካልሆነ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ ውጤት ማምጣት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- ሻምበል አትሌት በላይነህ ዲንሳሞ ለሰጠኸን ጊዜ ከልብ አመሰግናለሁ።
አትሌት በላይነህ፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ። ከሚዲያው ብርቅም አገሬና ህዝቤን አሁንም አልረሳሁም፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም በክፉና በደግ ጊዜ አብረውኝ ለነበሩ ምስጋናዬን አቅርብልኝ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2011
ቦጋለ አበበ