
‹‹የትምህርት አሠጣጡ በተሻለ ሁኔታ እየሄደ ነው››
–የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ
‹‹በትምህርት ቤቱ ላይ እርምጃ መውሰድ የአገራቱን ግንኙነትሊያሻክር ይችላል››
– ትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፡– ‹‹የግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት ዜጎች በአገራቸው መማርም ሆነ መሥራት እንዳይችሉ በሚያደርግ የትምህርት አሰጣጥና በግብረሰዶም ተግባር ላይ ተሰማርቶ ትውልድ እያመከነ ነው ›› በሚል ቅሬታ አቅራቢዎች ጠቁመዋል። ትምህርት ቤቱ በበኩሉ ድርጊቱን ቢያስተባልም፤ ትምህርት ሚኒስቴር ግን ጥቆማው ትክክለኛ እንደሆነ ተናግሯል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚያመጣቸው ተማሪ ወላጆች ለልጆቻቸው የውጭ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) እንደሚሰጣቸውና ዕድሉም ሁሉንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ቃል ቢገባም ተማሪዎቹ ያገኙት ዕድል ስለሚሰረዝባቸው በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግሪክ መንግስት ይደረግ የነበረው ድጋፍ መቆሙ የልጆቹን ተስፋ አጨልሟል።
ተማሪዎቹ አዳሪ ትምህርት ቤት በሆነው በግሪክ ክፍሉ በሚኖራቸው ቆይታ የሚማሩት በግሪክ ቋንቋ ብቻ በመሆኑ የውጭ የትምህርት ዕድሉን ካላገኙ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት መማርም ሆነ ተወዳድረው መሥራት የማይችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ተማሪዎቹ የወደፊት ተስፋቸው በመጨለሙም በትምህርት ቤቱ በተለያዩ የጉልበት ሥራዎች፣ ምግብ አብሳይነትና ለግሪካውያኑ የቤት ሠራተኛ በመሆን ሕይወታቸውን እንዲገፉ እንዳስገደዳቸው ተናግረው፤ብዙዎቹ በሚደርስባቸው የወሲብ ትንኮሳና ከፍ ብሎም የተመሳሳይ ፆታ የወሲብ ጥቃትን በመሸሽ ለሴተኛ አዳሪነትና ለጎዳና ሕይወት መጋለጣቸውን ጠቁመዋል።
ትምህርት ቤቱ አራት የተለያዩ ሥሞችን እንደሚጠቀምና የግሪክ ኮሙዩኒቲ ቢሆንም በግሪክ ክፍሉ የሚያስተምራቸው ግን ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ጉዳዩ በተደጋጋሚ ለትምህርት ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነትና ስኮላርሺፕ ቢሮ በቅሬታ ቢቀርብም ምላሽ ስላልተሰጠ ችግሩ እንዲቀጥል አድርጎት ቆይቷል። መንግስት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥም ጠይቀዋል።
የትምህርት ቤቱ የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ አቶ ወሰን ውበት በበኩላቸው፤ በትምህርት ቤቱ ችግር ቢኖርም በተባለው ልክ ግን አይደለም ብለዋል። የትምህርት አሰጣጡም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀው፤ የውጭ ትምህርት ዕድል የቆመውም ግሪክ ከደረሰባት ቀውስ ጋር ተያይዞ ቢሆንም የተማሪዎቹን ሕይወት ለማስተካከል ትምህርት ቤቱ ካለው ቁርጠኝነትና ፍላጎት የተነሳ በግሪክ ክፍሉ ያሉ ብዛት ያላቸው ተማሪዎች በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ መስፈርት መሠረት ትምህርት በሚሰጠው እንግሊዝ ክፍሉ እንዲገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል። አያይዘውም ወሲባዊ ጥቃት ግን በትምህርት ቤቱ እንደሌለና የሥም ማጥፋት ነው በማለት አስተባብለዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ አስፋው መኮንን ‹‹ግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት የተቋቋመው በኢትዮጵያ የሚኖሩ የግሪክ ማሕበረሰብን አገልግሎት ለመስጠት ነው። ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቱ በግሪክ ክፍሉ የሚያስተምራቸው ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ቅሬታዎች ሲቀርቡም የባለሙያዎች ቡድን ቦታው ድረስ ተገኝቶ ጉዳዩን አጣርቷል።
በዚህም ቅሬታው ትክክል እንደሆነ ታምኗል። ከወሲብ ጥቃት ጋር ተያይዞ በተነሳው ቅሬታም በእንግሊዝ ክፍሉም ችግር እንዳለና ከዚህ በተጨማሪም የአደገኛ ዕፅ ዝውውር እንዳለ ወላጆች ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ሆኖም ግን ይህን መሠል ችግሮች ተጠቂዎች ራሳቸው ካላጋለጡና ጥቆማ ካልተደረገ ሚኒስቴሩ ብቻውን የሚያከናውነው አይደለም።
በተቋሙ ላይ እርምጃ መውሰድ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ሊያሻክር ይችላልና ከፍተኛ ውሳኔን የሚጠይቅ ነው። በቀጣይም ቅንጅታዊ ሥራን የሚጠይቅ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል›› በማለት ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011
ፍዮሪ ተወልደ