የጨቅላ ሕፃን ቢጫ መሆን የሚታየው በሕፃኑ ሰውነትና ዓይን ላይ ነው፡፡ የጨቅላ ሕፃን ቢጫ መሆን የሚከሰተው የሕፃኑ ከመጠን ያለፈና ቢጫ መልክ ያለው ቢሊሩቢን የሚባለው ኬሚካል በሕፃኑ ደም ውስጥ መኖር ነው፡፡
የጨቅላ ሕፃናት ቢጫ መሆን በብዛት የሚታይ/የሚከሰት ሲሆን በተለይ ከ38 ሳምንታት የእርግዝና ጊዜያቸው በፊት የሚወለዱ/ያለ ጊዜያቸው የሚወለዱና አንዳንድ ጡት የሚጠቡ ሕፃናት ላይ በብዛት ይታያል። የጨቅላ ሕፃናት ቢጫ መሆን የሚመጣው ሕፃናት ጉበታቸው በደንብ ያልጎ ለበተ ከመሆኑ የተነሳ ቢሊሩቢን የሚባለውን ኬሚካል ከደም ውስጥ እንዲወገድ ማድረግ ስለማይችል ነው። አንዳንዴ ደግሞ መሠረታዊ የጤና ችግሮችም ካሉ ሊከሰት ይችላል፡፡
ምልክቶች
ሕፃናት በተወለዱ ከ2 እስከ 4 ቀናት ውስጥ የቆዳና የዓይን ነጩ ክፍል ቢጫ መሆን ይጀምራል፡፡ የልጅዎ ቆዳ መልክ ወደ ቢጫነት መቀየሩን ለማወቅ የልጅዎን የግንባር/ አፍንጫ ቆዳ ጫን ጫን በማድረግ በተጫኑበት ቦታ የቆዳው ቀለም ወደ ቢጫነት መቀየር መኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡
የሕክምና ባለሙያዎን ማማከር የሚገባዎ መቼ ነው
ልጅዎ ከተወለደ ከ3 እስከ 7 ቀናት ውስጥ የቢሊሩቢን መጠኑ በደም ውስጥ ከፍ የሚልበት ወቅት ስለሆነ በሕክምና ባለሙያዎች መታየት አለበት። የሚከተሉት የሕመም ምልክቶች በብሊሩቢኑ በጣም መጨመር ምክንያት የተከሰተ ሊሆን ስለሚችል የሕክምና ባለሙያዎን ማማከር ይገባል፡፡
• የልጅዎ ቆዳ በጣም ቢጫ መሆን ካለው
• በልጅዎ የእግር፣እጅና ሆድ አካባቢ ባለው ቆዳ ላይ ቢጫ መሆኑ ካለ
• የልጅዎ የዓይኑ ነጩ ክፍል ቢጫ ከሆነ
• ልጅዎ ከታመመ/ንቁ ካልሆነ
• ልጅዎ አመጋገቡ ከቀነሰ አሊያም ክብደት እየጨመረ ካልሆነ
• ልጅዎ ሲያለቅስ ድምፁ በጣም ከቀጠነ/ከሰለለ (ከተለወጠ) –high-pitched cries
• ቢጫ መሆኑ ከ3 ሳምንታት በላይ ከቆየ የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ነገሮች
• ያለጊዜያቸው የሚወለዱ ሕፃናት፡ – ያለጊዜያቸው/ከ38 ሳምንታት የእርግዝና ጊዜ በታች የሚወለዱ ሕፃናት የመውለጃ ጊዜያቸው ደርሶ ከሚወለዱት ሕፃናት አንፃር ሲታዩ ቢሊሩቢንን የማስወገድ አቅማቸው የቀነሰ ነው።
• ሕፃኑ በሚወለድበት ሰዓት ከወሊድ ጋር በተገናኘ የቆዳ ስር ደም መድባት/ bruising ከነበረው፡– በወሊድ ወቅት ሕፃኑ የመጋጋጥ/የቆዳ ስር መጥቆር አጋጥሞት ከነበረ ብዙ ቀይ የደም ሴሎች ስለሚሞቱና የቢሊሩቢን ኬሚካል መጠን ስለሚጨምር ለቢጫነት ያጋልጣል፡፡
• የደም ዓይነት፡– የእናትና የሕፃኑ የደም ዓይነት የተለያየ ከሆነ
• የጡት ወተት፡– የእናት ጡት የመጥባት ችግር ያለባቸው ወይም ከእናት ጡት ወተት በቂ ንጥረ ምግብ ማግኘት የሚያዳግታቸው ሕፃናት ይበልጥ ይጋለጣሉ፡፡ በቂ ወተት ሳያገኙ ቀርተው የፈሳሽ እጥረት የገጠማቸው ወይም የካሎሪ አወሳሰዳቸው አነስተኛ ከሆነ ለቢጫነቱ መከሰት ምክንያት ይሆናል። ነገር ግን ብዙዎቹ ኤክስፐርቶች የእናት ጡት ካለው ከፍተኛ ጥቅም የተነሳ የእናት ጡት ማጥባት መቀጠሉን ይመክራሉ። ሕፃናት በበቂ ሁኔታ መመገብና/ጡት ወተት ማግኘት አለባቸው፡፡
የቤት ውስጥ ሕክምና
የልጅዎ ቢጫ መሆን ብዙም የማያሳስብ ከሆነ የሕክምና ባለሙያዎ ቢሊሩቢኑን መጠን ሊቀንስ የሚችል የአመጋገብ ልማድ ሊመክርዎ ይችላል። የሚከተሉትን ምክሮች ቢተገብሩ ሊረዳዎ ይችላል፡፡
• ልጅዎን በበቂ መጠን መመገብ፡ – በተደጋጋሚና በበቂ መጠን መመገብ ልጅዎ በቂ ወተት እንዲያገኝ ስለሚረዳ ካካ/ሰገራ በተደጋጋሚ እንዲወጣና ከሰውነታቸው ቢሊሩብንን ለማስወገድ ይረዳል፡፡ ጡት የሚጠቡ ሕፃናት በቀን ውስጥ ከ8 እስከ 12 ጊዜ መመገብ አለባቸው። የቆርቆሮ ወተት የሚመገቡ ከሆነ ዕድሜያቸው ላይ ደግሞ በየ2 እና 3ት ሰዓታት ከ30 እስከ 60 ሚሊ ሊትር ወተት በመጀመሪያ ሳምንት ማግኘት አለባቸው፡፡
• ተጨማሪ ምግብ፡– ልጅዎ ጡት የመጥባት ችግር ከገጠመው አሊያም ክብደት እየቀነሰና ፈሳሽ እያጠረው ከመጣ የሕክምና ባለ ሙያዎ ከጡት ወተቱ በተጨማሪ የቆርቆሮ ወተት ሊያዝለት ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ የሕክምና ባለሙያዎ ጡት ለተወሰነ ቀናት እንዲያቋርጥና የቆርቆሮ ወተት እንድቀጥል ሊደረግ ይችላል፡፡
መከላከል
ሕፃናትን በበቂ መጠን መመገብ የጨቅላ ሕፃናትን ቢጫነት ለመከላከል ያገለግላል። ስለሆነም ከላይ እንደተጠቀሰው ጡት የሚጠቡ ሕፃናት በቀን ውስጥ ከ8 እስከ 12 ጊዜ መመገብ ያለባቸው ሲሆን የቆርቆሮ ወተት የሚመገቡ ከሆነ ደግሞ በመጀመሪያው ሳምንት ዕድሜያቸው ላይ በየ2 እና 3ት ሰዓታት ከ30 እስከ 60 ሚሊ ሊትር ወተት ማግኘት አለባቸው፡፡
ምንጭ፡– ቴሌ ሜድ ሜዲካል ሰርቪስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2011