ጦርነቱን እንዳያባብሰው የተሰጋው የዩክሬን አጋሮች ውሳኔ

የዩክሬን አጋሮች ለሀገሪቱ በሚሰጧቸው የጦር መሣሪያዎች ላይ ጥለዋቸው የነበሩትን ገደቦች ማንሳታቸው ተገልጿል:: የጀርመን መራሄ መንግሥት ፍሬድሪኽ ሜትስ ምዕራባውያን የዩክሬን አጋሮች ለሀገሪቱ በሚሰጧቸው መሣሪያዎች ዓይነትና የአጠቃቀም ገደብ ላይ ጥለዋቸው የቆዩትን ገደቦች እያነሱ እንደሆነ ተናግረዋል:: ገደቦቹን ካነሱት ሀገራት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካና ጀርመን እንደሚገኙበት ሜትስ ገልፀዋል::

ሜትስ በርሊን ውስጥ በተከናወነ ኹነት ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ዩክሬን በሩሲያ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎችን መምታት አትችልም ነበር:: ከዚህ በኋላ ግን ሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ይዞታዎችን በመምታት ራሷን መከላከል ትችላለች›› ብለዋል:: የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪም ወደ ጀርመን ተጉዘው ከሜትስ ጋር ተወያይተዋል::

ከአሜሪካ በመቀጠል ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ በማቅረብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ጀርመን፣ ‹‹ታውረስ›› (Taurus) የተሰኙትን ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኢሎችን ለዩክሬን ሳትሰጥ ቆይታለች:: የአሁኑ መራሄ መንግሥት ሜትስ በጀርመን ምክር ቤት ተቃዋሚ በነበሩበት ጊዜ ጀርመን በጦርነቱ በቀጥታ መሳተፍ እንደሌለባት የሚያምኑትን የቀድሞውን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ዩክሬን ሚሳኢሎቹን እንድታገኝ ፈቃድ እንዲሰጡ ሲወተውቱ ነበር::

ሚሳኢሎቹ እስከ 500 ኪሎ ሜትር ድረስ መምዘግዘግ የሚችሉ ሲሆኑ ጥብቅ ኢላማዎችን ለመምታት ያስችላሉ:: ሚሳኢሎቹ በሚጓዙት ርቀት፣ በሚሸከሙት ፈንጂ እና ዒላማ በመለየት ብቃታቸው ዩክሬን አሁን ካሰማራቻቸው የአሜሪካና የዩናይትድ ኪንግደም ሚሳኢሎች የተሻሉ ናቸው:: ጀርመን ሚሳኢሎቹን ለዩክሬን የምትሰጥ ከሆነ ዩክሬን እስካሁን ጥቅም ላይ ካዋለቻቸው የምዕራባውያን ሚሳኢሎች መካከል ጠንካራዎቹ ሚሳኢሎች ለውጊያ ታሰማራለች ማለት ነው::

ይሁን እንጂ ሜትስ በንግግራቸው ሀገራቸው እነዚህን ሚሳኢሎች ለዩክሬን እንደምታስታጥቅ ስለመግለፃቸው በትክክል የታወቀ ነገር የለም:: በርሊን ላይ ከቮሎድሚር ዘለንስኪ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ስለሚሳኢሎቹ ያነሱት ነገር የለም:: ዩክሬን ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኢሎችን በራሷ አቅም እንድታመርት ጀርመን ድጋፍ እንደምታደርግላት ለዘለንስኪ ቃል ገብተውላቸዋል::

አሜሪካ ባለፈው ኅዳር ወር ዩክሬን እስከ 300 ኪሎ ሜትር መምዘግዘግ የሚችለውን ‹አርሚ ታክቲካል ሚሳኤል ሲስተም› (Army Tactical Mis­sile System – ATACMS) የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤልን እንድትጠቀምና በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቃቶችን እንድትፈፅም ፈቅዳ ነበር:: ሩሲያም በወቅቱ በብሪያንስክ ግዛቷ ውስጥ በዚሁ ሚሳኤል በዩክሬን ጥቃት እንደተፈፀመባት ገልፃ ነበር:: ከዚህ በተጨማሪም ዩክሬን በዚያው ሰሞን የዩናይትድ ኪንግደም ስሪት በሆነውና እስከ 250 ኪሎ ሜትር መምዘግዘግ በሚችለውን ‹ስቶርም ሻዶው ሚሳኤል› (Storm Shadow Missiles) በሩሲያ ላይ ጥቃት እንደፈጸመች የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር::

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የምዕራብ አጋሮቻቸው እንደ ‹አርሚ ታክቲካል ሚሳኤል ሲስተም› (ATACMS) ባሉ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች አጠቃቀም ላይ የጣሏቸውን ገደቦች እንዲያነሱላቸው ደጋግመው ሲማፀኑ ቆይተዋል:: የገደቦቹ መነሳት ኪዬቭ ሩሲያ ግዛት ውስጥ የሚገኙ የሎጂስቲክስ ማከማቻዎችን፣ የእዝ ማዕከላትንና የጦር ካምፖችን ለመምታት እንደሚያስችላት ፕሬዚዳንቱ በፅኑ ያምናሉ:: ይሁን እንጂ ምዕራባውያን የዩክሬን አጋሮች በሩሲያ ግዛት ውስጥ የሚፈፀሙ የዩክሬን ጥቃቶች ጦርነቱን የበለጠ ሊያባብሱትና ሊያሰፉት ይችላሉ የሚል ስጋታቸውን ሲያንፀባርቁ ቆይተዋል::

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪይ ፔስኮቭ የዩክሬን አጋሮች ውሳኔ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት የሚደረገውን ጥረት ፍጹም የሚፃረር ተግባር መሆኑን በአፅንኦት ተናግረዋል:: ‹‹ውሳኔው የሚተገበር ከሆነ፣ ለጦርነቱ መፍትሄ ለመፈለግ የሚደረገውን ጥረት ፈፅሞ የሚያበላሽ ነው›› ብለዋል:: ለጦርነቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ ላይ ለመድረስ የሚደረገውን ተስፋ የሚያጨልም እንደሆነም ቃል አቀባዩ አስጠንቀቀዋል::

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው መስከረም በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ምዕራባውያን የዩክሬን አጋሮች ዩክሬንን ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኢሎችን አስታጥቀው በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቃት እንድትፈፅም ካደረጉ፣ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ከሩሲያ ጋር ጦርነት መግጠሙን ይወቀው›› በማለት አስጠንቅቀው ነበር:: ይህ ደግሞ የጦርነቱን መልክ እንደሚቀይረው ፑቲን ተናግረዋል::

የሩሲያ የፀጥታና ደህንነት ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ዲሚትሪይ ሜድቬዴቭ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰሞኑን የሩሲያውን አቻቸውን ቭላድሚር ፑቲንን ለወረፉበት ንግግራቸው በሰጡት ምላሽ፣ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እንዳይነሳ አስጠንቅቀዋል:: ቀደም ሲል ሩሲያን በፕሬዚዳንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት እና ከፑቲን የቅርብ ሰዎች መካከል አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሜድቬዴቭ፣ ምዕራባውያን በጦርነቱ ውስጥ ያላቸውን ጣልቃ ገብነት የማያቆሙ ከሆነ ሩሲያ የኑክሌር መሣሪያዎቿን ልትጠቀም እንደምትችል ደጋግመው አስጠንቅቀዋል::

በ ‹ቻተም ሃውስ› (Chatham House) የሩሲያና ኢውሬዥያ ክፍል ባልደረባ ቲሞቲ አሽ፣ የመራሄ መንግሥት ሜትስ ንግግር ሩሲያ የተኩስ አቁም ስምምነትን እንድትቀበል ለቀረበላት ጥሪ ላሳየችው ዳተኝነት የተሰጠ ምላሽ እንደሆነ ያምናሉ:: ‹‹አውሮፓውያኑ ይህ ዓይነቱ ርምጃ ሩሲያ ለድርድር ትኩረት እንድትሰጥ ጫና ያሳድርባታል ብለው ተስፋ አድርገዋል:: የሜትስ ንግግር ትርጉም ያለው የአካሄድ ለውጥ እንዳለ አመላካች ነው:: ሜትስ በሩሲያ ላይ ከሾልዝ የበለጠ ከረር ያለ አቋም አላቸው:: የሰላም ጉዳይን በተመለከተ ግን የሁለቱም ወገኖች አቋም የተራራቀ ነው›› ብለዋል::

መራሄ መንግሥት ፍሬድሪኽ ሜትስ የሚመሩት ጥምር መንግሥት አካል የሆነውና የቀድሞው መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ፓርቲ ‹ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ› ጀርመን በጦርነቱ በቀጥታ መሳተፍ እንደሌለባት ስለሚያምን ሚሳኢሎቹን ለዩክሬን የመስጠትን ሃሳብ በጽኑ ይቃወማል:: የፓርቲው ሊቀ መንበርና የሀገሪቱ ምክትል መራሄ መንግሥት ላርስ ክሊንግቤይል በታውረስ ሚሳኢሎች ጉዳይ ጀርመን ምንም የተቀየረ አቋም እንደሌላት ተናግረዋል:: የሜትስ ‹ክርስቲያን ዴሞክራሲያዊ ኅብረት› (CDU) ፓርቲ አባላት ጭምር የመራሄ መንግሥቱን ንግግር ተችተዋል::

የመራሄ መንግሥት ሜትስ ንግግር የተሰማው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከባድ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ክፉኛ መበሳጨታቸውን በገለፁበትና በኃይለ ቃልም እየወረፏቸው ባሉበት ወቅት ነው:: ሩሲያ ሰሞኑን በዩክሬን ላይ ከባድ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን እንደተበሳጩ መናገራቸው የሚታወስ ነው::

ትራምፕ ከሩሲያ ጥቃት በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሩሲያ ድርጊት ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልጸው፣ ጠንከር ባለ እና ባልተለመደ ተግሳጽ ፑቲንን ‹‹ምን ነካው? ብዙ ሰዎችን እየገደለ ነው›› ብለዋል። ኃይለ ቃላትን ተጠቅመውም ወርፈዋቸዋል:: ‹‹ፑቲንን ለረጅም ጊዜ አውቀዋለሁ፤ እንግባባለን፤ጥሩ ግንኙነት አለን:: በአሁኑ ወቅት ግን ሮኬቶችን ወደ ከተሞች እያስወነጨፈ ሰዎችን እየገደለ ነው። በጭራሽ የምወደው ነገር አይደለም›› ብለው ነበር። አሜሪካ በሩሲያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ለማክበድ እያሰቡ እንደሆነ ተጠይቀው የነበሩት ትራምፕ ‹‹በርግጠኝነት!›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከቀናት በኋላ ደግሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬንን ጦርነትን እንዲያስቆሙ የሁለት ሳምንታት ቀነ ገደብ እንደሰጡ ተናግረዋል። ፑቲን ጦርነቱን ማቆም ይፈልጋሉ ወይ ተብለው የተጠየቁት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ‹‹እሱን ልነግራችሁ አልችልም። ነገር ግን በሁለት ሳምንት ውስጥ ታውቁታላችሁ›› ብለዋል። ‹‹በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ፑቲን ከእኛ ጋር ነው ወይስ አይደለም የሚለውን እናውቃለን›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የሀገራቸው ቀጣይ ርምጃ በሩሲያ ምላሽና ድርጊት ላይ እንደሚወሰን ገልፀዋል::

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You