ኢትዮጵያ በ10 ወራት ከ354ሺህ ቶን በላይ ቡና ለዓለም ገበያ አቀረበች

ጀርመን፣አሜሪካናሳዑዲዐረቢያከፍተኛየቡናምርትየተላከባቸውሀገራት ናቸው

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት 10 ወራት ለውጭ ገበያ ከአቀረበችው 354 ሺህ 302 ቶን ቡና አንድ ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ። ይህም በኤክስፖርት ታሪክ የመጀመሪያው ከፍተኛ ገቢ መሆኑን ጠቅሷል።

የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳህለማርያም ገብረመድህን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ውስጥ 240ሺህ 753 ቶን ቡና በመላክ አንድ ነጥብ 315 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 354ሺህ 302 ቶን ለውጭ ገበያ በማቅረብ አንድ ነጥብ 868 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል።ይህም ከዕቅድ በላይ የተመዘገበ አፈጻጸም መሆኑን ገልጸዋል።

አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ869 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ጭማሪ እንዳሳየ ጠቅሰው፤ በሀገሪቱ የአንድ ዓመት ኤክስፖርት ታሪክ ውስጥ ተገኝቶ የማያውቅ እና የመጀመሪያ የሆነ ከፍተኛ የቡና ኤክስፖርት አፈጻጸም እንደሆነ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ከተላከው ቡና 61 ሺህ ቶን በላይ ወደ ጀርመን በመላክ 295 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ፣ 60 ሺህ ቶን በላይ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ በመላክ  290 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ እንዲሁም 28 ሺህ ቶን በላይ ወደ አሜሪካ በመላክ 192 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት ተችሏል ብለዋል። እነዚህ ሀገራት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን የያዙ መዳረሻዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። እንዲሁም ቤልጅዬም፣ ቻይና ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ዩናይትድ ዐረብ ኤሜሬትስ፣ ጃፓን፣ ጣልያን እና ጆርዳን ተጠቃሽ የኢትዮጵያ የቡና ገበያ መዳረሻ ሀገራት እንደሆኑ ጠቅሰው፤ አጠቃላይ በገቢ ረገድ እነዚህ ሀገራት 78 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ይሸፍናሉ ሲሉ ገልጸዋል።

ከተላኩት የቡና ዓይነቶች መካከል፤ ነቀምቴ በመጠን 110 ሺህ ቶን በላይ ድርሻ እንደሚሸፍን ጠቅሰው፤ 464 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ፤ ሲዳማ በመጠን 65 ሺህ ቶን በላይ በመላክ 404 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ፣ ጅማ በመጠን 61 ሺህ ቶን በላይ 255 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የገቢ አፈጻጸም በማስመዝገብ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ድረስ የገቢ ደረጃን ይዘዋል ሲሉ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የ6ቱ ዋና ዋና የቡና ዓይነቶች በአጠቃላይ በመጠን 88 በመቶ ለውጭ ገበያ መላካቸውን እና 87 በመቶ የገቢ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ የስድስቱ የቡና ዓይነቶች አፈጻጸም ከ2016 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር በገቢ ሲወዳደር ሁሉም የቡና ዓይነቶች ጭማሪ ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You