
አዲስ አበባ፡- ‹‹ምሁራን ራሳቸውን ሊጠይቁና ለሀገራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርጉባቸው ከሚገቡ ታሪካዊ አጋጣሚዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር መድረክ አንዱና ዋነኛው ነው›› ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ሂሩት ገብረሥላሴ አስታወቁ።
‹‹ለኢትትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት የምሁራን ሚና›› በሚል መሪ ሃሳብ በትናንትናው እለት በሃይሌ ግራንድ የምሁራን ውይይት ተካሂዷል። በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ሂሩት ገብረሥላሴ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ምሁራን በብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ራሳቸውን ሲያገሉ ወይም ሁኔታውን በዝምታ ሲመለከቱ ማየት የተለመደ ነው። በሀገራዊ ምክክር ሂደትም ተመሳሳይ ሁኔታዎች ይታያሉ።
መድረኩን ማዘጋጀት ያስፈለገው፤ ምሁራን በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑና የመፍትሄ ሃሳቦችን በማመንጨት በቀጣይ ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በማስፈለጉ እንደሆነ ተናግረው፤ ምሁራን ለሀገራቸው አስተዋጽኦ ሊያደርጉባቸው ከሚገቡ ታሪካዊ አጋጣሚዎች መካከል ሀገራዊ የምክክር መድረክ ዋነኛው ነው ሲሉ ወይዘሮ ሂሩት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ እጅግ መሠረታዊ እና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሰፊ አለመግባባቶች እና የሃሳብ ልዩነቶች ከሚታዩባቸው ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ነች ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ እነዚህን ሁሉ አለመግባባቶች በኃይል አማራጭ ለመፍታት ጥረት እየተደረገባት ያለች ሀገር መሆኗም ሌላው እውነታ ነው ብለዋል። በዚህም እንደሀገር ብዙ ዋጋ መከፈሉን እና እየተከፈለ መሆኑን አስረድተዋል። ሀገሪቱ ከቀውሶች መውጣት አለመቻሏ ከተዘፈቀችበት የድህነት አረንቋ ለመላቀቅ የምታደርገውን ጉዞ እጅግ በጣም አድካሚ እንዳደረገውና እንደሀገር የመቀጠሏን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እያስገባው እንደሄደም ገልጸዋል።
ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ መንስኤዎችን በመለየት ዘላቂ መግባባት ላይ በመድረስ ሀገርን ከጥፋት ማዳን እንደሚስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህንን ችግር ከግምት በማስገባት ሕጋዊ የምክክር መድረክ ያስፈልጋል የሚሉ ጥያቄዎች ለተደጋጋሚ ጊዜ ሲቀርቡ እንደነበር አውስተው፤ ከብዙ ድካም በኋላ ጥያቄው ይሁንታ አግኝቶ የኢትዮጵያ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
በሌሎች ሀገራት የተከናወኑ ሀገራዊ ምክክሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ካደረጓቸው ጉዳዮች መካከል የምሁራን አስተዋጽኦ ከፍ ያለ እንደነበር እና ሀገራዊ ምክክር አካሂደው ያልተሳካላቸው ሀገራትም ምሁራዊ ሚናቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸው ለውድቀት እንደዳረጋቸው ከተሞክሯቸው መገንዘብ ተችሏል ሲሉ አስረድተዋል። በሂደት ላይ ያለው ሀገራዊ ምክክርም ውጤታማ እንዲሆን የምሁራን አበርክቶ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በጽኑ ይታመንበታል ብለዋል።
መሠረታዊና ማህበራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አለመግባቶች ጎልተው ከሚታዩባቸው ወገኖች መካከል ምሁራን ተጠቃሽ ናቸው ያሉት ወይዘሮ ሂሩት፤ ምሁራን ሀገርን በሃሳብ የሚመሩ፣ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደመሆናቸው መጠን በመካከላቸው የሃሳብ ልዩነቶች መፈጠራቸው የሚገርም እንደማይሆን ገልጸዋል።
አብዛኛዎቻችን የኢትዮጵያ ምሁራን ማህበረሰቡ ከእኛ ይቀድማሉ፤ ሀገር ያሻግራሉ ብሎ ከሌለው ቆርሶ ያስተማረን ነን ያሉት ወይዘሮ ሂሩት ፤ የችግሮች ገፈት ቀማሽ ሆኖ እየደገፈ የምሁርነት ደረጃ ላይ ያደረሰንን ማህበረሰብና የተከፈለልንን ዋጋ መልሰን እየከፈልን ነው ወይ የሚለው መጤን ያለበት ጉዳይ እንደሆነ አስምረውበታል።
ሀገራዊ የምክክር መድረኩ በንግግር ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሃሳብ የሚዋጣበት፤ ሃሳብ የሚቋጭበት፤ ሃሳብ ብቻ አሸናፊ የሚሆንበት መድረክ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በዚህም ሃሳብ አፍላቂና አመንጪ የሆኑ ምሁራን ሚና ከፍተኛ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ምሁራን በውይይት እንዲሳተፉ እና እንዲካተቱ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ምሁራን ምክክር ሊደረግባቸው ይገባሉ ያሏቸውን አጀንዳዎች ስለመስጠጣቸውም ተናግረዋል። እስከ አሁን በነበረው ሂደትም ለኮሚሽኑ እገዛቸውን እያደረጉ ያሉ ምሁራን ስለመኖራቸው ጠቅሰው፤ ይህም ኮሚሽኑ ወደ ምሁራኑ ቀርቦ ባደረገው ጥረት የተገኙ ውጤቶች ናቸው ብለዋል።
በአጠቃላይ ምልከታ ሲታይ ግን ምሁራን በውይይት ሂደቱ ሊኖራቸው ከሚገባው እና ሊያደርጉት ከሚችሉት አስተዋጽኦ አኳያ ተሳትፏቸው አነስተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ምሁራን የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን መደገፍ ብቻ ሳይሆን ከመስመር የወጡ ጉዳዮች ሲኖሩ በምክንያት የተደገፉ ምሁራዊ ትችትን መሰንዘር እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል። በመደገፍም ይሁን በመቃወም የምሁራን ድምጽ መሰማት የሚገባው ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ሳለ፤ ዝምታ መንገሡ ጠቃሚ አይሆንም ብለዋል።
እንደሀገር ካጋጠመን ችግር መውጣት የሚቻለው ሁላችንም በትብብር እና በአንድነት ሠርተን ውጤት ማምጣት ስንችል ብቻ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በችግሩ ልክ ጥረት ማድረግ ይገባዋል ሲሉ ወይዘሮ ሂሩት አሳስበዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም