
ለተከታታይ ስድስት ቀናት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲከናወን የቆየው 54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ትናንት ተጠናቋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የቻምፒዮናው አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል።
የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ በሴቶች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፣ በወንዶች ደግሞ መቻል ነው። የሁለቱም ፆታ በ279 ነጥብ በነጥብ አጠቃላይ አሸናፊ ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆን ችሏል። መቻል 242 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ሸገር ሲቲ 143 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል ።
ከመም (ትራክ) ችግር ጋር በተያያዘ ቻምፒዮናው ደረጃውን የጠበቀ አይደለም ተብሎ ሲወቀስ የቆየ ቢሆንም በተለያዩ ውድድሮች አጓጊ ፉክክሮችን የታዩበት ነበር። በቻምፒዮናው ፍፃሜ እለት በተለያዩ ርቀቶች ውድድሮች ተከናውነዋል።
ጠንካራ ፉክክር የታየባቸውና በሁለቱም ፆታ የተካሄዱት የ5ሺህ ሜትር ውድድሮች የተመልካቹን ቀልብ መግዛት የቻሉ ናቸው። ብርቱ ፉክክር በታየበት የሴቶች 5ሺህ ሜትር ፍፃሜ አትሌት የኔዋ ንብረት በ16፡06.87 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀዳሚ በመሆን አጠናቃለች። አትሌት ገመኔ ማሚቴ በ16፡07.38 ከኦሮሚያ ፖሊስ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ፣ የኢትዮ ኤሌክትሪኳ አትሌት ዘይን አለልኝ በ16፡08.33 ሦስተኛ ሆናለች። በ5ሺህ ሜትር ወንዶች አብዲሳ ፈይሳ በ14፡12.51 ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ባለ ድል መሆን ችሏል።
በሁለቱም ፆታ በ1500 ሜትር ፣ 5000 ሜትር ፣ 4×100 እና 4×400 እንዲሁም በሴቶች የከፍታ ዝላይ የፍፃሜ ውድድሮችም ተከናውነዋል። በ1500 ሜትር በሴቶች ፅጌ ተሾመ ከሰላሌ ዩኒቨርሲቲ አሸናፊ ስትሆን ፤ በወንዶች ደግሞ ሞሲሳ ስዩም ከሸገር ከተማ አሸናፊ ሆኗል።
በ4×100 ርቀት በሴቶች ሲዳማ ቡና ፤ በወንዶች ሸገር ከተማ ውድድራቸውን በአሸናፊነት አጠናቀዋል። በ4×400 ውድድር በወንዶች የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌቶች አሸንፈዋል። በተመሳሳይ በሴቶችም የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌቶች የበላይነቱን ወስደዋል።
በውድድሩ ሁለት ወርቅ ያገኙ አምስት ፤ ሦስት ወርቅ ያመጡ ሁለት አትሌቶች እንዲሁም ክብረ ወሰን ያሻሻሉ አትሌቶች ልዩ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። በዘንድሮ ውድድር ከሌላው ጊዜ በተለየ ለ160 አሸናፊ አትሌቶች ትጥቅ ተበርክቶላቸዋል።
በ54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከክልሎች ፣ ከተማ አስተዳደሮች ፣ ክለቦች እና ተቋማት የተውጣጡ 1,379 አትሌቶች ተሳትፈዋል።
በቻምፒዮናው ላይ የባህልና ስፖርት ሚንስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባየ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ጌቱ ገረመው፣ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መሠረት ደፋር፣ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣አንጋፋ አሠልጣኞች፣ አትሌቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም