በመዲናዋ በቀን ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን እንቁላል እየተመረተ ነው

አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ በቀን ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን እንቁላል እየተመረተ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ገለጸ:: የእንቁላል ዋጋን ለማረጋጋት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነም ተጠቁሟል::

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር እና የአርሶ አደር ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሎኮ ዳለቻ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በክፍለ ከተሞች እና በወረዳዎች ደረጃ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በመቅረጽ በተሠሩ ሥራዎች፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሶስት ሚሊዮን በላይ ዶሮ ለማሰራጨት ተችሏል::

አዲስ አበባ ከሸማችነት ወደ አምራችነት መሻገር አለባት በሚል መርህ የከተማ ግብርና ወደ ሥራ መግባቱን አውስተው፤ በአሁኑ ጊዜ እንደ ከተማ አስተዳደር በቀን ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን እንቁላል እየተመረተ ይገኛል:: ይህም አምራች ከመሆን አንጻር ማሳያ የሚሆን ነው ሲሉ ገልጸዋል::

በእንቁላል ዋጋ ላይ ተጽዕኖ ከሚያደርሱ ነገሮች አንዱ መኖ መሆኑን ያነሱት ምክትል ዋና ኃላፊዋ፤ ከዚህ በፊት መኖ ከቀረጥ ነጻ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ቀረጥ መጣሉ የእንቁላል ዋጋ እንዲወደድ አድርጓል ብለዋል::

ችግሩን ከመፍታት አንጻር እንደ ከተማ አስተዳደር ቦታ በማዘጋጀት፤ የመኖ አምራቾችን በማደራጀት ከሸማቾች ጋር የማገናኘት ሥራ መሠራቱን አመልክተው፤ አሁን ላይ ሥራው በየክፍለ ከተማው የተጀመረ ሲሆን፤ የመኖ ዋጋ ገበያ ላይ ካለው ዋጋ አንጻር ከስምንት መቶ እስከ አንድ ሺህ ብር ቅናሽ ተደርጎበታል ሲሉ ተናግረዋል::

በሌላ በኩል መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች መኖ ማምረት እንዲችሉ የማበረታታት ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸው፤ እንደ አጠቃላይ ባለፈው ወር መኖ ላይ ትኩረት ተደርጎ ስለተሠራ በቀጣይ የእንቁላል ዋጋ ላይ መሻሻል ይኖራል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል::

ለማሳያ ያህል በአዋሬ አካባቢ ወይም በሴቶች አደባባይ እንቁላል በ10 ብር እየተሸጠ ይገኛል ሲሉ የጠቆሙት ወይዘሮ ሎኮ፤ በቀጣይ ዋጋው የበለጠ እንዲቀንስ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል::

ምክትል ዋና ምክትል ኮሚሽነሯ እንደተናገሩት፤ ቢሮው ከሥራና ክህሎት ቢሮ ጋር በመተባበር በከተማው የሚገኙ በርካታ ወጣቶችን በማደራጀት፤ ቦታ በማመቻቸት እና የቴክኒክ ድጋፎችን በመስጠት በከብት ማደለብ፤ በዶሮ ርባታ እና በሌሎች የግብርና ሥራዎች እንዲሠማሩ ተደርጓል:: በዚህም በከተማ ግብርና ከ296 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል::

በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ሴቶች፤ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመሆን፤ አረጋውያን የሀገር ባለውለታ እንደመሆናቸው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሠራ ሲሆን፤ በሚሠማሩባቸው የግብርና ዘርፎች የቴክኒክ ድጋፎች እንደሚያደርጉ ገልጸዋል::

የዋጋ ንረት የሚረጋጋው ስለ ኑሮ ውድነት በማውራት ሳይሆን በመሥራት ነው የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ ሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪ በእቃም ሆነ ባለው ውስን ቦታ የከተማ ግብርናን እንዲተገብር መልዕክት አስተላልፈዋል::
ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You