የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከተቋቋ መባቸው አላማዎች መካከል የከተማዋን ብሎም የአገሪቷን የአትሌቲክስ ስፖርት ማሳደግ፤ በአዋቂና ወጣት ስፖርተኞች በሁለቱም ጾታ በሚካሄዱ ከተማ አቀፍና ሀገራዊ ውድድሮች እንዲሁም ስልጠናዎች በመሳተፍ እንዲሁም ውጤት በማስመዝገብ የህብረተሰቡን ፍላጎት ማርካት ነው፡፡
የስፖርት አመራሩ አስተሳሰብ ከአጭር ጊዜ ጥቅም ይልቅ ቀጣይነት ወዳለው ውጤታማነትና ለስፖርቱ እድገት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ፤ የከተማውን መልካም ገጽታ ለመገንባት የራሱን ድርሻ የሚወጣ አካል ለማድረግ ከ2009ዓ.ም ጀምሮ ሁሉን አቀፍ የሆነ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ፌዴሬሽኑ የተቋቋመለትን አላማ ለማሳካት የአምስት ዓመት እቅድ መነሻ በማድረግ በየዓመቱ የጠቅላላ ጉባዔ ያካሂዳል፡፡ በዘንድሮውም ዓመት የጠቅላላ ጉባኤው የ2010 በጀት ዓመት የፌዴሬሽኑ የስራ ሪፖርት፣ የ2011 ዓ.ም እቅድና መሰል ጉዳዮችን ያካተተ ውይይት ሰሞኑን ከባለድርሻ አካላት ጋር በማካሄዱ የሪፖርቱ ዳሰሳ እንደሚከ ተለው ቀርቧል፡፡
የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጻነት ታከለ እንደሚናገሩት፤ በ2010 ዓ.ም የውድድር ዘመን 17 የውድድር ሰነድና በጀት የተዘጋጀ ሲሆን፤ በርካታ ወጣቶች በውድድሩ በማሳተፍ የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በአትሌቶች ምልመላና ስልጠና በታዳጊ ስልጠና እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ከዳኞችና አሰልጣኞች ማህበር ጋር ውይይቶች እንዲካሄዱ ተደርገዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም 2ሺ543 ወንዶች 1ሺ539 ሴቶች በድምሩ 4ሺ82 ስፖርተኞችን በማሳተፍ ፌዴሬሽኑ ያቀደውን ሙሉ በሙሉ ማሳካት ችሏል፡፡
ዓመታዊ ዕቅድ፣ ሪፖርትና ቃለ ጉባኤ ተዘጋጅቶ የጠቅላላ ጉባኤ መካሄድ፣ ውድድሮችን በአግባቡ ማከናወን፣ የቴክኒክ ኮሚቴ ስራዎች በአግባቡ መስራት፣ በአገር አቀፍ ውድድሮች የውጤት መሻሻሎች መታየቱ፣ የውድድር ሽልማቶች መሻሻላቸው ባለ ጉዳይ በማስተናገድና ተግባብቶ መስራት የተሻለ መሆኑ ፌዴሬሽኑ በ2010ዓ.ም ጥንካሬዬን አጉልተው አሳይተዋል ያላቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በእቅዱ መሠረት በፕሮግራም ስራዎችን አለመምራት፣ የውድድር መደራረብ ፣ የተሰጡ ስልጠናዎች አነስተኛ መሆናቸው፣ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ስልጠና ድጋፍና ክትትል አነስተኛ መሆን፣ የሙያ ማሻሻያና የዳኝነት ሥልጠና አለመሰራቱ፣ የውድድር እና ስልጠና ቁሳቁስ እጥረት መኖሩ፣ የአሰልጣኞችና የዳኞች ማህበርን እንዲሁም የአንጋፋ አትሌቶች ማህበርን ከመደገፍና ከማጠናከር አኳያ አለመሰራቱ፣ በተለያዩ ችግሮች የባለሙያ እጥረት በመከሰቱ አልፎ አልፎ የቢሮ መዘጋትና መሰል ተግባራት በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ሀገር አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ውጤታማነት ከማሳደግና ተተኪ ስፖርተኞች ከማፍራት አንፃር በሜጀር ጀነራል ሃየሎም አርአያና በሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያነት ውድድር ማካሄድ አለመቻሉንና በአገር አቀፍ የኢትዮጵያ ውድድር ላይ ውጤታማ ከመሆን አንፃር ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉበትም ተናግረዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ በጽሁፍ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ሊታይ በሚችል ቦታ በግልፅ በመለጠፍ ተገልጋዩን ክፍል አሰልጣኝ ፤ ዳኛ ፤ አትሌት በቅድሚያ መረጃ በመስጠት ቅሬታዎች እንዲፈቱ ተደርጓል፡፡ በተለይም ተገልጋዮችን ከማርካት አንጻር ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ክንውን መኖሩንም የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጻነት ጠቁመዋል፡፡
እንደ ፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ገለጻ፤ በ2010ዓ.ም በርካታ ውድድሮች ከሞሃ ለስላሳ መጠጦች አክሲዮን ማህበር እና ከወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ጋር በስኬት ማሄካድ የተቻለ ሲሆን፤ ተተኪ ስፖርተኞችን እና አትሌቶች እንዲሁም ክለቦች ያሉበትን ደረጃ እና አቋም በውድድር በማሳተፍ እንዲፈትሹበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በሌላ በኩል የማዘውተሪያ ስፍራ ችግር፤ የክለቦች አደረጃጀት አቅም ተመጣጣኝ ያለመሆን፤ ከክፍለ ከተማ ጋር ተቀናጅቶ አለመስራት በከተማዋ በአትሌቲክሱ እድገት በተፈለገው ደረጃ መሄድ አልተቻለም፡
አቶ ነጻነት እንደሚሉት፤ ፌዴሬሽኑ በተለያዩ የሙያ መስኮች ልምድና ችሎታ ያላቸው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ቴክኒክ ኮሚቴ አሉት፡፡ ክፍለ ከተሞች ለስራዎች ተባባሪ መሆናቸው እና በከተማ ደረጃ ለስፖርቱ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እና ፌዴሬሽኑ ለክለቦች፣ ለክፍለ ከተሞች እና ለልዩ ልዩ ኮሚቴዎች የሚያዘጋጃ ቸውን የተለያዩ ስልጠናዎች በፌደሬሽኑ በኩል ተፈፃሚ እንዲሆኑ ማድረግ በ2011ዓ.ም በእቅድ ከተካተቱት ተግባራት መካከል ናቸው፡፡
የባለሙያዎችን ቁጥርና የሙያ ብቃት በማሻሻል በኩል በተለያየ ደረጃ የዳኞች እና የአሰልጣኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና እንደሚሰጥ የገለጹት አቶ ነጻነት፤ ቀጣይነት ያለው ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ይቻል ዘንድ ክለቦችና ማሰልጠኛ ማዕከላት የታዳጊ ፕሮጀክት ጣቢያ እንዲያቋቁሙ በማበረ ታታት አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
‹‹የፌዴሬሽኑን የሀብት አሰባሰብ አቅምን ለማበዳበር የተለያዩ የሀብት ማሰባሰቢያ ፕሮፖ ዛሎችን በመቅረጽ ከባለሀብቶች፣ ከድርጅቶችና ከኩባንያዎች ጋር የስምምነት ሰነድ ይፈራረማል፡፡ በገንዘብና በዓይነት የተለያዩ ድጋፎችን በማግኘት የፌደሬሽኑን አቅም በማጎልበት በክፍለ ከተሞች፣ ክለቦችና ማዕከላት ለተከፈቱ የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና ፕሮግራም እና በፌደሬሽኑ ለሚወዳደሩ ደጋፊ ለሌላቸው ተወዳዳሪዎች የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ነው›› በማለት በቀጣይ በበጎ ፈቃድ ዙሪያም ጭምር ለመስራት መታቀዱን አቶ ነጻነት አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ነጻነት ማብራሪያ የክለብ ማቋቋሚያና መተዳደሪያ ሰነድ በማዘጋጀት ፍቃድ ያላወጡ የአትሌቲክስ ማዘውተሪያ ያላቸውን ተቋማት ፍቃድ እንዲያወጡ በማድረግ ከፌደሬሽኑ ጋር በቅርበት እንዲሰሩ ማስቻል ትኩረት የሚሰጥባቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ ለዚህም የሙያ ማህበራትን በማቋቋም የዳኞች ማህበር እንዲጠናከር ማድረግ፣ የተቋቋመው የአሰልጣኞች ማህበር ከፌደሬሽኑ ጋር የበለጠ በመተባበር ብቃት ያላቸውና በሀገር ሀቀፍ ደረጃ ምርጥ ተፎካካሪና ውጤታማ አትሌቶችን ለማፍራት የሚደረገውን ርብርብ በግንባር ቀደምነት እንዲመሩ ማስቻል፣ አስሩን ክፍለ ከተማ ጨምሮ አዲስ አበባ የሚገኙ ተቋማትን በማስተባበር አዳዲስ የአትሌቲክስ ክለቦች እንዲቋቋሙ ማድረግ፡፡
ክለብ ለመመስረት የመነሻ እቅድ በማስቀመጥ ተቋማትን ማነጋገር፣ ባለሀብቶች ወደ አትሌቲክስ እንዲሳቡ ብሎም ወደ ክለብ ምስረታ እንዲገቡ ማግባባት፣ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ ከንቲባ ቢሮ እና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበርና ስፖንሰር በማፈላለግ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ይሰራል፡፡ በዚህም ጃን ሜዳ፣ አበበ ቢቂላ ስታድየምና አቃቂ ቃሊቲ ስታዲየምን መጠቀም እንዲቻል ትኩረት እንደሚሰጥ አቶ ነጻነት አክለው ገልፀዋል፡፡
አቶ ነጻነት የተሳታፊ አትሌቶች ቁጥርን ከፍ በማድረግ ሠፊ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች በአካልና በአዕምሮ የዳበሩ ውጤታማና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማገዝ መከታተልና ማብቃት በየትምህርት ቤቶች ውድድር የተሻለ አቅም ያላቸው አትሌቶች ቀደም ብሎ በመመልመል ሠፊ ዝግጅት፣ ጠንካራ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ውጤታማ አትሌቶች ማፍራት፤ የታዳጊ ፕሮጀክት ጣቢያዎችን ድጋፍና ክትትል በማድረግ በዕድሜ ተገቢ የሆኑ አትሌቶች የተሻለ ስልጠና እዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ፤ የታዳጊ ፕሮጀክት የምዘና ውድድር በማዘጋጀት ኤሊት አትሌቶች መለየትና ከተቋማት ጋር ትስስር መመስረት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
አቶ ነጻነት አክለውም የህብረተሰቡን ተደራ ሽነትና የስፖርት ተሳትፎ በማሳደግ የልማት ባለቤትነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዙሪያ ለአመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ከውድድር ደንብ፣ ከስልጠና መርሃግብር፣ በአትሌቶች ምርጫ እና በመሳሰሉት ዙሪያ ከክለቦችና ከክፍለ ከተሞች ጋር ውይይት እንደሚካሄድ አብራርተዋል፡፡ በዚህ ረገድ በአትሌቶች ምልመላ እና ስልጠና፣ በታዳጊዎች ስልጠና ፕሮግራም፣ ፀረ-አበረታች መድሃኒት እና ዶፒንግ በመሳሰሉ ጉዳዮች፣ ክፍለ ከተሞችን ጨምሮ ከዳኞች ማህበር፣ ከአሰልጣኞች ማህበር፣ ከአንጋፋ አትሌቶች ማህበርና ከመሳሰሉት ባለድርሻ አካላት ጋር መድረክ በማዘጋጀት በውይይት ህብረተሰቡን የማሳተፍ ሥራ እንደሚኖርም አስገንዝበዋል፡፡
በህዝባዊ አደረጃጀቱ የሴቶችን ተሳትፎ ማጠናከር ሴቶችን በንዑሳን ኮሚቴ፣ በአሰል ጣኝነት፣ በዳኝነት እንዲሳተፉ ድጋፍ በማድረግ ተሳትፏቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ የገለጹት አቶ ነጻነት፤ በስፖርቱ የሴቶችና የወጣቶች ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አኳያ ሴቶችን ተሳታፊ የሚያደርጉ ተግባራት እንደሚኖሩና፤ ሴቶች በዳኝነት፣ በአሰልጣኝት፣ በስራ አስፈጻሚና በልዩ ልዩ ንኡሳን ኮሚቴዎች ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ እድል በመፍጠር እንዲሁም ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡ ሴቶች በክለብ እንዲሁም በአሰልጣኝነትና በዳኝነት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ፌዴሬሽኑ በ2011 ዓ.ም አሳካለሁ ብሎ ላሰባቸው ተግባራት የማዘውተሪያ ስፍራ (የውድድር ቦታ) እጥረት፤ የፕሮጀክት ማሠልጠኛ ጣቢያዎችን በታቀደው መሰረት በቂ ድጋፍና ክትትል አለማድረግ የግብዓት ችግሮችና የበጀት እጥረት ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶች ብሎ አስቀምጧል፡፡ ለዚህም ከሚመለከ ታቸው አካት ጋር ፕሮግራም ቀድሞ በማስያዝ በትብብር መስራት በዓመታዊ ዕቅድ መሰረት መመራት፣ በማካካሻ ፕሮግራም ድጋፍ ማድረግ፣ ሜዳዎችን በውሰት መጠቀምና የገቢ ምንጭ የሚያስገኙ ስራዎችን መስራት እንደ መፍትሄ አስቀምጧል፡፡ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ቴክኒክ ኮሚቴ በስፖርቱ ሙያ ውስጥ ያለፉና ስራውን አውቀው የሚሰሩ መሆናቸው ደግሞ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት አመቺ መሆናቸውን አመላክቷል፡፡
በፌዴሬሽኑ የቀረቡት የ2010ዓ.ም አፈጻጸሞች ላይ ሊስተካከሉ የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን የጠቆሙት የኢትዮ-ኤሌክትሪክ አትሌቲክስ ክለብ አሠልጣኝ መሠረት መንግስቱ፤ ፌዴሬሽኑ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱት ቅሬታዎች በመቶኛ ሲሰላ እየቀነሰ መሆኑን ቢያመላክትም ለአገልግሎት ወደ ፌዴሬሽኑ ቢሮ ሲኬድ አብዛኛውን ጊዜ ባለሙያዎች ስለማይገኙና ቢሮውም ዝግ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ አሳክቼዋለሁ የሚለውን እንደማይቀበሉት ገልጸዋል፡፡ አሰልጣኝ መሠረት አክለውም ፌዴሬሽኑ ለ2011ዓ.ም ያቀዳቸው 20 ግቦች ካለው የሰው ሀይል አንጻር ማሳካት ሊከብደው እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዳኞች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው፤ ፌዴሬሽኑ የአሰልጣኞችና የዳኞች ማኅበርን ያለመደገፍ ሁኔታዎችን ሊያስተካክል እንደሚገባው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የዳኞች ማኅበር እንደ ከተማ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ አገልግሎት እየሰጠ በመሆኑና የፌዴሬሽኑም ጠንካራ ክፍል እንደመሆኑ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ብዙ ጊዜ ዳኞች ላይ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም ዳኞች ከዚህ የበለጠ አገልግሎት እንዲሰጡ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ የቤት ሥራ ወስዶ ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ለሙያው የሰጡትን ተስፋ በማድነቅ ዳኞች በቁርጠኝነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተጠናክረው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ መኮንን የአትሌቶች ማኅበርን ስለ ማቋቋም በተመለከተ ውጤት ባይኖርም ሌሎች ማኅበራት ላይ ለመስራት ከተሞከረው በላይ ተሰርቷል ይላሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ አብሮ ለመስራት ካለው ፍላጎት አንጻር ማኅበሩን ማደራጀት ብቻ ሳይሆን የማኅበራትን ተወካዮች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ እንዲካተቱ አቋም መያዙንም ነው ማብራሪያ የሰጡት፡፡ ማህበሩ ስለሚደራጅበት ሁኔታ አትሌት ስለሺ ስህንና ማርቆስ ገነቴን ያካተተ ሰፊ ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩን ወደ ተግባር የመለወጡ ሂደት የአትሌቶቹ መሆን አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ስለተደረሰ ከዚህ በላይ መስራት እንዳልተቻለም አስታውቀዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ፤ የአሠልጣኞች ማኅበር ላነሱት የቢሮ ጥያቄ ፌዴሬሽኑ አቅም እንደሌለውና ፌዴሬሽኑ ለሌሎች ማህበራት ቢሮ መስጠት ቀርቶ ለራሱም በቂ የሆነ ቢሮ እንደሌለው በማንሳት የአዲስ አበባ ወጣቶችና ቢሮ ችግሩን ለመቅረፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ አክለውም በአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል በተደጋጋሚ አለመግባባቶች እየተፈጠሩ ስለመሆናቸውና ችግሩ በዘላቂነት መፈታት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
‹‹በመዲናዋ የሚገኙ ክፍለ ከተሞች ለአትሌቲክስ ስፖርት እድገት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል›› ያሉት ደግሞ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ወንዳለ ስጦታው ናቸው፡፡ አቶ ወንዳለ አክለውም ‹‹ባለፈው ዓመት ከክፍለ ከተሞች ጋር ተቀራረቦ ለመስራት ብዙ ስራዎች ተሰርተው ነበር፡፡ ነገር ግን ለእግር ኳስ እንጂ ለአትሌክስ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ነው አፈጻጸሙ ደካማ የሆነው፡፡ በቀጣይም ይህን በማስተካከል ክፍለ ከተሞች ከፌዴሬሽኑ ጋር በቅርበት ሊሰሩ ይገባል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ቢሮ ለስፖርቱ ቅን አመለካከት ስላለው ለአትሌቲክስም ሆነ ለሌሎች ስፖርቶች እድገት የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ ነው፡፡›› በማለት ፌዴሬሽኖችም ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በማድረግ በኩል መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይለሰማዕት መርሃጥበብ ለቢሮው እንግዳ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ለዚህ ቢሮ የልምድ ውስንነት ቢኖርባቸውም፤ በስፖርቱ ከአሁን በፊት በግለሰቦች የቅንነት ጉድለት ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች እንደማይኖሩ ቃል በመግባት ጭምር ተናግረዋል፡፡ ‹‹የስፖርት ባለሙያዎችን የማታል ለበት የሞራልም ሆነ የስነ ምግባር መሠረት የለኝም›› በማለትም አዲስ ተስፋ ሰጥተዋል፡፡ ስፖርት የህብረተሰቡ ቋንቋ በመሆን ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በከተማዋ ስፖርትን ለማበረታት የተጀመሩ ስራዎች በተመለከተ የሚነሱትን ቅሬታዎች እንደሚፈቱና በተለይ በማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ የተከሰቱትን ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኙ እየተሰሩ ያሉት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለአትሌቲክስ ስፖርት አመቺ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በአዲስ አበባ ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጉባኤ ላይ በ2010 በጀት ዓመት የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ክለቦችና ተቋማት የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል። በዚህም መሰረት ባለፈው ዓመት የመከላከያ አትሌቲክስ ስፖርት ክለብ የተሻለ ውጤት በማስመዘገቡ ከብሄራዊ ፌዴሬሽኑ የ300 ሺ ብር ተሸላሚ ሆኗል። እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን የ240 ሺ ብርና የ180 ሺ ብር እንደ ቅደም ተከተላቸው ተሸላሚ ሆነዋል።
ዴራል ማረሚያ ቤትና የፌዴራል ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብ ደግሞ የ100 ሺ እና 80 ሺ ብር ተሸላሚ ሆነዋል። እንዲሁም የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤትም ለአትሌቲክስ ስፖርት ላበረከተው አስተዋጽኦ የ140 ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት ከብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ተበርክቶለ ታል። የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በረጅም ጊዜ የአትሌቲከስ ስፖርት አሰልጣኝነት ውጤታማ ለሆኑ አሰልጣኞችና ዳኞች እውቅና ሰጥቷል። በሌሎች ዘርፎችም በከተማ አትሌቲክስ ስፖርት የላቀ ስራ ሰርተዋል ላላቸው ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 5/2011
አዲሱ ገረመው