
አዲስ አበባ፡– የሰው ሠራሽ አስተውሎት ልማት ባለሙያዎች ከልማት ድርጅቶች ጋር በጋራ መሥራት እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ገለጸ፡፡ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የመንግሥት እና የግል ተቋማትን ያቀናጀ የትብብር መድረክ ተካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ እና የምርቶቻቸውን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር ካሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጋር በትብብር እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡ ለዘርፉም አስፈላጊው የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግም ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆሊዲንግ 41 የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የሚያስተዳድር ግዙፍ ተቋም መሆኑን የገለጹት ብሩክ (ዶ/ር) ፤ ተቋሙ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ጠንካራ ሥራ ለመሥራት ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፤ የመንግሥት ተቋማት ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ሙከራ ክፍት በመሆን ለዘርፉ ዕድገት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡም ይሠራል ብለዋል።
እንደ ብሩክ (ዶ/ር) ገለጻ፤ በልማት ሴክተሮች ላይ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ተግባራዊ ለማድረግ ውጤታማ ተግባር ለማከናውን ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለቴክኖሎጂ ልማት ባለሙያዎች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለያዩ በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የሚፈጠሩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመደገፍ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው በገለፃቸው፤ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከተመሠረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም ለሀገር የሚጠቅሙ ሥራዎች እየሠራ መሆኑ የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለሁሉም በሚል መሪ ቃል ከግሉ እና ከመንግሥት ዘርፍ ጋር ትብብር ተፈጥሮ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ የግሉን ዘርፍ ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ በማድረግ፣ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን በመደገፍ በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሥራዎች በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
እንደ ዶክተሩ ገለጻ፤ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከዘመኑ እኩል አብሮ ለመሄድ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ ዘርፉም ለሀገር ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ ብዙ ሥራዎች በኢንስቲትዩቱ እየተሠራ ነው፡፡ በፍጥነት እያደገ ያለውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ይገኛል።
ተቋሙ ዘርፉን ለማሳደግ በሥልጠና ብቁ የሰው ሃይል ለመፍጠር ከተለያዩ ተቋማት ጋር የመሠረተ ልማት አቅርቦትና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እያደረገ በአጋርነት እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
የመንግሥትና የግል አጋርነት ዘርፉን ለማሳደግ ወሳኝ ነው ያሉት ወርቁ (ዶ/ር)፤ ከግሉ ዘርፍ ጋር የተጀመረው አብሮ የመሥራት ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ ይህንን አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በተዘጋጀው የመንግሥት እና የግሉን ዘርፍ ትብብር መፍጠር ዓላማው ባደረገው መድረክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢንስቲትዩቱ አመራሮች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ ጀማሪ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ተቋማት፣ ተማሪዎች፣ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ታድመውበታል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም