“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 መቶ በመቶ ተሳክቷል”  – ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር

አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ቴክኖሎጂን መጠቀም የግድ እንደሚያስፈልግ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ “ከቴክ ቶክ ከሰለሞን ጋር” በክፍል አንድ በነበራቸው ቆይታ ወቅት እንደተናገሩት፤ ዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 መቶ በመቶ የተሳካ እቅድ ነው። አሁን ዲጂታል 2030 እቅድ እየተዘጋጀ ይገኛል። ይህ እውን የሚሆን ከሆነ በሀገራችን እውቀት መር ኢኮኖሚ ለመገንባት መሠረት ይጥላል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ድህነት፣ ዕዳ፣ ርዳታ መጠበቅ፣ ፖለቲካዊ ችግር እና ሌሎች በርካታ ውስብስብ ችግሮች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ አንዱን ችግር ብቻ በመፍታት የኢትዮጵያን ፍላጎት ማሟላት አይቻልም። ከዚህ አንፃር ሁሉንም ችግሮች ለመፍታት በሁሉም ዘርፎች ቴክኖሎጂን መጠቀም የግድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለአብነት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሙስና፣ የአገልግሎት መዘግየት እና ሌሎች በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ይህንንም ለመፍታት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ የደህንነት ተቋማትም ዲጂታል ካሜራዎችን እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ፖሊስ በሌለበት አካባቢዎች የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የመመርመር አቅም ተፈጥሯል። ቴክኖሎጂን በሁሉም ዘርፎች ለመጠቀም እየሠራ ያለውን ሥራ እነዚህ ሥራዎች ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ቴክኖሎጂን የመጠቀም ልምምድ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገለጻ፤ የሎጀስቲክስ ሚና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ትልቁ ነው። እኤአ በ2024 ሰባት ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አስመዝግቧል። አሁን ደግሞ በዓመት ከ100 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን የሚያጓጉዝ አየር ማረፊያ ሊገነባ ነው።

ይህ ማለት በቀን 300 ሺህ የሚደርሱ መንገደኞች ይጓጓዛሉ ማለት እንደሆነ ጠቁመው፤ ይህንን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለማስተናገድ የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቴክኖሎጂ አቅሙን በማሳደግ አሁን ያለውን አቅምና ስም መጠበቅ ይችላል ብለዋል።

አለበለዚያ ግን ስሙንና ዝናውን መጠበቅ አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ መጪውን ዘመን በሚዋጅ መንገድ አየር መንገዱ ስሙን፣ ክብሩና ቦታውን ጠብቆ የሚቀጥል ይመስለኛል። የአየር መንገዱ የአውሮፕላን ብዛት እና የተሳፋሪዎች ቁጥር እያደገ መጥቷል። ይህ እድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ቴክኖሎጂ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም እድሜ ጠገብ ተቋም ነው። ከለውጡ በኋላ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ማሳደግ ተችሏል። ከዚህም ባለፈ የ4ጂ እና የ5ጂ ኢንተርኔትን በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ማስፋት ተችሏል። እንዲሁም ሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ተጀምሯል ነው ያሉት።

ይህም ኢትዮ ቴሌኮምን ለውድድር ክፍት ማድረግ በመቻሉ የተገኘ ስኬት መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም የቴሌኮም ዘርፉ ላይ የሌሎች ሀገራት ቴሌኮሞች እንዲገቡ ተፈቅዷል። ይህም ገንዘብ፣ እውቀትና የቴሌኮም ዘርፉ እንዲያድግ ማድረጉን ነው የገለጹት።

ይህንንም በተለያዩ መስኮች የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ሲሆን በዚህም የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ሀገራት ባንኮች ክፍት እንዲደረግ ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ በዚህም በቴሌኮም ዘርፉ የተገኘው ድል በፋይናንስ ዘርፉም የሚደገምበት ሁኔታ እንደሚኖር ተናግረዋል።

ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊት ስልክ በሁሉ ሰው ቤት ይኖራል ሲባል የማይጨበጥ እንደመሰለን ሁሉ፣ እንደዚሁ ዛሬም ለተለያየ ዓላማ የሚያገለግሉ ሮቦቶች በየግለሰቡ ቤት ይኖራል ተብሎ ቢነገር እምብዛም ለማመን ያስቸግር ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ነገር ግን ይህ እውን ይሆናል፣ ሮቦቶች በየቤቱ ይኖራሉ ሲሉ ተናግረዋል። ነገር ግን እነዚህ ሮቦቶች ከዚህ ቀደም ከሚታወቁ ቴክኖሎጂዎች የተለዩ ይሆናሉ ሲሉም ነው ያመላከቱት።

ከዚህ ቀደም የሚታወቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለአንድ ዓላማ ብቻ የሚያገለግሉ እንደሆኑ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ ሮቦቶች ግን በየቤቱ ሰዎች ላሉባቸው ችግሮች፣ ለሚፈልጉት ዓላማ የሚጠቀሙባቸው ይሆናሉ ነው ያሉት።

ይህን ሲያብራሩም፥ በአዕምሮ ውስንነት የሚቸገር ልጅ ያለው ቤተሰብ ልጁን ትምህርት ቤት መላክ ባይፈልግ ለልጁ በሚመች መልኩ የተዘጋጀን ትምህርት ሮቦት በቤት ውስጥ እንዲያስተምርለት ሊቀጥረው አልያም ሊገዛው ይችላል ብለዋል።

በተመሳሳይ የታመመ፣ በየጊዜው መድሃኒት መውሰድ የሚገባው አባል ያለው ቤተሰብ ሮቦት ጊዜውን ጠብቆ መድሃኒት እንዲሰጠው ሊያደርግ ይችላል ነው ያሉት።

ጠላቶቻችን የኢትዮጵያን ሕዝብ በሃይማኖት፣ በዘር መከፋፈል ዋና ዓላማቸው እና የየዕለት ሥራቸው ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ይህን እያጠና፣ እያከሸፈ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ሕልም፣ ለጋራ ትርክት በጋራ እንዲቆሙ የሚያደርግ ሮቦት ቢኖራቸው እንደሚመርጡ ገልፀዋል።

ሰዎች በሆነ ጊዜ ይደክማሉ፤ ቀን ቀን ይሠራሉ፣ ማታ ማታ ይተኛሉ፤ ሮቦት ግን ቀንም ማታም ስለማይተኛ፣ ከየትም ዓለም የሚነሳን አሉታዊ አጀንዳ እየተከታተለ ለማክሸፍ፣ ኢትዮጵያውያንን ለማንቃት የሚያስችል ብቃት ይኖረዋል ነው ያሉት።

ከሁሉ በላይ ግን “ኢትዮጵያ መበልፀግ ትችላለች” የሚልን እምነት በትውልድ ውስጥ የሚያሰርፅ ሮቦት ቢኖራቸው በእጅጉ ደስ እንደሚሰኙ ነው ያመላከቱት።

ዕውቀት ችግር እስካልፈታ ድረስ በዕውቀት መስፈርት ውስጥ ሊታይ የሚያስችል ብቃት አይኖረውም ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ እስከ ቀጣይ ዓመት ድረስ በአጠቃላይ ወደ 55 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው፤ ይህም በዓለም ላይ ትልቁ የደን ማልማት ሥራ ይሆናል ብለዋል።

በሀገራችን ቴክኖሎጂ በሲቪል ሰርቪስ፣ በሕግ ማስከበር፣ በመከላከያ፣ በሚዲያ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ ዘርፎች ያሉ ሥራዎችን ለማሳካት እና ለማሳለጥ ጥቅም ላይ እዋለ መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ሎጂስቲክስ የሚያጓጉዙ ድሮኖች እንዲሁም በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) የሚንቀሳቀሱ ተዋጊ ጀቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ ነው ያሉት።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ – ኤ አይ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በፒኤችዲ ደረጃ መሰጠት መጀመሩን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከ“ቻት ጂፒቲ” ወይንም “ዲፕ ሲክ” ጋር ተመሳሳይነት ያለው “መላ” የተሰኘ የሀገር ውስጥ ቋንቋን በስፋት የሚጠቀም የኤአይ ሥርዓት መገንባቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለጻ፤ የአፍሪካ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) ሰሚት በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል። በዚሁ ወቅት አንድ ሺህ ገደማ ድሮኖች በኤአይ ታግዘው ትርዒት ያቀርባሉ፡፡

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአፍሪካ ውስጥ ቀዳሚ ሚና መኖሩን አንስተው፤ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮም ሁሉ የአፍሪካውያን ኩራት መሆን ይችላል ብለዋል።

ዘመኑ የመረጃ ነው፤ መረጃ ማምረት፣ መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ እንደዛ ካልሆነ ብልፅግና እንደማይመጣ ገልፀዋል።

መበልፀግ 4 ዋና ነጥቦችን የያዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ አንደኛው በሃርድዌር ወይም በመሠረተ ልማት ግንባታ እንደሆነ ገልፀዋል።

ይህም የምንፈልገውን ለውጥ ለማሳለጥ በእጅጉ ጠቀሜታ ያለውና ለሌሎችም መሠረት የሆነ ነው ሲሉ ገልፀውታል።

እንደ መንገድ፣ የኤሌክትሪክ መስመር፣ የቴሌ ኮሙኒኬሽን ዳታ ሴንተር ዝርጋታ እና የመሳሰሉትን እንደሚያካትት አብራርተዋል።

ሁለተኛው መበልፀግ በሂውማንዌር ወይም በሰው ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የተገነቡትን መሠረተ ልማቶች ለመጠቀም፣ ለማሻሻል፣ ከዛም አልፎ አዳዲስ ፈጠራዎችን ለማመንጨት የሰው ልጅ ብቃት እንዲኖረው እና እውቀት እንዲያገኝ ማስቻል ነው ብለዋል።

ሶስተኛው መበልፀግ በኢንፎዌር ወይም በመረጃ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን በደረስንበት ዘመን ሰዎች እንደ መረጃ አጠቃቀማቸው በቅጽበት በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ሊያተርፉ አልያም ሊከስሩ እንደሚችሉ አንስተዋል።

አራተኛው መበልፀግ በተቋማዊ ግንባታ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም አንድ ሰው ሲመጣ የሚገነባ፣ ሲሄድ ደግሞ የሚፈርስ መሆን የለበትም ብለዋል።

ምንም ነገር ሲጀምር መዳረሻው መታወቅ አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ ጨርሶ የሚጀምር ከሆነ እና ድርጊት ካለ ስኬት ይከተላል፣ አይቀሬ ነው ሲሉ ነው የገለፁት።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You