
ያደጉ የሚባሉት ሀገራት አሁን ለደረሱበት እድገት በዋነኛነት የሚጠቀሰው ለፈጠራ ሰዎች እና ሥራዎቻቸው የሰጡት ትኩረት ነው። አሁናዊው ዓለምም ቢሆን ለደረሰበት ሁለንተናዊ እድገት የፈጠራ ባለአዕምሮዎች እና ተጨባጭ የሆነው ሥራቸው የማይተካ አስተዋፅዖ አበርክቷል። ለፈጠራ አቅሞች የተሰጠ ልዩ እንክብካቤ እና ጥበቃም የዓለምን ገጽታ ለመቀየር ትልቅ አቅም ሆኗል።
ባለንበት ዘመን ሆነ በቀደሙት ዘመናት ሰፊ የሥልጣን እና የሥልጡንነት ትርክት ያላቸው ሀገራት፤ ከትርክታቸው በስተጀርባ ትላልቅ የፈጠራ አዕምሮዎች እና ለዚህ አዕምሮ የተገዙ ትውልዶች አሏቸው። የሥልጣኔያቸውም ቀጣይነት የተመሠረተው እነዚህን አዕምሮዎች ዘመንን በሚዋጅ እሳቤ እና የመፍጠር መነቃቃት እየገሩ የመሄዳቸው እውነታ ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያንም የሩቅ ዘመን የትላልቅ ሥልጣኔዎች ባለቤት ከመሆናችን አኳያ፤ ለትላልቅ ፈጠራዎች የተገዙ፤ በዚህም ለብዙ ትውልዶች የመንፈስ ብርታት፤ የብሔራዊ ክብር ምንጭ የሆኑ፤ እስከዛሬም ድረስ ዓለምን እያስደመሙ የሚገኙ ጥልቅ እና ምስጢር የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች አስቀምጠውልን አሸልበዋል።
ለዚህም የአክሱም ሐውልቶችን፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ..ወዘተ ማንሳት ይቻላል፤ እነዚህ ከፍ ባለ እውቀት እና የመፍጠር ብቃት እውን የሆኑ ቅርሶቻችን በፈጠራ የተካኑ ትውልዶች ልጆች መሆናችንን በአደባባይ የሚመሰክሩ፣ ለፈጠራ እንግዶች እንዳልሆንንም አመላካች የታሪክ ምስክሮች ናቸው።
አንድም ለዘመናት የመጣንበት ያልተገራ የመገዳደል እና የነበረን ረግሞ የማጥፋት የፖለቲካ ባህል፤ ከዛም በላይ ለፈጠራ ሰዎች እና ለባለአዕምሮዎች የሰጠነው ያልተገባ ስፍራ፤ የተሳሳተ ትርክት እና የአግላይነት እሳቤ እንደ ሀገር ፈጠራን በተመለከተ ለከፋ ድንዛዜ እና ድባቴ ዳርጎናል። በቀደሙት አባቶቻችን አዕምሮ ከመኮፈስ ባለፈ ወደ ራሳችን እንዳንመለከት አድርጎናል።
ችግሩ እንደ ጥላ ከሚከተለን ግጭት እና ጦርነት ጋር ተዳምሮ አሁን ላለንበት ድህነት እና ኋላቀርነት፤ ጠባቂነት እና ተመፅዋችነት አጋልጦናል። ትናንት ላይ በብዙ ተግዳሮት ቆሞ የቀረውን የትውልዶች የመፍጠር አቅም ማደስ፤ በዚህም ነገዎቻችንን ብሩህ እድርገን ማስቀጠል እንዳንችል ፈተና ሆኖብናል።
በየዘመኑ በብዙ ቁጭት ይህንን የፈጠራ አዕምሮ ለመመለስ የተደረጉ ጥረቶች፣ መሠረታዊ የሆነ አስተሳሰብ ተሐድሶ መፍጠር ባለመቻላችን ስኬታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በዚህም ብዙ ትውልዶች ሀገርን ወደ ከፍታ፣ ሕዝባችንን ወደ ተሻለ ሕይወት የሚያሻግሩ የፈጠራ አቅሞቻቸውን ይዘው አንቀላፍተዋል።
ይህን ሀገራዊ ስብራት ለማከም አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ጥረት፣ በርግጥም የትናንት ትውልዶች የፈጠራ የዘር ፍሬ በዚህ ትውልድ ማንነት ውስጥ መኖሩን ያመላከተ ነው፤ አሁን በትውልዱ የሚታየው የፈጠራ መነቃቃት ቀደም ሲል ከነበርንበት የፈጠራ ድንዛዜ እና ድባቴ እየወጣን ስለመሆናችን ተጨባጭ ማሳያ ነው።
ይህ በትውልዱ ውስጥ ያለ የፈጠራ መነቃቃት፤ ብሩህ ነገዎቻችንን፣ በራሳችን፣ ለራሳችን ተጨባጭ ለማድረግ “አልፋ እና ኦሜጋ” ነው። ብዙ ትውልዶች ናፍቀውት፣ በብዙ መቃተት አምጠው ማዋለድ ያልቻሉትን ሀገራዊ ክብር እና ማኅበረሰባዊ ልዕልና እውን ማድረግ የሚያስችል የፍጻሜው ጅማሬ ነው።
እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች ዓለም አሁን ላይ ከደረሰበት ደረጃ አንሰው የሚታይበት ሁኔታ ቢኖርም፣ ዘመን ከተሻገረ የከፋ እንቅልፍ፣ ድንዛዜ እና ድባቴ የመውጣታችን ትልቅ ማሳያ ናቸው፣ ጅማሬያቸው ትንሽ ቢመስልም፣ የነገይቱን የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር አልፋ እና ኦሜጋ ናቸው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም