‹‹“የባሕር በር ጥያቄ የቀጣዩን ትውልድ ዕጣ ፋንታ የሚወስን ጉዳይ ነው”›› -አምባሳደር ሙክታር ዋሬ

 -አምባሳደር ሙክታር ዋሬ በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጸሙ ስህተቶችን የሚያርም እና የቀጣዩን ትውልድ ዕጣ ፋንታ የሚወስን ጉዳይ ነው ሲሉ በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሙክታር ዋሬ ገለጹ።

አምባሳደር ሙክታር ዋሬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባሕር ላይ ይዞታ የነበራትና ቀይ ባሕርንም በባለቤትነት ስትቆጣጠር የቆየች ሀገር ብትሆንም በተፈጸሙባት ሴራዎች ከቀይ ባሕር እንድትገለል ተደርጓል።

አንድ ሺህ 800 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የቀይ ባሕር ይዞታ በቁጥጥሯ ስር ያኖረችና ለወጪና ገቢ እቃዎች በርካታ ወደቦችን የምታስተዳድር ሀገር ነበረች ያሉት አምባሳደር ሙክታር፤ ሆኖም የኢትዮጵያን ማደግ በማይፈልጉ ኃይላት ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ አድርገዋታል ብለዋል።

አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ ባሕር አልባ በመሆኗም ፀጥታ እና ደኅንነቷን አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለማረጋገጥ አዳጋች ከመሆኑ ባሻገር ለወደብ ኪራይ በርካታ ዶላሮችን ለመክፈል መገደዷንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ ጥያቄውን በውስጡ ሲያብሰለስል መቆየቱን የተናገሩት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ውጪ ቀይ ባሕርንም ከኢትዮጵያ ውጭ ማሰብ የማይቻል በመሆኑ የባሕር በር ጥያቄው ወቅቱን የጠበቀ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወደብ አልባ ከሆኑት 16 ሀገራት አንዷ ብትሆንም ወደብ አልባ የሆነችባቸው አመክንዮዎች ግን ታሪካዊም ሆነ ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው በመሆናቸው የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ አይቀሬ መሆኑን አመልክተዋል።

አምባሳደሩ እንዳብራሩትም፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ 130 ሚሊዮን እንደሚደርስ እና በአጠቃላይም የባሕር በር የሌላቸውን ሀገራት ሕዝብ 1/3ኛውን የሚሸፍን ሀገር ይዞ ያለባሕር በር መኖር የሚታሰብ አይደለም። በዚህም ላይ ኢኮኖሚው በየጊዜው እያደገ የሚሄድ በመሆኑ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ መቀጠል የሚታሰብ አለመሆኑም አስረድተዋል።

የባሕር በር ጥያቄ አሁን ካለው ትውልድ ባሻገር የመጪውንም ትውልድ ዕጣ ፋንታ የሚወስን በመሆኑ መንግሥት ይዞ የተነሳውን ጥያቄ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት የሚቀበሉት መሆኑንም ተናግረዋል።

ይሄንን የሚያህል ሕዝብ ይዞ የባሕር በርና ወደብ የተነፈገ ሀገር የለም ያሉት አምባሳደሩ፤ ከ60 ኪሎ ሜትር የባሕር ርቀት ላይ እየተገኙ ኢትዮጵያውያን ወደብ እና የባሕር በር እንዳይኖራቸው መፈረዱ ኢ-ፍትሐዊ ውሳኔ መሆኑም ጠቁመዋል።

አምባሳደር ሙክታር እንደገለጹትም፤ ኢትዮጵያ በግፍ ከይዞታዋ እንድትነቀል ከመደረጓ ውጪ ባለቤትነቷን የሚከለክላት አንዳችም ዓለም አቀፍ ሕግ የለም። ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ የሆነችበትም ሆነ ከቀይ ባሕር እንድትገለል የተደረገበት አካሄድ ምንም አይነት ሕጋዊ መሠረት የሌለው ነው።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በተደረጉ እልህ አስጨራሽ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተቀባይነት እያገኙ መምጣታቸውን ገልጸው፤ በዓለም አቀፍ መድረኮችም እውቅና ከማግኘቱም ባሻገር የተለያዩ መሪዎችም በአንደበታቸው መስክረውለታል። ይህም የዲፕሎማሲ ውጤት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You