የንግድ ባንክ ሴቶች የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ እሁድ ይረከባሉ

 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን የ 2017 ዓም የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕርምየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል። የውድድር ዓመቱ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻና 26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ፣ ነገና ከነገ በስቲያ ሲካሄዱ የንግድ ባንክ ሴቶች እሁድ አዳማ ከተማን በሚገጥሙበት ጨዋታ ዋንጫውን ይረከባሉ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን ከቀናት በፊት ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 5ለ0 ማሸነፉን ተከትሎ አንድ ጨዋታ እየቀረው ከወዲሁ ቻምፒዮን መሆኑ ይታወቃል። በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕርሚየር ሊግ ዋንጫን ሲያነሳ የዘንድሮው ለተከታታይ አምስተኛ ጊዜ ሲሆን በአጠቃላይ በታሪኩ ለስምንተኛ ጊዜ ቻምፒዮን ሆኖ ፈፅሟል። ይህም በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያው ቡድን ያደርገዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን በዚህ የውድድር ዓመት ምንም ጨዋታ ሳይሸነፍ መጓዝ የቻለ ሲሆን፣ በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያን በመወከል የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር ላይ የሚሳተፍ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ የሴቶች ቡድን አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በ26 የአሠልጣኝነት ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ 25 ጨዋታ ሳይሸነፍ የዘንድሮውን ዋንጫ በማሸነፉ አድናቆት ተችሮታል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በ25 ጨዋታ 18ምቱን አሸንፈው 7ቱን አቻ ተለያይተው አንድ ቀሪ ጨዋታ እየቀራቸው በ61 ነጥብ የሊጉ ሃያል መሆናቸውን አረጋገጠዋል። አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በ26 የአሠልጣኝነት ታሪኩ 27 ዋንጫ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ደግሞ በ14 ዓመታት 8ቱ የሊግ ዋንጫን ጨምሮ 16 ዋንጫ ማንሳት ችሏል።

አሠልጣኙ ከንግድ ባንክ ጋር ክብረወሰን በሆነ 50 ጨዋታ ወይም 4550 ደቂቃ ሽንፈት ሳይገጥመው ተጉዟል። በአሠልጣኝነት ሕይወቱ ከየካ ክፍለ ከተማ ጋር 2 ፣ ከሴንትራል ጤና ኮሌጅ ጋር 3 ፣ ከአዲስ አበባ ምርጥ ጋር 6 ዋንጫ ሲያነሳ ከነገሰበት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ደግሞ 8 የፕሪሚየር ሊግ በታሪክ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ የመጀመሪያ ያደረገውን አንድ የሴካፋ ዋንጫ ፣ 1 የአዲስ አበባ አንደኛ ዲቪዚዮን፣ 1 የጥሎ ማለፍ ፣ 2 የአሸናፊዎች አሸናፊ እና 3 ሰሜን ማዕከላዊ ዋንጫውን አንስቷል።

በወንዶች ከፍተኛ ሊግ ፉክክር የ2018 ፕሪሚየር ሊግን መቀላቀሉን ያረጋገጠው ሸገር ከተማ በሴቶችም በቀጣይ ዓመት የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ መሆኑን ቀደም ብሎ ማረጋገጡ ይታወቃል። ሸገር ከተማ በ23ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ወላይታ ድቻን 3-2 ማሸነፋቸውን ተከትሎ ነው ሦስት ጨዋታ እየቀራቸው ወደ 2018 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ማድጋቸውን ያረጋገጡት።

ንግድ ባንክ ቻምፒዮን መሆኑን ቀደም ብሎ ማረጋገጡን ተከትሎ ከሊጉ ላለመውረድ የሚደረገው ትግል በመጨረሻው ሳምንት መርሃግብር ጨዋታዎች ይበልጥ አጓጊ ነው። ሀምበሪቾ ሁለት ነጥብ ብቻ በመያዝ ቀደም ብሎ መውረዱን አረጋግጧል። አዲስ አበባ ከተማ በ20 ነጥብ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛል። ባህርዳር ከተማና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በእኩል 21 ነጥብ ከፍ ብለው ቢገኙም የመጨረሻውን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። አዲስ አበባ ከተማ ነገ ሀምበሪቾን ሲገጥም፣ ባህርዳር ከተማ መቻልን፣ ቂርቆስ ክፍለከተማ ደግሞ ሲዳማ ቡናን ይገጥማል።

የንግድ ባንኳ ሴናፍ ዋቁማ በ21 ግቦች የኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱን ስትመራ፣ የሃዋሳ ከተማዋ እሙሽ ዳንዔል በ14 ግቦች ትከተላለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You