‹‹በሰው የሳቁት በራስ ይደርሳል›› ሲባል ሰምቼ ይኸው 24 ሰአት ሴቶችን በሚላከፉት ወንዶች እስቃለሁ፡፡ ግን ‹‹ወፍ የለም›› 1ሺ ሴቶች ብቻ ናቸው የሚከተሉኝ፡፡ (በፌስ ቡክ)
የቅርብ ጓደኞቼ በዚህ ሁኔታዬ እብድ ይሉኛል፡፡
ድርጊቴ እብደት ከመሰላቸው ግን እንደ እነርሱ ሥራ ከመፍታት ይሻለኛል፡፡ ህይወት በየመንገዱ ዳር ዘፍዝፋ ሲጋራና ጫት ከምታስጨብጠኝ ጠበሳ ይሻለኛል፡፡ ይህ ጊዜ የኔ ወርቃማው የጠበሳ ዘመን ነው፡፡ በእርግጥ በአለካከፌ ልብ የለሽ ነገር ግን ‹‹ወንድ ነን›› ከሚሉት ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ ደግሞም ለለከፋ ያህል እንጂ ማንንም ማግባት አልፈልግም፡፡ ወንዶች ጋብቻ ሲነሳብን በራችን ላይ ሳማ የምንተክል ይመስል ግብግብ ያደርገን የለ፡፡
እንደለመድኩት የታክሲ ውስጥ ለከፋ ለመጀመር አንድ ወር ሙሉ በሁሉም አቅጣጫ የሚሄዱትን ታክሲዎች ማደን ጀመርኩ፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የኔ ወርቃማው የለከፋ ዘመን ነው፡፡ የምቀመጠው ከኋላ ወንበር ነው፡፡ ታዲያ እኔ ወንበር ከመያዜ በፊት የምትለከፍ ሴት ከኋላ ወንበር ላይ መግባቷን ማረጋገጥ ስለሚኖርብኝ ወደ መስኮቱ ጠጋ ብዬ እመለከታለሁ፡፡ ይህ አይነት የቅንጦት ድርጊት የታክሲ ሰልፍ ባለባቸው አካባቢዎች አይሰራም፡፡ ምክንያቱም እንኳን ከኋላ የተቀመጠውን ሰው አማርጦ በማየት መግባት ይቅርና የትርፍ ትርፍ ላይ የተቀመጠውን ሰው ለማስተዋል እንኳን ጊዜ አይበቃም፡፡
ለዛሬ ከፒያሳ መገናኛ በሚጭነው ታክሲ ውስጥ በለመድኩት ቦታ ተቀምጫለሁ፡፡ አጠገቤ ‹‹ከቀሚስ የተሰራ›› አጭርዬ ቀሚስ ለብሳ፣ ከፊቷ የሚበልጥ ስፋት ያለው መነጽሯን አድርጋ፣ ጧ…ጧ…ጧ የሚል የማስቲካ ድምጽ እያሰማች ዘና ብላ የተቀመጠች እንስት አለች፡፡ የምታኝከው ማስቲካ ‹‹ጦር ማስቲካ›› እንድሆነ ከጩኸቱ ማስተዋል ችያለሁ፡፡ ልጅቷን ለማዋራት የመነሻ ቃላት ይሆኑኝ ዘንድ ካነበብኳቸው መጽሐፍት ስለ ፍቅር የሚያወሩትን ባስታውስ ከየት ላምጣው፡፡
ከትንሽ ደቂቃ ጉዞ በኋላ የመጣው ይምጣ አልኩና ድፍረት ቢጤ መዘዝ አደረግኩ፡፡ ምክንያቱም ይህ ጊዜ የኔ ወርቃማው የጠበሳ ዘመን ነው፡፡ ጅንጀናውን ለመጀመር ብዬ ወሬ እንደመጀመር ያህል ‹‹ውይ የዛሬው ሙቀት ድንጋይ ያቀልጣል አይደል ቆንጂት?›› ከማለቴ ‹‹ለዚያ ነዋ ያላበህ›› አለችኝ፡፡ በፍርሃት ከግንባሬ የሚፈሰውን ላቤን እየጠቆመችኝ፡፡ አንድ ሁለት ጊዜ ሌሎች ጠበሳ ነክ ቃላትን ወርወር ባደርግላትም ‹‹አንተ ሂድ ከዚህ! በኩርኩም ብዬ ኖርማል እንዳላደርግህ›› ስትለኝ ከዚህ ቀደም ባለማወቅ ካራቲስት ስላከፍ የደረሰብኝን የጫማ ጥፊ መዓትና ለሳምንት ያህል ጎድኔን ስቆጥር መክረሜ ታወሰኝና ፊቴን አዙሬ ተቀመጥኩ፡፡ ልቤ ግን አሁንም ማጉረምረም አልተወም፡፡
የኔን የጠበሳ ወርቃማ ዘመን በስኬት ሳልጨርስ ተስፋ አልቆርጥም አልኩና በዚሁ ቀን በአንዱ ታክሲ ውስጥ ሌላ ጉድ ገጠመኝ፡፡ በጣም ቆንጆ የሚል ቃል የማይመጥናት መልከ መልካም ሴት ከኋላ ወንበር አጠገቤ ተቀምጣለች ከልጅቷ በሌላኛው በኩል የተቀመጠው ሌላው የኔ ቢጤ እንቅልፍ እንዳስቸገረው ዓይነት ልጅቷ ትከሻ ላይ በተደጋጋሚ ይተኛል፡፡ በማያገባኝ ነገር ውስጥ ገብቼ በቅናት እርርር አልኩኝ፡፡
ሲፈልግ ወገቧ ላይ ሲፈልግ ጉልበቷ ላይ ይጋደማል፡፡ ምርቃና እንዳስቸገረው ሰው ሲቅበዘበዝ ልጅቷ መናገር ፈርታ ኖራ ወደ እኔ ፈቀቅ ስትል የመጥበስ እድሉን ለማግኘት ይበልጥ ተመቸኝ፡፡ ኋላ ላይማ ቀና ብሎ አላይ አለኝ እንጂ በደንብ እንዲደገፋት በዓይን ጥቀሻ ልነግረው ዝግጁ ነበርኩ፡፡ ልጅቷም ከዚህ የኔ እጅ እጅ የሚል የጠበሳ ወሬ፣ ከዚያ ደግሞ ጭነት እንደበዛበት አህያ ያዘነበለ ሰው ሲያስቸግራት በድንገት ረዳቱን ጠርታ ‹‹አባት ቦታ ቀይረኝ የመኪና ትራስ አደረገኝ እኮ›› አለችው፡፡
ታክሲ ውስጥ ያሉት ተሳፋሪዎች ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሳቅ አሰሙ፡፡ ንግግሯ እኔን ለሳቅ ባይጋብዝም ሳቁን ለመካፈል ያህል ሰዎቹ ስቀው ሲጨርሱ ብቻዬን አገጠጥኩ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተናደደች ልጅት ይቅርታ አሳልፈኝ ልወርድ ነው አለችኝ፡፡ ቦታው ሌላ ትራንስፖርት እንደማይገኝበት ስላወቅኩ አዛኝ መስዬ አብሬያት ወረድኩ፡፡ እናቱ…እናቱ… እያልኩ ጥቂት ተከተልኳት፡፡ በሰከንዶች ሽርፍራፊ ከስፓልቱ ተንጋልዬ የለከፋ ውጤትን ቀመስኩት፡፡ (በተለመደው ካራቴ) ብዙ ሰዎች ከበውኝ ሲስቁብኝ ከቆዩ በኋላ ጎተት አድርገው ከመንገዱ ዳር አስቀመጡኝ፡፡
የጠበሳ ወርቃማው ዘመኔን በዝምታ ከማልፍ ብዬ አሁን ላይ አቅሜን መጥኜ መላከፍ ጀምሬያለሁ፡፡ የኔ ቢጤ የሆኑ አንገሽጋሽ ጠባሾች ግን ያለአቅማቸው ፍቅራቸውን በግጥም መግለጽ ይወዳለሉ፡፡
ኃያሉ ፍቅርሽ ————— ያ ኃያል ፍቅርሽ
ጉድ ሰራኝ ቄጠማ ሆነልሽ ክንዴ፤
ውስጥ ውስጤን እያስጨነቀ አልወጣም አለኝ ከሆዴ! ዓይነት ግጥም ለለከፋ ምን ሊረባ ነው፡፡ እንዲህ ተብሎ የተገጠመላት እንስት በእርግጠኝነት ‹‹ለመሆኑ ግጥሙን የጻፍከው መጸዳጃ ቤት ስትገባ ድርቀት አስቸግሮህ ነው እንዴ? አለማለቷን እጠራጠራለሁ፡፡
በዚህች ምድር ለጾታዊ ለከፋ ሲሉ ልባቸው የደማ ዕልፍ አዕላፋት ተለካፊዎች መኖራቸው አይካድም፡፡ ሆኖም እውቅና የሚሰጣቸው ቀርቶ የሚናገርላቸው እንኳን የለም፡፡ እንግዲህ ተላካፊዎች በፍቅር ራሳችንን እንድንችል ዋስትና የሚሆኑን የምንለክፋቸው ሰዎች ሳይሆኑ የራሳችን የልብ ቁጥብነት ነው፡፡ የቃላት ተኳሽ የልብ ፊት አውራሪ ጠባቂያችንም ምላሳችን ናት፡፡ እርሷ ካልተቆጠበች የውትወታ አውታሩ ልባችን በሠላም መጓዝ አይችልም፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 5/2011
አዲሱ ገረመው
Your blog post was fantastic, thanks for the great content!
Love this blog! The content is always so relevant and insightful, keep up the great work!
Thank you for sharing your personal experience and wisdom with us Your words are so encouraging and uplifting
This blog has opened my eyes to new ideas and perspectives that I may not have considered before Thank you for broadening my horizons