
የ2017 ዓ.ም ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የክለቦች ቻምፒዮና በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እየተካሄደ ይገኛል።
ቻምፒዮናው ከትናንት በስቲያ ሲጀመር የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሲሳይ ዮሐንስ በውድድሩ መክፈቻ እንደገለፁት፣ ይህ ውድድር በሁለቱም ፆታ አዋቂዎችና ታዳጊዎችን በማወዳደር በቀጣይ ግንቦት ወር 2017 ዓ.ም በማዳጋስካር በሚደረገው የምስራቅ አፍሪካ የአዋቂዎች ቻምፒዮና ላይ የሚሳተፉትንና በሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም በናይጀሪያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ የታዳጊዎች ቻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፍ ብሔራዊ ቡድን አባላትን ለመምረጥ ነው።
“ኢትዮጵያ በጠረጴዛ ቴኒስ ያላት ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ እያሳየች ነው” ያሉት ኢንጂነር ሲሳይ ኢትዮጵያ ከ45 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በግንቦት ወር በኳታር ዶሃ በሚካሄደው የዓለም ቻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ አራት ሴትና አንድ ወንድ ተጫዋቾችን ለብሔራዊ ቡድን ማስመረጥ መቻሏን ምሳሌ አድርገው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቀልቤሳ ኤባ፣ በበኩላቸው ይህ የበጀት ዓመቱ ሁለተኛው ዙር መርሃግብር መሆኑን በማስታወስ በክለቦች መካከል ጤናማ የስፖርት ፉክክር እንዲኖር፤ ክለቦች እርስበርሳቸው ልምድ እንዲለዋወጡ ለማድረግ ብሎሞ ስፖርቱን ለማነቃቃት ቻምፒዮናው ሚና እንዳለው ተናግረዋል። አክለውም፣ ቻምፒዮናው ክለቦች የሥልጠናቸውን ውጤት እና የተጫዋቾችን አቅም ለመፈተሽ ይረዳል ብለዋል። በሀገር ደረጃም የአዋቂዎችና የታዳጊ ስፖርተኞችን በዕድሜያቸው ልክ ምርጥ ስፖርተኞችን ለመለየት ያስችላል ብለዋል።
በዚህ የክለቦች ቻምፒዮና አስር ክለቦች የሚወዳደሩ ሲሆን የትግራይ ክልል ቴኒስ ቡድን በተጋባዥ እንግድነት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ውድድሩ በሁለቱም ፆታ በነጠላና በቡድን በአዋቂዎችና በታዳጊዎች የዕድሜ ክልል በማወዳደር ነገ እንደሚጠናቀቅ ከወጣው መርሃግብር ለማወቅ ተችሏል።
የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን አንደኛ ዙር የክለቦች ቻምፒዮና ባለፈው ጥር መጀመሪያ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ ዘጠኝ ክለቦችን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ያፎካከር ነበር።
የመጀመሪያው ዙር ቻምፒዮናው በቱኒዚያው የአፍሪካ ቻምፒዮና የሚሳተፍ አሸናፊ ክለብ ለመምረጥ፣ ክለቦች የእርስ በርስ ልምድ ልውውጥ እንዲወስዱ ለማድረግ፣ ምርጥ ተተኪ ስፖርተኛችን ለመለየት እንዲሁም ስፖርቱ ያለበትን ደረጃ ለመገምገም ዓላማ ያደረገ ነበር።
በሦስት የእድሜ ካታጎሪ ተከፍሎ በሁለቱም ፆታ ከጥር 2-5 በተካሄደው ቻምፒዮና የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ ወወክማ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ፒንግ ፖንግ፣ ፌኒክስ፣ ፌዴራል ፖሊስና አራዳ ክፍለ ከተማ ክለቦች ተሳታፊ ነበሩ።
ብዙ ትኩረት እየተሰጣቸው ከማይገኙ ስፖርቶች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ በአፍሪካና ሌሎች ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች አበረታች እንቅስቃሴ ይደረግበታል። በዚህም ዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን በዚህ ዓመት በፈረንጆቹ ሜይ ወር ባወጣው የዓለም ሀገራት የጠረጴዛ ቴኒስ ደረጃ መሠረት ኢትዮጵያ በወንዶች የቡድን ከዓለም አርባ ሁለተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ስድስተኛ ላይ ትገኛለች። በተመሳሳይ በሴቶች የቡድን ደረጃ ከዓለም ሃምሳኛ ከአፍሪካ ደግሞ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም