
ደራሲ አሌክስ አብርሃም ሰሞኑን ‹‹ከዚያም ከዚህም ያልሆነ ትውልድ›› በሚል ርዕስ በማህበራዊ ገጹ የጻፈውን አንድ ጉዳይ ብዙዎች ወደውት ነበር:: ጉዳዩ በአጭሩ ሲጨመቅ፤ ከ35 እስከ 45 ዓመት ውስጥ ያለው ጎልማሳ ካለፈው ትውልድም፤ ከአሁኑ ትውልድም ያልሆነ የተከዳ ትውልድ ነው የሚል ነው:: ምክንያቱን ሲያስቀምጥም፤ ይህ ትውልድ ልጅ እያለ ትምህርት የሚያስከብር እና ጥሩ ኑሮ የሚያኖር መሆኑን እያየ እና እየተመኘ ያደገ ትውልድ ነው:: ታላላቆቹን መሆን እየተመኘ አደገ:: እነርሱ የደረሱበት ሲደርስ ግን ትምህርት ድሮ የነበረውን ክብርና ሞገስ አጣ:: ጥሩ ኑሮ የሚያኖር አልሆነም::
እንደ አሁኑ ትውልድ እንዳይሆን ደግሞ ያደገበት ሞራል እና ሥነ ምግባር የማይፈቅድለት ሆነ:: የአሁኑ ትውልድ እንደ ቲክቶክ ባሉ ዘመን የወለዳቸው ቴክኖሎጂዎች ባህልና ወግ፣ ሥነ ሥርዓት ሳይገድበው በብልግና ታዋቂ ሆነ:: ነውር እና ፀያፍ ነገሮችን በመናገር፣ በማሳየትና በማድረግ ብዙ ተከታይ ማፍራት ቻለ:: በዚህም ማስታወቂያ ማግኘት እና ባለገንዘብ መሆን ቻለ:: መኪና መግዛት እና ጥሩ ኑሮ መኖር ቻለ::
ከዚያም ከዚህም ያልሆነ የተባለው ትውልድ ደግሞ ከሁለቱም ሳይሆን ቀረ:: እንደ ታላላቆቹ እንዳይሆን ትምህርት የሚያስከብርና ጥሩ ኑሮ የሚያኖር አልሆነም፤ እንደ ታናናሾቹ እንዳይሆን ደግሞ ያደገበት ሞራልና ሥነ ምግባር ሊፈቅድለት አልቻለም:: አሌክስ አብርሃም ‹‹ከዚያም ከዚያም ያልሆነ ትውልድ›› ያለው ይህንን ነው::
አሁን ወደራሴ ትዝብት ልሂድ::
በአሌክስ አብርሃም ሃሳብ እስማማለሁ፤ የገለጻቸው ነገሮች ትክክል ናቸው:: ትምህርት ጥሩ ኑሮ ማኖሩ ቢቀር እንኳን፤ ቢያንስ ሊያስከብር አልቻለም:: ከአንድ ጀግና መምህር ይልቅ አንድ ባለጌ ቲክቶከር የተሻለ እየተከበረ ነው፤ ማስታወቂያ ተፈልጎ እየተሰጠው ነው:: ሥነ ምግባር የሚባል ነገር እንዳይኖር እየተደረገ ነው::
ያም ሆኖ ግን በአሌክስ አብርሃም ሃሳብ የማልስ ማማባቸው ነገሮችም አሉ:: ሃሳብ ነውና ነገሩን መነሻ በማድረግ ስለዚህኛውም ሆነ ስለዚያኛው ትውልድ ሃሳቦቻንን ብናንሸራሽር ዘመናዊነት ነው::
የአሁኑን ታዳጊ ትውልድ በዚህ ልክ ማጣጣልና ማጥላላት አግባብ አይመስለኝም:: አንዳንድ ነገሮች ዘመን ይሽራቸዋል:: ነገሮች ሁሉ እኛ በነበርንበት ልክ ይሂዱ ማለት አይቻልም:: እኔም የዚያው ትውልድ አካል ስለሆንኩኝ የ90ዎቹን ትውልድ በሚገባ አውቀዋለሁ፤ ተሽኮርማሚ ነው:: ያ ግን ልክ ነው ወይ ነው ጥያቄው!
በነገራችን ላይ የ90ዎቹ ትውልድ ማለት በ1990ዎቹ የተወለደ ማለት አይደለም:: የትምህርት ቤት ትዝታውንና ልጅነቱን በ1990ዎቹ ያጣጣመ ማለት ነው:: ሥብዕና የሚቀረጸው በዚህ ዕድሜ ስለሆነ የ90ዎቹ ትውልድ ይባላል:: ለምሳሌ፤ የ60ዎቹ ትውልድ ማለት በ1960ዎቹ ውስጥ የተወለዱ ማለት አይደለም፤ የተወለዱት ከዚያ በፊት ነው:: አፍላ ዕድሜያቸው በነበረበት ነው የ60ዎቹ ትውልድ የተባለው:: ስለዚህ ቢያንስ ከ35 እስከ 40 ዓመት ያለውን የ90ዎቹ ትውልድ ልንለው እንችላለን::
ይህ ትውልድ ተሽኮርማሚ ትውልድ ነው:: ይህ ተሽኮርማሚነቱ ግን ትክክል አይመስለኝም:: ወግና ሥርዓቱን ጠብቆ ደፋር መሆን አለበት:: ከምቾት ክበብ (Comfort zone) መውጣት አለበት:: ግራ የተጋባ ይመስላል:: ግራ የተጋባው ደራሲው እንዳለውም ከታላላቆቹም ከታናናሾቹም ስላልሆነ ነው:: ከታላላቆቹም ከታናናሾቹም ያልሆነው ግን ግማሹን ዘመን ሽሮት ነው፤ ግማሹ ስንፍናው ነው፤ ግማሹ ደግሞ እንደ ሀገር የተፈጠረው መዘናጋት ነው:: ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ማስተካከል የሚችለውም ይሄው ትውልድ መሆን አለበት::
ሃሳብ ነውና ሌላም ነገር እንጨምር! የምር ግን ታላላቆቹ የተሳካላቸው ነበሩ? ትምህርት በዚያን ጊዜ ያስከብር እንደነበር ግልጽ ነው፤ ጥሩ ኑሮ ያኖር እንደነበርም ግልጽ ነው:: ዳሩ ግን በዚያን ጊዜ ደግሞ ብዙ ምቹ ያልሆኑ ነገሮች ነበሩ:: የአሁኑ መሠረተ ልማት አልነበረም፣ የአሁኑ ቴክኖሎጂ አልነበረም:: በዚያን ዘመን ትምህርት ቢያስከብርም ዳሩ ግን ከፍተኛ ድካም ነበረው:: በእግር ብዙ ኪሎ ሜትር አቋርጦ መሄድ የግድ ነበር:: ለሀገር የሠሩት ውለታ ስለሆነ ሊኮሩበት ይገባል:: ከፍተኛ የህሊና ርካታ ያገኙበታል፤ በዚህ እንቀናባቸዋለን:: ዳሩ ግን እኛ ያገኘነውን ዕድል ደግሞ ከእነርሱ የተሻለ አድርገን መጠቀም እንጂ የእነርሱን ብቻ እንደ መታደል መቁጠር መፍትሔ አያመጣም::
የአሁኑ ትውልድ (በተለምዶ የሚሊኒየም ትውልድ የምንለው) ደግሞ ከባህልና ወግ፣ ከሥነ ሥርዓት እያፈነገጠ ይመስላል:: በተለይም ‹‹ቲክቶክ›› በሚባለው የማህበራዊ ሚዲያ እጅግ መረን የለቀቁ ነገሮች ይታያሉ፤ አንዳንዶቹም በግልጽ ‹‹ተከታይ ለማብዛት ብዬ ነው›› ሲሉ ይሰማል:: የተከታይ ማብዛት ጥቅሙ ማስወቂያ ማግኘት ነው፤ የማስታወቂያ ጥቅሙ ደግሞ ገንዘብ ማግኘት ነው:: በነገራችን ላይ ለእነዚህ ‹‹ባለጌ›› ለተባሉት ወጣቶች ማስታወቂያ የሚሰጣቸው በባህልና ወግ ታንጾ ያደገ ነው የሚባለው ይሄው ከ35 እስከ 45 ዓመት እና ከዚያ በላይ ያለው ነው:: ከዚያ በታች ያሉት ያን ያህልም የምርትና አገልግሎት ባለቤት የሚሆኑ አይመስለኝም፤ ስለዚህ የዘመኑ ባህሪም ነው ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል:: መስተካከል ካለበትም ሊያስተካክለው የሚገባው ይሄው ከ35 ዓመት በላይ የሆነው ትውልድ ነው፤ ምክንያቱም ታናናሾቹ ናቸው::
የ90ዎቹ ትውልድ ዝም ብሎ በትዝታ ብቻ መቆዘም የለበትም:: የዘመኑን ባህሪ መረዳት አለበት:: ከዘመን ዘመን ነገሮች ይቀያየራሉ:: ዘመን ቴክኖሎጂ ብቻ አይደለም ይዞ የሚመጣው፤ አስተሳሰብ ጭምር ይቀየራል:: ከዛሬ 100 ዓመት በፊት የነበረ አስተሳሰብና ሥነ ልቦና ዛሬ ላይ አይኖርም፤ የዛሬውም ከዛሬ 50 እና 100 ዓመት በኋላ አይኖርም:: አመለካከት እና ሥነ ልቦና ዝግመተ ለውጥ አለው::
የ90ዎቹ ትውልድ ዘመኑን የዋጀ እንቅስቃሴ ያድርግ ሲባል ግን የግድ እንደ ታናናሾቹ ልቅ እና ባለጌ ይሁን ማለት አይደለም:: እዚህ ላይ አንድ ችግር እንዳለ ይገባኛል:: በአሁኑ ጊዜ ቁም ነገር የሚከታተል የለም፤ ቁም ነገር ይዚህ ብትወጣ ተከታይ አታገኝም የሚባል ነገር አለ:: ትክክል ነው! ብዙ ተከታይ ያላቸው ነውር ነገሮችን የሚናገሩት ናቸው:: ዳሩ ግን መለኪያችን የማህበራዊ ገጾች አማራጮች ብቻ መሆን የለባቸውም:: ሌሎች አማራጮችም መታየት አለባቸው:: የዘመኑ አዋጪ ነገር እሱ ብቻ ነው ተብሎ ስለታሰበ ነው እንጂ ሌሎች የሥራ ዘርፎችም አሉ::
በሌላ በኩል ልብ መባል ያለበት፤ የ90ዎቹ ትውልድ ሆነው ብዙ ስኬታማ የሆኑ አሉ:: ቤትና መኪና ከመግዛት አልፈው ትልልቅ የንግድ ባለቤት የሆኑም አሉ::
ሲጠቃለል፤ የመሃሉ ትውልድ ከታላላቆቹም ከታናናሾቹም ያልሆነ ዘመን የካደው ትውልድ ቢመስልም፤ ዘመኑን የሚመስል የአመለካከት አብዮት ሊያመጣ ይገባዋል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም