
ሎተሪ በጣሊያን ፍሎረንስ ከተማ መጀመሩን ሰነዶች ያስረዳሉ:: ቃሉ ሎቶ ከሚለው የጣሊያን ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙ ሰውና መልካም አጋጣሚ ማለት ነው። ሎተሪ ቁጥር ያላቸውን ትኬቶች በመሸጥ እና ከቁጥሮቹ ዕጣ በማውጣት ለዕድለኞች በያዙት ቁጥር መሠረት አሸናፊ የሚሆኑበት ነው::
የሎተሪ ዲፊተርስ ሶፍትዌር ድረ ገጽ በጥንታዊት ሮም ሎተሪን እንደ መዝናኛ ይገለገሉበት ነበር ይላል:: የሮም ቄሳሮች በቅንጡ ግብዣዎች ግብር ሲያበሉ የሎተሪ ትኬት ይሸጥ እንደነበርና አሸናፊዎቹ፤ ባሪያዎች፣ ርስት (መሬት) ወይም ዋጋ ያላቸው ነገሮች ይቀበሉ ነበር:: ሎተሪዎቹ ዘወትር ሰፊ ሕዝባዊ ሁነት እና በማኅበራዊ ስብሰባ ጋር የተጣመረና የሚጫወቱበት እንደነበር ያስረዳል:: አውግስጦ ቄሳር ከክርስቶስ ልደት በፊት 12 ዓ.ም. ሎተሪ በማጫወት ለአሸናፊዎቹ ጠቃሚ እቃዎች እና ባሪያዎች በመስጠት በገቢው በሮም ለተገነቡት አዳዲስ ሕንጻዎች መደጎሚያ አውሎታል::
በምጣኔ ሀብት ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን የሠሩትና በጁሱፕ ባላሳኝ ኪርግዝ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤርሜካ ላይሊኤቫ ኢኮኖሚክ ፎረም ጆርናል ቅጽ14 ቁ.1 /2024 ላይ ባወጡት ጥናት ግን ሎተሪ በአውሮፓ በቀዳሚነት የጀመረችው በርግስ የአሁኗ ቤልጅየም እኤአ በ1466 ነች ይላሉ:: በሎተሪው ተሳትፎ በዕድለኛነት ያሸነፈ ማንኛውም ሰው ገንዘቡን ይወስድ ነበር:: የሎተሪው ትኬት ተሸጦም በተገኘው ገቢ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ይደጉሙበት ነበር::
በእንግሊዝ ሎተሪ የተዋወቀው ንግሥት ኤልሳቤጥ ቀዳማዊ በ1559 ዘውድ እንደጫኑ ሲሆን በወቅቱ ሀገሪቱ የገጠማትን የኢኮኖሚክ ተግዳሮት ቀልብሰውበታል:: በወቅቱ በአስርት ሺዎች የሚቆጠሩ የሎተሪ ትኬቶች ለሽያጭ ቀርበው ወርቅ፣ ብር (ገንዘብ) እና ስጋጃ አሸናፊዎች ይወስዱበት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ::
በዓለም ከዘመናችን ጋር ተዛማጅና ተጣማጅ የሎተሪ ቀመር (ፎረሙላ) በቀዳሚነት የተከሰተው ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ልደት 206 -195 በቻይና መሆኑን ተባባሪ ፕሮፌሰር ኤርሜካ ላይሊኤቫ ያወጡት ጥናት ያሳያል:: በወቅቱ የሀገሪቱ መሪ ግርማዊ ጋኦ ትዙ የሎተሪን ሃሳብ በማነሳሳት ሠራዊቱን ለመደጎሚያነት ተገልግለውበታል:: ሎተሪው የሚሸጠው ዘወትር ሆኖ በማለዳና በምሽት ዕጣው ይወጣ ነበር:: በወቅቱ የሎተሪው ትኬት ገቢውን የቻይናን ግዙፍ ሠራዊት ከመጠበቅ አልፎ ለታላቁ የቻይና ግንብ ግንባታ መደጎሚያ ተጠቅመውበታል::
በመላው ዓለም ሎተሪ የኅብረተሰቡን መሠረታዊ ጉዳዮችን፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ለመደገፍ ይሠራል:: ድንገተኛ አደጋዎችን በመከላከል ላይም ይረዳል:: የሎተሪ ሥራ ሠፊና ተለዋዋጭ እያደገና እየተመነደገ የሚሄድ ለድርጅቶች ገቢ የሚያመነጭ ብቻ ሳይሆን ለመንግሥት ግምጃ ቤት እና ለብዙ ረድኤት ድርጅቶች ጉልህ ገቢዎችን የሚለግስ ኢንዱስትሪ ነው::
በአንዳንድ መንግሥታት እንደ ሕገ ወጥ የሚታይ ሲሆን ሌሎች ሀገራት ደግሞ የራሳቸውን ብሔራዊ ሎተሪ አቋቁመው ይሠራሉ:: መንግሥት በሎተሪ ላይ የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት የሎተሪ ጨዋታዎችን የመስመር ላይ ቲኬትን ጨምሮ በመፍቀድ ወይም በማገድ እንዲሁም በመቆጣጠር የሚሠራ ነው:: በሀገራችንም ማንኛውም ሎተሪ አጫዋች ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ማገድም ሆነ መፍቀድ የሚችለው ብሔራዊ ሎተሪ አገልግሎት ነው::
በሉዓላዊነት (Globalization) ዘመን ደግሞ ከመደበኛው ባሻገር ‹‹ኦን ላይን›› የምንለው የመስመር ላይ ሎተሪ በሥራ ላይ ውሏል:: ከጊዜ ወደ ጊዜም የኦንላይን ሎተሪ ተጫዋቾች የገቢውና የተጠቃሚው ሰው ብዛት እየጨመረ ነው:: በዓለም አቀፍ ደረጃ እኤአ ከ2017 እስከ 2023 የመስመር ላይ ሎተሪ ገቢ ከነበረበት 5 ነጥብ 46 ቢሊዮን ዶላር ወደ 15 ነጥብ 24 ቢሊዮን ዶላር ጨምሯል:: በተጠቃሚ ሰው ብዛት ከላይ በተጠቀሱት ዓመታት መሠረት ደግሞ ከ13 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወደ 29 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተመንድጓል::
እኤአ ከ2024 እስከ 2029 ድረስ ገቢው እስከ 22 ነጥብ 15 ቢሊዮን ዶላር ያድጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የመስመር ላይ ሎተሪ ተዋናዮች ደግሞ በ2029 ወደ 42ነጥብ 6 ሚሊየን እንደሚደርሱ ይጠበቃል:: ይህም የመስመር ላይ ሎተሪ በተደራሽነቱ ብዙውን የሚያሳትፍ፤ ኅብረተሰቡም ለመጫወት ፍላጎት ያለው መሆኑንና ብዙ ተጠቃሚዎችንና ወሳኝ ገቢዎችን ማመንጨት የሚፈልጉትን ሀገራትንም ሆነ ሰዎችን የበለጠ እየሳበ የሚሄድ የዘርፉ ዋና መጫወቻ ኢንዱስትሪ መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ::
ቀደም ሲል በሀገራችን ከተሞች የሎተሪ ዕጣ እያዞሩ በግላቸው የሚያጫውቱ ነበሩ:: ሎተሪ በጣም በመስፋፋቱ በ1938 ዓ.ም ሎተሪን ሕገ ወጥ በሚል የሚያግድ አዋጅ ወጣ:: በወቅቱ በግል የሚካሄዱት የሎተሪ ጨዋታዎቹ ኪሳራ በሚል ስያሜ ይጠሩ እንደነበር ሰዎች ይናገራሉ:: ስያሜው በራሱ ኪሳራ መባሉ ለተጫዋቾቹም ሆነ ለአጫዋቾቹ ብዙም ተስፋ የሚጭር ሳይሆን ተስፋ የሚቀጭ ይመስላል::
በኢትዮጵያ በመንግሥት የተደራጀ ሎተሪ የተመሠረተው በ1954 ዓ.ም በወጣ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጅ ነው:: ብሔራዊ ሎተሪ ከተቋቋመ 60 ዓመቱን እየነገደ ቆይቶ ወደ 65ኛ ዓመቱ እየነጎደ ነው:: ብሔራዊ ሎተሪ እንደተጀመረ ለማስተዋወቅና ለመሸጥ ስድስት ወራት ለሚጠጋ ጊዜያት ፈጀበት:: ሰውም እንግዳ ስለነበር የሎተሪ ቲኬት ለመግዛት ያሳየው ጉጉት አልነበረም:: የመጀመሪያው ዕጣ የሽልማቱ ጣሪያ 50 ሺህ ብር ነበር::
በገና ዕለት ታኅሣሥ 29 በጃንሜዳ ከፈረንሳይ በመጡ ማሽኖች ሰዎች በተሰበሰቡበት የመጀመሪያው ሎተሪ ዕጣ ወጣ:: ዕድለኞቹም የኤርትራ ክፍለ ሀገር የሀማሴን አውራጃ ነዋሪዎች ነበሩ:: አንድ ሴትና አራት ወንዶች በወቅቱ 50 ሺህ ብር የነበረውን ትልቁን ሽልማት ወስደዋል:: ሙሉውን ዕጣ ከነበረው አምስት ትኬት እያንዳንዳቸው 10 ሺህ ብር ደርሷቸዋል::
የሎተሪ ዕድለኞቹ አንድ ላይ ቆመው የተነሱት ፎቶ በብሔራዊ ሎተሪ ሕንፃ ውስጥ ተሰቅሎ ለማየት ችያለሁ:: ከሥሩ የመጀመሪያዎቹ የሎተሪ ዕድለኞች ይላል:: ብሔራዊ ሎተሪ ሲመሠረት በአዲስ አበባ ከነበሩት ሦስት ማከፋፈያዎች በተጨማሪ በናዝሬት (በአዳማ)፣ በድሬዳዋና በአስመራ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች፤ ነበሩት:: አሁን በመላው ሀገሪቱ 55 ቅርንጫፎች እና ከ200 በላይ ወኪሎች አማካይነት ይሠራል::
ብሔራዊ ሎተሪ ሲመሠረት ከነበረው 50 ሺህ ብር ሽልማት ተነስቶ ከአራት ዓመት በፊት የሽልማት ጣሪያው በዕንቁጣጣሽ ሎተሪ 20 ሚሊዮን ብር አድጓል:: በያዝነው ዓመት ደግሞ የዲጂታል ሎተሪን በይፋ ጀምሯል:: በተጨማሪም የቲኬት ሎተሪው የሽልማት ጣሪያው ወደ 50 ሚሊዮን ብር ተመንድጓል:: ለመጋቢት 2017 ዓ.ም የሚወጣ የ50 ሚሊዮን ሎተሪ እየተሸጠ ነበር::
የ50 ሚሊዮን የሽልማት ዕጣ በሎተሪው ታሪክ ትልቁ የእድለኛ ክፍያ ነው:: ነገር ግን በመጋቢት የታሰበው ሎተሪ መውጣት አልቻለም:: ወደ ግንቦት ተዘዋውሯል:: ያው በሚፈለገው መጠን ትኬቱ ስላልተሸጠ ሊሆን ይችላል:: የዕጣው ቀን መራዘሙ ግን የብሔራዊ ሎተሪ ተዓማኒነት ላይ ጥያቄ ያስነሳል:: የብር ነገር ስሱ ስለሆነ ለወደፊት ቲኬት ቆራጩ ጥያቄ እንዳያነሳ ተደርጎ መሠራት አለበት::
ዘንድሮ በትንሳኤ ሎተሪ የ10 ሚሊዮን ብር ሎተሪ አውጥቶ ነበር:: አሸናፊው ዕጣ ዜሮ ቤት ሲሆን ማስተዛዘኛው ደግሞ ስድስት ቁጥር ነው:: ሙሉ ዕጣው ሦስት ቲኬት በሆነው በዚህ ሎተሪ በማስተዛዘኛው ዕጣ መሠረት 60 ብር ያገኛል:: ብሔራዊ ሎተሪ አገልግሎት ያሳተመው የዕጣ ማሳያ ግን ማስተዛዘኛ ዕጣ አሸናፊው የሚወስደው ብር 60 ሲሆን ትኬት ማውጫው ላይ እና ሎተሪው ላይ የማስተዛዘኛ ሽልማቱ 50 ብር ይላል:: ሙሉ ትኬቱ ሦስት ነው:: አንዱ ቲኬት የተሸጠው በ20 ብር ነው:: ሙሉ ቲኬት 60 ብር ማለት ነው:: እንደዚህ ዓይነት ግድፈቶች የሎተሪ አገልግሎቱ ላይ ተግዳሮት የሚፈጥሩ ናቸው:: ጥንቃቄ ማድረጉ ለተቋሙ ስምና ዝና ነው::
ብሔራዊ ሎተሪ ሲነሳ ብዙ ጊዜ ሎተሪ የደረሳቸው መሐመድ አብደላ የተባሉ የጎንደር ነዋሪ ይጠቀሳሉ፤ በዚህም ሰው መሐመድ ሎተሪ በሚል ይጠራቸው ነበር:: አፄ ኃይለሥላሴም የመኪና ባለዕድል ነበሩ:: እሱን መልሰው ሸልመዋል:: አርቲስት ሀረገወይን አሰፋም የአምስት መቶ ሺህ ብር ባለዕድል ነበረች:: የብሔራዊ ሎተሪ ካስተዳደሩት መካከል አቶ አስፋው ዳምጤ እና ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሦስተኛ አመራር ሆነው አገልግለዋል:: መዓዛ ቅጣው ፈጣን ሎተሪን በማስጀመር አገልግሎቱን ለማሻሻል ጥረት አድርገዋል:: እንዲያውም በወቅቱ ወጣቱ ሁሉ በፈጣን ሎተሪ ቲኬት ተስቦ እየገዛ ይፍቅ ይዝናናም ስለነበረ ‹‹መዓዛ ቅጣው ፒያሳ ያለችው፣
የጨዋን ልጅ ሁሉ ፋቂ አረገችው››
ተብሎ ተገጥሞባቸዋል::
በ1954 በአዋጅ የተመሠረተው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥር 26 ቀን 2001 ዓ.ም በደንብ ቁጥር 108/ 2001 እንደገና ተቋቋመ፤ ይህም በደንቡ ላይ አንዳንድ ማሻሻያዎችን ለማድረግ እና አሠራሩን ከዘመኑ ጋር ጎን ለጎን ለማስኬድ ነው::
ደንቡ የሽልማት አሸናፊው በዕድል አሰጣጥ ወይም በማናቸውም ሌላ ዘዴ የሚታወቅበት ጨዋታ ወይም ድርጊት ሲሆን ቶምቦላ ሎቶን፣ ፈጣን ሎተሪን፣ የቁጥር ዕድልን፣ የተደራራቢ ሽልማት ሎተሪን፣ ቢንጎን የስፖርት ውርርድ ሎተሪንና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችን እንደሚጨምር ያስረዳል:: ብሔራዊ ሎተሪ ሥራው ሎተሪ ማሳተምና መሸጥ፣ ሕጋዊ የሎተሪ ሥራ ለሚሠሩ ፈቃድ መስጠትና ለስፖርት ውድድሮች ዕጣ ለሚያወዳድሩ ፈቃድ በመስጠት 15 በመቶ ለልማት እንዲውል በመቁረጥና ግብርም እንዲገብሩ በማድረግ መቆጣጠር ነው::
ይህን የግል ዕጣ አሁንም እያዞሩ እያስከፈሉ ቁጥር እየሰጡ የሚጠቀሙ አሉ:: በቲኬት እስከ መቶ ከሚደርሱ ሰዎች ገንዘብ ሰበስበው ዕጣ አውጥተው አንደኛ የወጣውን ዕጣ ነግረው ሰጥተው የቀረውን ወደ ራሳቸው ካዝና ይከታሉ:: የግሉ ዕጣ በተለይ ንግድ በሚበዛባቸው ቦታዎች በመጠጥ ቤቶችም እየተሸጠ ዕጣ የሚወጣበትና ለባለዕድለኛው የሚሰጥበት ነው:: በዓላት ሲሆኑ ከበግ ጀምሮ በሬ ሁሉ በንግድ ቦታ አዙረው ዕጣ ያወጣሉ::
ቲኬት አዟሪዎቹ ረጅም ዓመት የሠሩበት ሥራ ስለሆነ መሥራታቸውን ይበረታታል:: ግብር መረብ ውስጥ አለመግባታቸው ግን የክትትል ማነሱን ያሳያል:: የዚህ ጨዋታ ዋና ተዋናዮቹ መካከል ብዙዎቹ ቀን ቀን ሥራ የሌላቸው ናቸው:: ቀን ቀን በመርካቶ የግል ሥራቸውን እየሠሩ ሰዓታቸው ሲደርስ ግሮሰሪያቸው ሄደው የሚያጫውቱ አሉ:: አጫዋጮቹ ባሉባቸው ቦታዎች በብዛት ተፎካካሪ አጫዋች አይገኝም::
ይህን ጨዋታ በአንዳንድ የቀበሌ መዝናኛ የሚያጫውቱ አሉ:: አንዳንድ ክበቦች ደግሞ አጫዋቾቹ እንዳያጫውቱ የሚያግዱ አሉ:: ምክንያቱን ደግሞ ሰው ለመጠጣትና ለመዝናናት መጥቶ አንድ ሁለት ቀምሶ ብሩ በዕጣ ጨዋታው ጨርሶ ስለሚወጣ ነው ያሉን አሉ:: ያም ሆነ ይህ ግን የግል ዕጣ የሚያዘዋውሩ ሰዎችን ግብር ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ የሚደረገው ቁጥጥር የላላ ነው::
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሎተሪ አገልግሎት ከወረቀት ቲኬት ሎተሪ በተጨማሪ የዲጂታል ሎተሪ የተጀመረው ኢትዮ ቴሌኮም እና የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በቴሌብር የዲጂታል ሎተሪ ለመጀመር ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረጉት የስምምነት ፊርማ ነው:: በያዝነው ዓመት ሚያዝያ 2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ሳምንት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሎተሪ ራሱን ችሎ የዲጂታል ሎተሪ በማስተዋወቅ ይፋ አድርጓል:: ይህ ዘመናዊ ሎተሪ ከወረቀት ሎተሪ በተጨማሪ በዲጂታል መላ በሞባይል መተግበሪያ አማካኝነት ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ ነው::
በዲጂታል ሎተሪ ለረጅም ዓመታት በመፋቅ እድለኛ የሚያደርጉት የፈጣን እና የቢንጎ ሎተሪዎችም በዲጂታል መንገድ ተካተውበታል። ከሃምሳ ሚሊዮን ብር ሽልማት አንስቶ በርካታ የጨዋታ አማራጮችን የቀረበበት ሲሆን በኢትዮጵያ በስምንት የሀገራችን ቋንቋዎች መዘጋጀቱ ታውቋል። አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቲኬት ሎተሪ ወደ ዲጂታል ሎተሪ በተጨማሪ በሃምሳ ሺህ ብር ሽልማት የከፈተውን የእድል በር ወደ ሃምሳ ሚሊዮን ብር ከፍ አድርጎታል። ዲጂታል ሎተሪ በሃምሳ ሚሊዮን ብር መጀመሩ ወደፊት የሽልማት ጣሪያው እንደሚያድግና በተደራሽነቱ ብዙ ሰዎች ዕድላቸውን ለመሞከር እንደሚታደሙበት ይጠበቃል::
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ዲጂታል ሎተሪ መጀመር ቀደም ሲል ለሕትመት እና ሌሎች ተያያዥነት ላላቸው ሥራዎች ያወጣው የነበረውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ይሆናል:: ይህም ማለት ግን የወረቀት ቲኬት ደህና ሰንብት ማለት አለመሆኑ ይሰመርበት:: ዲጂታል ሎተሪ ለብሔራዊ ሎተሪ ደንበኞች ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችለው ነው::
በሎተሪ ገበያ መሪ የሆኑ ሀገሮች የሎተሪ ገቢን ማኅበራዊ ጉዳዮችን ለመደጎምና ለሰብዓዊ ፕሮጀክቶች ለመደገፍ በአማራጭ ምንጭነት ይጠቀሙበታል:: በመስመር ላይ ሎተሪ እንግሊዝ በየዓመቱ 10 ቢሊዮን ዶላር በመሰብሰብ ከዓለም ታዋቂና ቀዳሚ ሆናለች:: ሀገሪቱ አብዛኛው ገቢ ለመንግሥትና ለረድኤት ተቋማት በማዋል ከዓለም ሀገሮች ሁሉ ፊታውራሪ የሆነችበት ነው::
ከላይ እንደተገለጸው በየሀገራቱ የሎተሪ ቲኬት ገቢ ለረድኤት ድርጅቶች እና ማኅበራዊ ጎዳዮች መደጎሚያ የሚውል ነው:: ቻይና በዓለም ዝነኛ የሆነውን የታላቁን የቻይና ግንብ የገነባቸው ከሎተሪ ቲኬት ሽያጭ ገቢዎች ነው:: የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሎተሪም በሎተሪ ሽያጭ ለጳውሎስ ሆስፒታል፣ ወወክማና ቼሻየር ሲቋቋሙ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋምም ዋና አስተዋጽኦ ካደረጉት ነበር:: ከሜክሲኮ ኦሎምፒክ ጀምሮ ከአትሌቲክስ ጐን አልተለየም::
ዜጋው ሎተሪ (ብሔራዊ ሎተሪን ማለቴ ይሰመርበት) ሲቆርጥ እና በዲጂታል ሎተሪ ሲታደም ገንዘቡን ከግራ ኪሱ ወደ ቀኝ ኪሱ እንዳዛወረው መቁጠር አለበት:: ገንዘቡ ተሰብስቦ ለልማት ስለሚውል:: ከሎተሪ አዟሪዎች ሎተሪ መቁረጥም ሰዎችን ለሥራ እንደማበረታታት ነው:: የግሎቹ ዕጣ አዟሪዎች ወደ ብልፅግና ይጠጋሉ፤ የብሔራዊ ሎተሪዎቹ ጎስቆል ያሉ ይመስላሉ:: ግን የሎተሪ ዕጣ አዟሪዎች ዕጣ ፈንታቸው እንደ ግሎቹ ባይሆንም የሚበላሽበት ነገር የለም፤ ከሥራ ፈትነት መራቃቸው በራሱ ከአልባሌ ነገሮች እንዲርቁ ያግዛቸዋል:: በግል ያነጋገርኳቸውም፤ የሎተሪው ሥራ ኑሮዋቸውን ለመደገፍ እንደሚረዳቸውና መሥራትም ግዴታ ነው ብለውኛል::
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም