የአርበኞችን ታሪክ በምን እንድገመው?

ጀግንነት የዘመን ዓውድ አለው። በጥንት ዘመን የነበረው ጀግንነት አውሬ እያደኑ መግደል ነበር። በዚህ ዘመን ግን እንስሳት እያደኑ መግደል ኋላቀርነት ብቻ ሳይሆን ወንጀል ሆኗል። የሰው ልጅ ከራሱ አልፎ የእንስሳት መብት ተሟጋች እና ጠባቂ ሆኗል። በጥንት ዘመን ማደን እና መግደል የወንድነት መለኪያ ነበር፤ በዚህ ዘመን ግን ወንድነት የሚባል ነገር ፆታን ለመለየት እንጂ ከጀግንነት ጋር የተያያዘ አይደለም። ዘመን እንዲህ ነው፤ የጀግንነትን ትርጉም ይበይናል። የዚህ ዘመን ጀግንነት ብልህ እና አስተዋይ ሆኖ በዘመናዊነት አሸናፊ መሆን ነው።

ቀደም ባለው የነገሥታቱ ዘመን ጀግንነት ተጋዳይነት ነበር። ይህ በአውሮፓም ሆነ በሌሎች የዓለም ሀገራት የነበረ ታሪክ ነው። በዚህ ዘመን ግን ጀግንነት ማለት በዲፕሎማሲ እና በኢኮኖሚ አቅም ማሸፍ ሆኗል። የጦርነትም አይነቱ ተለይቷል። ምንም እንኳን አውዳሚ ጦርነት ዛሬም ያለ ቢሆንም፤ አስመስጋኙ እና ጀግና የሚያሰኘው ግን በኢኮኖሚ እና በዲፕሎማሲ ማሸነፍ ሆኗል። እነ ጃፓን በሥልጣኔ የሚጠቀሱት በዚህ ጀግንነታቸው ነው። ጃፓን የጦርነት ታሪክ የነበራት ቢሆንም፤ የዘመኑ ጀግንነት ሥራ እና አስተዋይነት ነው በማለት የሥልጡንነት ዘመቻ ጀመረች። እነሆ ከዓለም በልጻጊ ሀገራት በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሆነች።

ዛሬ በኢትዮጵያ የአርበኞች ቀን ነው። የታሪክ ይዘቶቹን ለሳምንቱ በታሪክ ዓምዳችን ልተወውና በታሪክ አረዳድ እና በጀግንነት ትርጉም ላይ ግን ትዝብቴን ላካፍል።

በተለያየ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚቀርቡ ብዙ ምሁራን እና ፖለቲከኞችን እንከታተላለን። የሚቀርቡት በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ፣ ወይም በሀገሪቱ ቀጣይ የዕድገትና ብልፅግና ጉዞዎች ላይ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ ነው። ልብ ብላችሁ ከሆነ ግን ብዙ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ከወቅታዊ እና ከወደፊት ጉዳይ ይልቅ መቶ እና ሺህ ዓመታት ወደኋላ ተመልሰው ‹‹በዚህ ጊዜ እገሌ እንዲህ አድርጎ ነበር!›› ይላሉ። አብዛኞቹ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የተቸነከሩ ናቸው። አስቂኝ በሆነ ሁኔታ ከመቶ እና ከሺህ ዘመናት በፊት የነበሩ መሪዎችንና ሥርዓቶችን እየጠቀሱ ‹‹ጨቋኝ ነበሩ›› ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ከመቶ እና ከሺህ ዘመናት በፊት ከነበረ ትውልድ ጋር እየተወዳደሩ ነው። ዛሬ ላይ እንኳን ‹‹አለ! የለም!›› እያከራከረ ያለውን ዴሞክራሲ ከ100 እና ከ200 ዓመት በፊት በነበረ ሥርዓት ‹‹ዴሞክራሲያዊ አልነበሩም!›› እያሉ ይወቅሳሉ። እሺ አልነበሩም! ስለዚህ ምን ይሁን? ይከሰሱ? የእስር ማዘዣ ይውጣባቸው? ከሥልጣን እናውርዳቸው? እነዚያ ሰዎች እኮ እንኳን ሕይወታቸው አጥንታቸው ራሱ በአካል አይገኝም! በአጭሩ የሉም!

ታሪክ በታሪክነቱ ይጠቀሳል። ከነበረው ስህተት እንማራለን፣ ከነበረው ጠንካሬም እንማራለን። ስህተታቸው እንዳይደገም፣ ጥንካሬያቸው እንዲቀጥል ይሠራበታል። እንዴት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በ19ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ ነገር ላይ ሙጭጭ ይባላል? ያ ትውልድ እና ይሄኛው ትውልድ ማለት እኮ ሌላ ዝርያ እና ሌላ ዝርያ እንደማለት ነው። አንድ የስብሃት ገብረእግዚአብሔር አገላለጽ እንጠቀም።

ስብሃት በወጣትነቱ ዘመን ወጣትነትን ሲገልጽ ስለአዛውንቶች ቀጥቃጣነትና ነዝናዛነት የተናገረው ነገር ነበረው። እሱ አዛውንት ከሆነ በኋላ ደግሞ ስለአዛውንትነት ውበትና ፀጋ ተናገረ። አንድ ጋዜጠኛ፤ ያኔ አዛውንቶችን እንዲህ ብለህ ነበር፤ አሁን ደግሞ አዛውንትነትን እንዲህ እያሞጋገስክ ነው አለው። የስብሃት መልስ አፍ የሚያስይዝ ነበር። ‹‹እየውልህ! ይሄን ጥያቄ መጠየቅ ያለብህ ያኛውን ስብሃት ነበር!›› አለው። የስብሃት ሃሳብ፤ ያኔ በወጣትነቱ የአዛውንትነትን ቦታ ስለማያውቀው ያለበትን እያጣጣመና እየወደደ ነበር። እሱ አዛውንት ከሆነ በኋላ ደግሞ የአዛውንትነት ውበት ታየው። ስለዚህ ስብሃት በ30ዎቹ እድሜው ውስጥ እና በ60ዎቹ እድሜው ውስጥ ሌላ ሰው እና ሌላ ሰው ማለት ነው! ይህ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው።

ይህ እንግዲህ 100 ዓመት እንኳን በማይሞላ የአንድ ሰው እድሜ ውስጥ ብቻ የሚታይ ለውጥ ነው። ከመቶ እና ከሺህ ዘመናት በፊት ያለውን ትውልድ ከዚህኛው ትውልድ ጋር እያነፃፀሩ ማየት ኋላቀርነት ነው። ለዚያውም ከእነርሱ ያልተሻለ ሁኔታ ላይ ሆነን ማለት ነው። 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥነውን ይቅርና እነርሱ የሠሩትን እንኳን ሳንሠራ ማለት ነው።

ይህ ያለፉ ነገሮች ላይ ብቻ መቸንከር ‹‹ምን ችግር አመጣ?›› ከተባለ ከዓለም ጋር እንዳንራመድ ያደርገናል፤ አድርጎናል። የሠለጠኑ ሀገራት እጅግ ዘግናኝ የሆኑ የእርስ በእርስና ጦርነቶችን አድርገዋል። ዛሬ ላይ ግን ያ ጉዳያቸው አይደለም። ያ ያለፈ ታሪክ ለእነርሱ ታሪክ ብቻ ነው። ‹‹ያኔ ለካ የሰው ልጅ እንዲህ ነበር!›› እያሉ የሚዝናኑበትና የሚገረሙበት እንጂ ዛሬ ላይ የሚገዳደሉበት አይደለም። ይህን አልፈው ሄደዋል። ትንታኔዎቻቸው ሁሉ ስለአሁናዊና ወደፊታዊ ሁኔታዎች እንጂ 100 ዓመት ወደኋላ እየተመለሱ አይደለም። ዕለቱን በታሪክ የሚያስተውሱትም የዚያ ዘመን ክስተት ለዚህኛው ትውልዳቸው ስለሚያስገርም ወይም ስለሚያዝናና እንጂ ‹‹ተነስ!›› ለሚል ቅስቀሳ አይደለም። ቢቀሰቅሱም የሚነሳላቸው የለም።

እኛ ግን በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን የሚኖረን የሰውነት ዋጋ ይወርዳል። አዕምሯዊ ሥልጣኔ ከሌለን፣ ማሰብና ማሰላሰል ካልቻልን፣ አገልግሎታችን አካላዊ ብቻ ይሆናል ማለት ነው። አካላዊ አገልግሎት ደግሞ በዚህ ዘመን በቴክኖሎጂ እየተተካ ነው። በዚህ ከቀጠልን በመጭው ዘመን በጉልበት ሥራ እንኳን ማገልገል አንችልም። የጉልበትን ሥራ ማሽን እየተካው ነው። እንኳን የጉልበትን ሥራ የአዕምሮ ሥራ የሚጠይቁ ሥራዎች ራሱ በሮቦት እየተተኩ ነው። የሰው ልጅ ከሮቦት የተሻለ አስተሳሰብ ኖሮት የሚያገለግለው ነገር ከሌለው ከሰው ሠራሽ ማሽን በታች ሆነ ማለት ነው። ይህ ሊቆጨን ይገባል።

ትልልቅ ፈጠራና ግኝት ይቅር! ቢያንስ ግን ስለአሁናዊና የወደፊት ጉዳዮች እንኳን ማውራት ይቸግረን? በሙያ ዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት አሁናዊና ወደፊታዊ መላ ሲናገሩ አይሰማም። ሐኪሙም፣ መሃንዲሱም፣ ጠበቃውም፣ የሃይማኖት አባቱም… ታዋቂ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው መገናኛ ብዙኃን ላይ ሲቀርቡ፤ ሮጠው ወደኋላ ነው። ዓለም የደረሰበትን ተሞክሮ አምጥተው ከመናገር ይልቅ የጨቋኝና ተጨቋኝ ታሪክ ያመጣሉ። የእኔ 7 ዘር ጨቆነም ተጨቆነም ለእኔም ሆነ ለልጆቼ ምንም ነው! ያ ድርጊት ቅድመ አያቶቼ የኖሩበት ዘመን ባህሪ ነው፤ እኔ መኖር የምፈልገው ያለሁበት ዘመን እየኖረ ያለውን ሕይወት ነው። ለልጆቼም ማውራት የምፈልገው ቀጣዩ ትውልድ ሊኖርበት የሚችለውን የዓለም ፍጥነት ነው። አሁን ላይ የሚቀርቡ ትንታኔዎችና ክርክሮች ሁሉ ከዛሬ 100 ዓመት በፊት በነበሩ ነገሮች ላይ ከሆነ ግን ለቀጣዩ ትውልድ ሰነድ ሆኖ የሚቀመጠው ንትርክ ይሆናል ማለት ነው። የዚህኛውን ዘመን ክስተቶች በበቂ ሆኔታ የሚሰንድለት አያገኝም ማለት ነው። ይህ ደግሞ የትውልድ ክፍተት ይፈጥራል።

ስለዚህ ዓለም ወደፊት ብቻ እያሰበ፣ እኛ ወደኋላ ብቸ እያሰብን የሰለጠነው ዓለም ከሚሠራው ሰው ሠራሽ ማሽን በታች እንዳንሆን ወደፊት እናስብ! የዚህ ዘመን ጀግንነት ማለት ይህ ነው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You